በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 22

አራት ደቀ መዛሙርት ሰው አጥማጆች ሊሆኑ ነው

አራት ደቀ መዛሙርት ሰው አጥማጆች ሊሆኑ ነው

ማቴዎስ 4:13-22 ማርቆስ 1:16-20 ሉቃስ 5:1-11

  • ኢየሱስ የሙሉ ጊዜ ተከታዮቹ የሚሆኑ ደቀ መዛሙርትን ጠራ

  • ዓሣ አጥማጆች፣ ሰው አጥማጆች ሆኑ

የናዝሬት ሰዎች ኢየሱስን ሊገድሉት ከሞከሩ በኋላ ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አቅራቢያ ወደምትገኘው ወደ ቅፍርናሆም ከተማ ሄደ፤ የገሊላ ባሕር “ጌንሴሬጥ ሐይቅ” ተብሎም ይጠራል። (ሉቃስ 5:1) ኢየሱስ ወደዚያ መሄዱ፣ በባሕሩ አቅራቢያ የሚኖሩ የገሊላ ሰዎች ታላቅ ብርሃን እንደሚያዩ የተነገረው የኢሳይያስ ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል።—ኢሳይያስ 9:1, 2

በገሊላም ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማያት ስለቀረበ ንስሐ ግቡ” እያለ መስበኩን ቀጠለ። (ማቴዎስ 4:17) ኢየሱስ በዚህች ከተማ ውስጥ አራት ደቀ መዛሙርቱን አገኛቸው። እነዚህ ደቀ መዛሙርት ቀደም ሲል አብረውት ተጉዘው የነበረ ቢሆንም ከኢየሱስ ጋር ከይሁዳ ከተመለሱ በኋላ ቀድሞ ያከናውኑት የነበረውን ዓሣ የማጥመድ ሥራ ቀጥለዋል። (ዮሐንስ 1:35-42) ከዚህ በኋላ ግን ኢየሱስ ከእነሱ ሲለይ፣ አገልግሎቱን ለማከናወን የሚያስፈልጋቸውን ሥልጠና እንዲያገኙ በቋሚነት ከእሱ ጋር መሆን አለባቸው።

ኢየሱስ በባሕሩ ዳርቻ እየሄደ ሳለ ስምዖን ጴጥሮስና ወንድሙ እንድርያስ ከጓደኞቻቸው ጋር ሆነው መረባቸውን ሲጠግኑ አየ። ኢየሱስ ወደ እነሱ ሄደና የጴጥሮስ ጀልባ ላይ በመውጣት ጀልባዋን ከየብስ ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጋት ጠየቀው። ከመሬት ትንሽ ራቅ ሲሉ ኢየሱስ ጀልባዋ ላይ ተቀምጦ በባሕሩ ዳርቻ ለተሰበሰበው ሕዝብ የመንግሥቱን እውነቶች ማስተማር ጀመረ።

በኋላ ላይ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስን “ጥልቅ ወደሆነው አካባቢ ፈቀቅ በልና መረቦቻችሁን ጥላችሁ አጥምዱ” አለው። ጴጥሮስም መልሶ “መምህር፣ ሌሊቱን ሙሉ ስንደክም አድረን ምንም አልያዝንም፤ አንተ ካልክ ግን መረቦቹን እጥላለሁ” አለው።—ሉቃስ 5:4, 5

መረቦቹን ሲጥሉ እጅግ ብዙ ዓሣ ስለያዙ መረቦቻቸው መበጣጠስ ጀመሩ! ወዲያውኑ፣ በአቅራቢያቸው በነበረች ጀልባ ላይ ያሉ የሥራ ባልደረቦቻቸውን መጥተው እንዲያግዟቸው በምልክት ጠሯቸው። ብዙም ሳይቆይ ሁለቱም ጀልባዎች በዓሣ ስለተሞሉ መስጠም ጀመሩ። ጴጥሮስ ይህን ሲመለከት ኢየሱስ ፊት ተንበርክኮ “ጌታ ሆይ፣ እኔ ኃጢአተኛ ስለሆንኩ ከእኔ ራቅ” አለው። ኢየሱስም “አይዞህ አትፍራ፤ ከአሁን ጀምሮ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ” በማለት መለሰለት።—ሉቃስ 5:8, 10

ኢየሱስ ጴጥሮስንና እንድርያስን “ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰው አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው። (ማቴዎስ 4:19) ለሌሎች ሁለት ዓሣ አጥማጆች ይኸውም የዘብዴዎስ ልጆች ለሆኑት ለያዕቆብና ለዮሐንስም ይህንኑ ጥሪ አቀረበላቸው። እነሱም ምንም ሳያመነቱ ጥሪውን ተቀበሉ። እነዚህ አራት ሰዎች፣ ዓሣ የማጥመድ ሥራቸውን በመተው የኢየሱስ የሙሉ ጊዜ ተከታዮች የሆኑ የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ናቸው።