በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 25

በሥጋ ደዌ የተያዘን ሰው በርኅራኄ ፈወሰ

በሥጋ ደዌ የተያዘን ሰው በርኅራኄ ፈወሰ

ማቴዎስ 8:1-4 ማርቆስ 1:40-45 ሉቃስ 5:12-16

  • ኢየሱስ የሥጋ ደዌ ያለበትን ሰው ፈወሰ

ኢየሱስና አራቱ ደቀ መዛሙርቱ ‘በመላዋ ገሊላ በምኩራቦች’ ሲሰብኩ ኢየሱስ ስለፈጸማቸው አስደናቂ ነገሮች የሚገልጸው ወሬ በስፋት ተሰራጨ። (ማርቆስ 1:39) ወሬው በሥጋ ደዌ የተያዘ አንድ ሰው ወደሚኖርባት ከተማ ደረሰ። ሐኪሙ ሉቃስ፣ ይህ ሰው “መላ ሰውነቱን የሥጋ ደዌ” እንደወረሰው ገልጿል። (ሉቃስ 5:12) ይህ አሠቃቂ በሽታ እየተባባሰ ሲሄድ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን መልክ ቀስ በቀስ ያበላሻል።

የሥጋ ደዌ የያዘው ይህ ሰው በሚያሳዝን ሁኔታ ውስጥ ከመሆኑም ሌላ ከሌሎች ተገልሎ እንዲኖር ይጠበቅበታል። በተጨማሪም ሰዎች በአካባቢው ካሉ ወደ እሱ በጣም ቀርበው በበሽታው እንዳይያዙ ለመከላከል ሲል “ርኩስ ነኝ፣ ርኩስ ነኝ!” እያለ መጮኽ አለበት። (ዘሌዋውያን 13:45, 46) ይህ ሰው ግን ምን አደረገ? ወደ ኢየሱስ ቀርቦ በፊቱ በመንበርከክ “ጌታ ሆይ፣ ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” ሲል ለመነው።—ማቴዎስ 8:2

በኢየሱስ ላይ ያለው እምነት እንዴት ጠንካራ ነው! ሰውየው፣ በሽታው ምን ያህል እንደጎዳው ሲታይ በጣም ያሳዝናል። ታዲያ ኢየሱስ ምን ያደርግ ይሆን? አንተ በዚያ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር? ኢየሱስ በርኅራኄ ስሜት በመገፋፋት እጁን ዘርግቶ ሰውየውን ዳሰሰው። ከዚያም “እፈልጋለሁ! ንጻ” አለው። (ማቴዎስ 8:3) ለአንዳንዶች ይህን ማመን የሚከብድ ቢሆንም እንኳ ሰውየው ከበሽታው ወዲያውኑ ነጻ።

እንደ ኢየሱስ ሩኅሩኅ እንዲሁም አስደናቂ ነገሮችን ማድረግ የሚችል ንጉሥ ቢኖርህ ደስ አይልህም? ኢየሱስ፣ የሥጋ ደዌ በሽተኛ የሆነውን ሰው የያዘበት መንገድ፣ በመላው ምድር ላይ በሚነግሥበት ወቅት “ለችግረኛውና ለድሃው ያዝናል፤ የድሆችንም ሕይወት ያድናል” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደሚፈጸም እርግጠኛ እንድንሆን ያደርገናል። (መዝሙር 72:13) አዎን፣ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መከራ የደረሰባቸውን ሰዎች ሁሉ ለመርዳት ያለውን ልባዊ ፍላጎት ያሳካል።

ኢየሱስ ይህን ሰው ከመፈወሱ በፊትም እንኳ ባከናወነው አገልግሎት ሕዝቡ በጣም ተደንቆ እንደነበር ታስታውስ ይሆናል። አሁን ደግሞ ሰዎች፣ ኢየሱስ የፈጸመውን ይህን አስደናቂ ነገር ሊሰሙ ነው። ኢየሱስ ግን ሰዎች ከሰሙት ነገር ብቻ ተነስተው በእሱ እንዲያምኑ አልፈለገም። ወደ ራሱ ትኩረት በሚስብ መንገድ ‘ድምፁን በጎዳና ላይ እንደማያሰማ’ የሚገልጸውን ስለ እሱ የተነገረ ትንቢት ያውቃል። (ኢሳይያስ 42:1, 2) በመሆኑም ኢየሱስ ከሥጋ ደዌ በሽታ የተፈወሰውን ሰው “ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ሙሴ ያዘዘውንም መባ አቅርብ” አለው።—ማቴዎስ 8:4

ሰውየው ግን በመፈወሱ በጣም ስለተደሰተ የተደረገለትን ተአምር ሊደብቅ አልቻለም። ሰውየው የሆነውን ነገር በሰፊው አወራ። ይህም ሕዝቡ ስለ ኢየሱስ ይበልጥ የማወቅ ጉጉት እንዲያድርባቸው አደረገ። ወሬው በየቦታው ከመሰራጨቱ የተነሳ ኢየሱስ በግልጽ ወደ ከተማ መግባት አልቻለም፤ በመሆኑም ከከተማ ውጭ ማንም በማይኖርባቸው ቦታዎች ለተወሰነ ጊዜ ቆየ። ያም ቢሆን ሰዎች እንዲያስተምራቸውና እንዲፈውሳቸው ከተለያዩ ቦታዎች ወደ እሱ መምጣታቸውን አላቆሙም።