በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 18

ኢየሱስ እየጨመረ ዮሐንስ ግን እየቀነሰ ሄደ

ኢየሱስ እየጨመረ ዮሐንስ ግን እየቀነሰ ሄደ

ማቴዎስ 4:12 ማርቆስ 6:17-20 ሉቃስ 3:19, 20 ዮሐንስ 3:22–4:3

  • የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አጠመቁ

  • መጥምቁ ዮሐንስ ታሰረ

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በ30 ዓ.ም. በጸደይ ወቅት ፋሲካን ካከበሩ በኋላ ኢየሩሳሌምን ለቀው ሄዱ። ይሁን እንጂ በገሊላ ወደሚገኘው መኖሪያቸው ወዲያውኑ አልተመለሱም። ከዚህ ይልቅ ወደ ይሁዳ ክልል ሄደው ብዙዎችን አጠመቁ። መጥምቁ ዮሐንስ ይህንኑ ሥራ ማከናወን ከጀመረ አንድ ዓመት ገደማ ሆኖታል፤ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አንዳንዶቹ አሁንም ከእሱ ጋር ናቸው፤ ምናልባትም በዮርዳኖስ ወንዝ አካባቢ ሳይሆኑ አይቀርም።

እርግጥ፣ ኢየሱስ ራሱ ማንንም አላጠመቀም፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን የእሱን መመሪያ በመከተል ሰዎችን እያጠመቁ ነው። በዚህ ወቅት ኢየሱስም ሆነ ዮሐንስ እያስተማሩ ያሉት፣ የአምላክን የሕግ ቃል ኪዳን በመጣስ ለፈጸሙት ኃጢአት ንስሐ የገቡ አይሁዳውያንን ነው።—የሐዋርያት ሥራ 19:4

ሆኖም የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ቅናት ስላደረባቸው “ከአንተ ጋር የነበረው . . . ሰው [ኢየሱስ] እያጠመቀ ነው፤ ሰዉም ሁሉ ወደ እሱ እየሄደ ነው” ብለው በኢየሱስ ላይ የተሰማቸውን ቅሬታ ለዮሐንስ ነገሩት። (ዮሐንስ 3:26) ዮሐንስ ግን አልቀናም። በኢየሱስ ሥራ መሳካት የተደሰተ ሲሆን ደቀ መዛሙርቱም እንደ እሱ ሊደሰቱ እንደሚገባ ነገራቸው። “‘እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤ ከዚህ ይልቅ ከእሱ በፊት የተላክሁ ነኝ’ እንዳልኩ እናንተ ራሳችሁ ትመሠክራላችሁ” በማለት አስታወሳቸው። ከዚያም ሁሉም ሊረዱት የሚችሉት ምሳሌ በመጠቀም እንዲህ አላቸው፦ “ሙሽራይቱ የሙሽራው ናት። ይሁን እንጂ የሙሽራው ጓደኛ በዚያ ቆሞ ሲሰማው በሙሽራው ድምፅ የተነሳ እጅግ ደስ ይለዋል። በመሆኑም የእኔ ደስታ ተፈጽሟል።”—ዮሐንስ 3:28, 29

እንደ ሙሽራው ሚዜ ሁሉ ዮሐንስም ከስድስት ወር በፊት ደቀ መዛሙርቱን ከኢየሱስ ጋር ሲያስተዋውቅ በጣም ተደስቶ ነበር። ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ የኢየሱስ ተከታዮች ሆነዋል፤ ከጊዜ በኋላም በመንፈስ ቅዱስ ይቀባሉ። ዮሐንስ፣ አብረውት ያሉት ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስን እንዲከተሉ ይፈልጋል። ዮሐንስ የተላከበት ዓላማ ለክርስቶስ አገልግሎት መንገዱን ማዘጋጀት ነው። ዮሐንስ “እሱ እየጨመረ መሄድ አለበት፤ እኔ ግን እየቀነስኩ መሄድ አለብኝ” ሲል ሁኔታውን ግልጽ አድርጓል።—ዮሐንስ 3:30

ከዚህ ትንሽ ቀደም ብሎ ኢየሱስን መከተል የጀመረ ዮሐንስ የተባለ ደቀ መዝሙር፣ ኢየሱስ ከየት እንደመጣና በሰው ልጆች መዳን ረገድ ምን ሚና እንደሚጫወት ከጊዜ በኋላ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “ከላይ የሚመጣው ከሌሎች ሁሉ በላይ ነው። . . . አብ ወልድን ይወዳል፤ ደግሞም ሁሉንም ነገር በእጁ ሰጥቶታል። በወልድ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ወልድን የማይታዘዝ ግን የአምላክ ቁጣ በላዩ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።” (ዮሐንስ 3:31, 35, 36) ይህ ሰዎች ሊያውቁት የሚገባ እንዴት ያለ ጠቃሚ እውነት ነው!

መጥምቁ ዮሐንስ፣ እሱ የሚጫወተው ሚና እንዲሁም የሚያከናውነው ሥራ እየቀነሰ እንደሚሄድ ከተናገረ ብዙም ሳይቆይ ንጉሥ ሄሮድስ አሰረው። ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን ወስዶ አግብቷት ነበር። ይህ ድርጊቱ ምንዝር መሆኑን ዮሐንስ በሕዝብ ፊት ባጋለጠው ጊዜ ሄሮድስ ወደ ወህኒ አወረደው። ኢየሱስ፣ ዮሐንስ መታሰሩን ሲሰማ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይሁዳን ለቆ “ወደ ገሊላ ሄደ።”—ማቴዎስ 4:12፤ ማርቆስ 1:14