በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 24

በገሊላ በስፋት ሰበከ

በገሊላ በስፋት ሰበከ

ማቴዎስ 4:23-25 ማርቆስ 1:35-39 ሉቃስ 4:42, 43

  • ኢየሱስ ከአራት ደቀ መዛሙርቱ ጋር ገሊላን ዞረ

  • ስብከቱም ሆነ ያከናወናቸው ሥራዎች በስፋት ታወቁ

ኢየሱስ በቅፍርናሆም ከአራት ደቀ መዛሙርቱ ጋር የዋለው በሥራ ተወጥሮ ነው። አመሻሹ ላይ የቅፍርናሆም ሰዎች የታመሙ ሰዎችን እንዲፈውስ አመጡለት። ኢየሱስ ብቻውን ለመሆን ጊዜ አላገኘም።

በሚቀጥለው ቀን ገና ጎህ ሳይቀድ ኢየሱስ ብቻውን ወደ ውጭ ወጣ። ወደ አባቱ ለመጸለይ ጭር ወዳለ አካባቢ ሄደ። ሆኖም በዚህ ሁኔታ ብዙም አልቆየም። “ስምዖንና ከእሱ ጋር የነበሩት” ኢየሱስን ሲያጡት እሱን ፍለጋ ወጡ። ኢየሱስ ያረፈው ጴጥሮስ ቤት በመሆኑ እሱን ለመፈለግ ጴጥሮስ ቅድሚያውን ወስዶ ሊሆን ይችላል።—ማርቆስ 1:36፤ ሉቃስ 4:38

ኢየሱስን ሲያገኙት ጴጥሮስ “ሰው ሁሉ እየፈለገህ ነው” አለው። (ማርቆስ 1:37) የቅፍርናሆም ሰዎች ኢየሱስ እነሱ ጋ እንዲቆይ ቢፈልጉ የሚያስገርም አይደለም። ያደረገላቸውን ነገር ከልብ ስላደነቁ ‘እንዳይሄድባቸው ለመኑት።’ (ሉቃስ 4:42) ይሁንና ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት ዋነኛ ዓላማ እንዲህ ዓይነት ተአምራዊ ፈውስ መፈጸም ነው? ደግሞስ ሥራውን ማከናወን ያለበት እዚህ አካባቢ ብቻ ነው? እሱ ስለዚህ ጉዳይ ምን አለ?

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በዚያም እንድሰብክ በአቅራቢያ ወዳሉት ከተሞች እንሂድ፤ የመጣሁት ለዚሁ ነውና።” ኢየሱስ አብሯቸው እንዲቆይ ለጠየቁት ሰዎች ደግሞ “ለሌሎች ከተሞችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው” አላቸው።—ማርቆስ 1:38፤ ሉቃስ 4:43

አዎ፣ ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት ትልቁ ዓላማ ስለ አምላክ መንግሥት ለመስበክ ነው። ይህ መንግሥት የአባቱን ስም የሚያስቀድስ ከመሆኑም ሌላ የሰው ልጆችን ችግሮች ለዘለቄታው ያስወግዳል። ኢየሱስ ተአምራዊ ፈውስ ማከናወኑ በአምላክ የተላከ መሆኑን ያረጋግጣል። ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መልኩ ከበርካታ ዘመናት በፊት ሙሴም ከአምላክ የተላከ ለመሆኑ ማስረጃ እንዲሆን ሲል አስደናቂ ነገሮችን አድርጓል።—ዘፀአት 4:1-9, 30, 31

ኢየሱስ በሌሎች ከተሞች ለመስበክ ቅፍርናሆምን ለቆ ሲወጣ አራቱ ደቀ መዛሙርቱም አብረውት ተጓዙ። አራቱ ደቀ መዛሙርት፣ ጴጥሮስና ወንድሙ እንድርያስ እንዲሁም ዮሐንስና ወንድሙ ያዕቆብ ናቸው። ኢየሱስ ከእሱ ጋር እየተጓዙ የሚያገለግሉ የመጀመሪያዎቹ የሥራ ባልደረቦቹ እንዲሆኑ ከአንድ ሳምንት በፊት ጥሪ አቅርቦላቸው ነበር።

ኢየሱስ ከእነዚህ አራት ደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆኖ በገሊላ እየተዘዋወረ ያከናወነው ስብከት እጅግ የተሳካ ነበር! እንዲያውም ስላከናወናቸው ነገሮች በሰፊው ተወራ። “ስለ እሱም የተወራው ወሬ በመላዋ ሶርያ” እንዲሁም ዲካፖሊስ ተብሎ በሚጠራው አሥሩ ከተሞች የሚገኙበት ክልል እና ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ ባሉት አካባቢዎች ሁሉ ተዳረሰ። (ማቴዎስ 4:24, 25) ከእነዚህ አካባቢዎች እንዲሁም ከይሁዳ የመጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ኢየሱስንና ደቀ መዛሙርቱን ተከተሏቸው። ብዙዎች የታመሙ ሰዎችን ወደ እሱ አመጡ። ኢየሱስም ቢሆን አላሳፈራቸውም፤ የታመሙትን ፈወሰ፣ ጋኔን የያዛቸውን ሰዎችም ርኩስ መንፈሱን አስወጣላቸው።