በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 43

ስለ መንግሥቱ የተነገሩ ምሳሌዎች

ስለ መንግሥቱ የተነገሩ ምሳሌዎች

ማቴዎስ 13:1-53 ማርቆስ 4:1-34 ሉቃስ 8:4-18

  • ኢየሱስ ስለ መንግሥቱ ምሳሌዎች ተናገረ

ኢየሱስ ፈሪሳውያንን ያወገዘው በቅፍርናሆም ሳይሆን አይቀርም። በዚያው ቀን ወደ በኋላ ላይ ከቤት ወጣና በአቅራቢያው ወደሚገኘው የገሊላ ባሕር ሄደ፤ በዚያ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። ኢየሱስ ጀልባ ላይ ወጥቶ ከተቀመጠ በኋላ ከባሕሩ ዳርቻ ፈቀቅ አለ፤ ከዚያም ሕዝቡን ስለ መንግሥተ ሰማያት ማስተማር ጀመረ። ያስተማራቸው በርካታ ምሳሌዎችን በመጠቀም ነው። አድማጮቹ ኢየሱስ የጠቀሳቸውን አብዛኞቹን ክንውኖች ወይም ሁኔታዎች ስለሚያውቋቸው የመንግሥቱን የተለያዩ ገጽታዎች መረዳት ቀላል ሆኖላቸዋል።

በመጀመሪያ ኢየሱስ ዘር ስለዘራ ሰው ነገራቸው። አንዳንዶቹ ዘሮች በመንገድ ዳር ወደቁና ወፎች ለቀሟቸው። ሌሎቹ ዘሮች ደግሞ ብዙ አፈር በሌለው ድንጋያማ መሬት ላይ ወደቁ። ዘሩ ሲበቅል ሥር መስደድ አልቻለም፤ በመሆኑም ያቆጠቆጠው ተክል ፀሐይ በወጣ ጊዜ ደረቀ። ሌሎቹ ዘሮች በእሾህ መካከል የወደቁ ሲሆን ብቅ ማለት ሲጀምሩ እሾሁ አነቃቸው። አንዳንዶቹ ዘሮች ግን ጥሩ አፈር ላይ ወደቁ። እነዚህ ዘሮች “ፍሬ ማፍራት ጀመሩ፤ አንዱ 100፣ አንዱ 60፣ ሌላውም 30 እጥፍ አፈራ።”—ማቴዎስ 13:8

በሌላ ምሳሌ ደግሞ ኢየሱስ መንግሥቱን፣ አንድ ሰው ዘር ሲዘራ ከሚኖረው ሁኔታ ጋር አመሳሰለው። በዚህ ምሳሌ ላይ ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ማለዳም ይነሳል፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ዘሩን አድጎ ያገኘዋል። ዘሩ ያደገው ‘እንዴት እንደሆነ አያውቅም።’ (ማርቆስ 4:27) ዘሩ በራሱ አድጎ ፍሬ ያፈራል፤ ሰብሉ ሲደርስ ሰውየው ይሰበስበዋል።

ኢየሱስ የተናገረው ሦስተኛውም ምሳሌ ዘር ስለ መዝራት ነው። አንድ ሰው ጥሩ ዘር ዘራ፤ ሆኖም “ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ” ጠላት መጣና በስንዴው ላይ እንክርዳድ ዘራበት። የሰውየው ባሪያዎች እንክርዳዱን ለመንቀል ጥያቄ አቀረቡ። ሰውየው እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እንክርዳዱን ስትነቅሉ ስንዴውንም አብራችሁ ልትነቅሉ ስለምትችሉ ተዉት። እስከ መከር ጊዜ ድረስ አብረው ይደጉ፤ በመከር ወቅት አጫጆቹን፣ በመጀመሪያ እንክርዳዱን ሰብስቡና እንዲቃጠል በየነዶው እሰሩ፤ ከዚያም ስንዴውን ሰብስባችሁ ወደ ጎተራዬ አስገቡ እላቸዋለሁ።”—ማቴዎስ 13:24-30

