በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 37

ኢየሱስ የአንዲት መበለትን ልጅ ከሞት አስነሳ

ኢየሱስ የአንዲት መበለትን ልጅ ከሞት አስነሳ

ሉቃስ 7:11-17

  • በናይን የተፈጸመ ትንሣኤ

ኢየሱስ የጦር መኮንኑን አገልጋይ ከፈወሰ ብዙም ሳይቆይ ከቅፍርናሆም በስተ ደቡብ ምዕራብ ከ30 ኪሎ ሜትር በሚበልጥ ርቀት ላይ ወደምትገኘው ወደ ናይን ከተማ ሄደ። ኢየሱስ ብቻውን አይደለም። ደቀ መዛሙርቱና ሌሎች ብዙ ሰዎች አብረውት እየተጓዙ ነው። ወደ ናይን ከተማ ዳርቻ የደረሱት አመሻሹ ላይ ሳይሆን አይቀርም። እዚያም የቀብር ሥነ ሥርዓት ለመፈጸም የሚጓዙ በርካታ አይሁዳውያንን አገኙ። ሰዎቹ የአንድን ወጣት አስከሬን ተሸክመው ለመቅበር ከከተማዋ እየወጡ ነው።

ከሁሉ ይበልጥ በሐዘን የተደቆሰችው የልጁ እናት ነች። ይህች ሴት ባሏ የሞተባት ሲሆን አሁን ደግሞ አንድ ልጇን አጣች። ባሏ ሲሞት፣ የምትወደው ልጇ ስላለ በእሱ ትጽናና ነበር። ተስፋዋ እንዲሁም ለወደፊቱ ጊዜ መተማመኛዋ እሱ በመሆኑ ምን ያህል ትቀርበው እንደነበር መገመት ይቻላል። አሁን ግን እሱም ሞተ። ከዚህ በኋላ ከጎኗ የሚሆንና የሚደግፋት ማን አላት?

ኢየሱስ ሴትየዋን ሲያያት፣ የደረሰባት ጥልቅ ሐዘንና ያለችበት አሳዛኝ ሁኔታ ልቡን ነካው። ስለዚህ ርኅራኄ በተሞላበትና እምነት በሚያሳድር መንገድ “በቃ፣ አታልቅሺ” አላት። ይሁንና በዚህ አላበቃም። ቀረብ ብሎ አስከሬኑን የተሸከሙበትን ቃሬዛ ነካው። (ሉቃስ 7:13, 14) የኢየሱስ ሁኔታና ድርጊቱ የሐዘንተኞቹን ቀልብ ስለሳበው ባሉበት ቆሙ። ብዙዎች ‘ምን ማለቱ ነው? ደግሞስ ምን ሊያደርግ ነው?’ ብለው አስበው ይሆናል።

ከኢየሱስ ጋር የሚጓዙትና የተለያዩ በሽታዎችን በመፈወስ ተአምር ሲፈጽም ተመልክተው የሚያውቁት ሰዎችስ ምን ተሰምቷቸው ይሆን? ኢየሱስ የሞተን ሰው ሲያስነሳ አይተው የሚያውቁ አይመስልም። በእርግጥ ቀደም ባሉት ዘመናት ትንሣኤ ተከናውኗል፤ ሆኖም ኢየሱስ የሞተ ሰው ማስነሳት ይችል ይሆን? (1 ነገሥት 17:17-23፤ 2 ነገሥት 4:32-37) ኢየሱስ “አንተ ወጣት፣ ተነስ እልሃለሁ!” አለ። (ሉቃስ 7:14) እንዳለውም ሆነ። ወጣቱ ቀና ብሎ ተቀመጠና መናገር ጀመረ! ኢየሱስም ልጁን ለእናቱ ሰጣት፤ እናትየው በሁኔታው ብትደነግጥም በደስታ እንደተሞላች ጥርጥር የለውም። ከዚህ በኋላ ብቸኛ አይደለችም።

ሰዎቹ፣ ወጣቱ ሕያው መሆኑን ሲመለከቱ “ታላቅ ነቢይ በመካከላችን ተነስቷል” በማለት ሕይወት ሰጪ የሆነውን ይሖዋ አምላክን አወደሱ። ሌሎችም ኢየሱስ የፈጸመው ተአምር ምን ትርጉም እንዳለው ስለተገነዘቡ “አምላክ ሕዝቡን አሰበ” በማለት ተናገሩ። (ሉቃስ 7:16) ስለዚህ ተአምራዊ ድርጊት የሚገልጸው ወሬ በአካባቢው ባሉ ከተሞች ሁሉ በፍጥነት ተሰራጨ፤ ዜናው ኢየሱስ ወዳደገባትና 10 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ወደምትገኘው ናዝሬት ሳይደርስ አይቀርም። በስተ ደቡብም እስከ ይሁዳ ድረስ እንኳ ተሰማ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ መጥምቁ ዮሐንስ አሁንም እንደታሰረ ነው፤ ኢየሱስ የፈጸማቸውን ነገሮች ለማወቅ ጓጉቷል። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ስለ እነዚህ ተአምራት ነገሩት። ታዲያ ምን ምላሽ ይሰጥ ይሆን?