ኢየሱስን ከሚያዳምጡት ሰዎች አብዛኞቹ ስለ ግብርና ያውቃሉ። ኢየሱስ ሰዎቹ በደንብ የሚያውቁትን ሌላ ነገር ይኸውም በጣም ትንሽ የሆነችውን የሰናፍጭ ዘር ጠቀሰ። የሰናፍጭ ዘር አድጋ በጣም ትልቅ ዛፍ ስለምትሆን ወፎች በቅርንጫፎቹ ላይ መስፈሪያ ያገኛሉ። ኢየሱስ ይህን ዘር በተመለከተ “መንግሥተ ሰማያት አንድ ሰው ወስዶ እርሻው ውስጥ ከተከላት አንዲት የሰናፍጭ ዘር ጋር ይመሳሰላል” ብሏል። (ማቴዎስ 13:31) ኢየሱስ ይህን ሲል ስለ ተክሎች ትምህርት እየሰጠ አልነበረም። አስደናቂ ስለሆነ እድገት ይኸውም በጣም ትንሽ የሆነ ነገር አድጎ ወይም ተስፋፍቶ በጣም ትልቅ ሊሆን እንደሚችል በምሳሌ ማስረዳቱ ነው።

ቀጥሎም ኢየሱስ ከአድማጮቹ ብዙዎቹ የሚያውቁትን አንድ ሂደት ጠቀሰ። መንግሥተ ሰማያትን “አንዲት ሴት ወስዳ ሊጡ በሙሉ እስኪቦካ ድረስ ከሦስት ትላልቅ መስፈሪያ ዱቄት ጋር ከደባለቀችው እርሾ” ጋር አመሳሰለው። (ማቴዎስ 13:33) እርሾው በዓይን ባይታይም እንኳ ሊጡን በሙሉ ስለሚያዳርሰውና ስለሚያቦካው ኩፍ እንዲል ያደርገዋል። እርሾው፣ በቀላሉ የማይታይ ከፍተኛ እድገትና ለውጥ እንዲኖር ያደርጋል።

ኢየሱስ እነዚህን ምሳሌዎች ከተናገረ በኋላ የተሰበሰቡትን ሰዎች አሰናብቶ ወዳረፈበት ቤት ተመለሰ። ብዙም ሳይቆይ ደቀ መዛሙርቱ የምሳሌዎቹን ትርጉም እንዲያብራራላቸው ስለፈለጉ ወደ እሱ መጡ።

ከኢየሱስ ምሳሌዎች ጥቅም ማግኘት

ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ በምሳሌዎች ሲጠቀም ሰምተው ያውቃሉ፤ ሆኖም እንደዚህ ብዙ ምሳሌዎችን የተናገረበት ጊዜ የለም። በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱ “በምሳሌ የምትነግራቸው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።—ማቴዎስ 13:10

ይህን የሚያደርግበት አንዱ ምክንያት የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት ለመፈጸም ነው። የማቴዎስ ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “ያለ ምሳሌ አይነግራቸውም ነበር፤ ይህም የሆነው ‘አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ከምሥረታው ጊዜ አንስቶ የተሰወሩትን ነገሮች አውጃለሁ’ ተብሎ በነቢዩ የተነገረው እንዲፈጸም ነው።”—ማቴዎስ 13:34, 35፤ መዝሙር 78:2

ይሁን እንጂ ኢየሱስ በምሳሌ የሚጠቀምበት ሌላም ምክንያት አለው። በምሳሌዎች መጠቀሙ የሰዎች የልብ ዝንባሌ ገሃድ እንዲወጣ ያደርጋል። አብዛኞቹ ሰዎች ወደ ኢየሱስ የተሳቡት የተዋጣለት ተራኪና ተአምር ሠሪ በመሆኑ ብቻ ነው። ሰዎች ሊታዘዙት የሚገባ ጌታ እንደሆነና ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ሊከተሉት እንደሚገባ አድርገው አልተመለከቱትም። (ሉቃስ 6:46, 47) ለነገሮች ያላቸውን አመለካከትም ሆነ አኗኗራቸውን ለመለወጥ አይፈልጉም። መልእክቱ ወደ ልባቸው ያን ያህል ጠልቆ እንዲገባ አልፈለጉም።

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ላነሱት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ እንዲህ አለ፦ “በምሳሌ የምነግራቸው ለዚህ ነው፤ ቢያዩም የሚያዩት እንዲያው በከንቱ ነውና፤ ቢሰሙም የሚሰሙት እንዲያው በከንቱ ነው፤ ትርጉሙንም አያስተውሉም። ደግሞም የኢሳይያስ ትንቢት በእነሱ ላይ እየተፈጸመ ነው። ትንቢቱ እንዲህ ይላል፦ ‘. . . የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኗል።’”—ማቴዎስ 13:13-15፤ ኢሳይያስ 6:9, 10

ይሁንና ይህ ሐሳብ የሚሠራው በሁሉም አድማጮቹ ላይ አይደለም። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ፣ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ ደስተኞች ናችሁ። እውነት እላችኋለሁ፣ ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ አሁን የምታዩትን ነገር ለማየት ተመኝተው ነበር፤ ግን አላዩም፤ አሁን የምትሰሙትን ነገር ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ግን አልሰሙም።”—ማቴዎስ 13:16, 17

አዎን፣ 12ቱ ሐዋርያትና ሌሎች ታማኝ ተከታዮቹ ተቀባይ ልብ ነበራቸው። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ቅዱስ ሚስጥሮች የመረዳት ችሎታ ተሰጥቷችኋል፤ ለእነሱ ግን አልተሰጣቸውም” ሲል ተናገረ። (ማቴዎስ 13:11) ደቀ መዛሙርቱ የኢየሱስን ትምህርት የመረዳት ልባዊ ፍላጎት ስላላቸው ኢየሱስ የዘሪውን ምሳሌ አብራራላቸው።

ኢየሱስ “ዘሩ የአምላክ ቃል ነው” አለ። (ሉቃስ 8:11) አፈሩ ደግሞ ልብ ነው። የምሳሌውን ትርጉም ለመረዳት ይህን ማወቅ ቁልፍ ነው።

በመንገድ ዳር ወድቆ በተረጋገጠው ዘር ስለተመሰሉት ሰዎች ሲያብራራ “አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል” አለ። (ሉቃስ 8:12) ኢየሱስ በድንጋያማ መሬት ላይ ስለተዘራው ዘር ሲናገር፣ ቃሉን በደስታ ቢቀበሉም ቃሉ በልባቸው ሥር ስላልሰደደ ሰዎች መግለጹ ነው። ‘በቃሉ የተነሳ መከራ ወይም ስደት ሲደርስባቸው ይሰናከላሉ።’ “በፈተና ወቅት” ማለትም ከቤተሰባቸው ወይም ከሌሎች ተቃውሞ ሲያጋጥማቸው ይወድቃሉ።—ማቴዎስ 13:21፤ ሉቃስ 8:13

ኢየሱስ በእሾህ መካከል ስለወደቀው ዘርስ ምን አለ? ይህ ዘር ቃሉን የሰሙ ሰዎችን እንደሚያመለክት ለደቀ መዛሙርቱ ገለጸ። እነዚህ ሰዎች ቃሉን ቢሰሙም “የዚህ ሥርዓት ጭንቀት እንዲሁም ሀብት ያለው የማታለል ኃይል” ያሸንፋቸዋል። (ማቴዎስ 13:22) ቃሉ ወደ ልባቸው ቢገባም ስለሚታነቅ ፍሬ የማያፈራ ይሆናል።

በመጨረሻም ኢየሱስ ስለ ጥሩው አፈር አብራራ። ይህ አፈር፣ ቃሉን ሰምተው በልባቸው የሚያሳድሩትን ይኸውም ቃሉን የሚገነዘቡትን ሰዎች ያመለክታል። ምን ውጤት ይገኛል? “ፍሬ የሚያፈሩ” ይሆናሉ። ያሉበት ሁኔታ ለምሳሌ ዕድሜያቸው ወይም ጤንነታቸው የተለያየ ስለሚሆን ሁሉም እኩል አያፈሩም፤ አንዱ 100፣ አንዱም 60፣ ሌላውም 30 እጥፍ ያፈራል። በእርግጥም “ቃሉን በመልካምና በጥሩ ልብ ሰምተው በውስጣቸው በማኖር በጽናት ፍሬ የሚያፈሩ” ሰዎች አምላክን በማገልገላቸው ይባረካሉ።—ሉቃስ 8:15

ስለ ኢየሱስ ትምህርቶች ማብራሪያ ለማግኘት ሲሉ ወደ እሱ የሄዱት ደቀ መዛሙርቱ ይህ ሐሳብ ትኩረታቸውን እንደሚስበው ጥርጥር የለውም! አሁን የምሳሌዎቹን ትርጉም በጥልቀት መረዳት ችለዋል። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ምሳሌዎቹን ተረድተው እነሱም በተራቸው እውነትን ለሌሎች ማስተማር እንዲችሉ ይፈልጋል። በመሆኑም “መብራት አምጥቶ እንቅብ የሚደፋበት ወይም አልጋ ሥር የሚያስቀምጠው ይኖራል? የሚቀመጠው በመቅረዝ ላይ አይደለም?” ሲል ጠየቀ። ከዚያም “የሚሰማ ጆሮ ያለው ሁሉ ይስማ” የሚል ምክር ሰጠ።—ማርቆስ 4:21-23

ተጨማሪ ትምህርት በማግኘት ተባርከዋል

ደቀ መዛሙርቱ፣ ኢየሱስ ስለ ዘሪው ምሳሌ የሰጠውን ማብራሪያ ካዳመጡ በኋላ ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት ፈለጉ። በመሆኑም “በእርሻው ውስጥ ስላለው እንክርዳድ የተናገርከውን ምሳሌ አብራራልን” ብለው ጠየቁት።—ማቴዎስ 13:36

ደቀ መዛሙርቱ ይህን ጥያቄ በማቅረባቸው በባሕሩ ዳርቻ ከተሰበሰበው ሕዝብ በጣም የተለየ አመለካከት እንዳላቸው አሳይተዋል። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ሕዝቡ ምሳሌዎቹን ቢሰሙም ትርጉማቸውንና ከዚያ የሚገኘውን ትምህርት የማወቅ ፍላጎት የላቸውም። በምሳሌው ላይ የተጠቀሱትን ነገሮች በጥቅሉ ስለሚያውቋቸው ብቻ ረክተዋል። ኢየሱስ በባሕሩ አጠገብ ሆነው ያዳመጡትን ሰዎች እና የማወቅ ጉጉት ስላላቸው ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ወደ እሱ የመጡትን ደቀ መዛሙርቱን በማወዳደር እንዲህ አለ፦

“የምትሰሙትን ነገር ልብ በሉ። በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል፤ እንዲያውም ከዚያ የበለጠ ይጨመርላችኋል።” (ማርቆስ 4:24) ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሱስ የሚሰሙትን ነገር ልብ ይላሉ። እንዲህ በማድረጋቸውም እውቀት የማግኘት ልባዊ ፍላጎት ያሳዩ ከመሆኑም ሌላ ለኢየሱስ ትኩረት ሰጥተውታል፤ ኢየሱስ እንዳለው በዚህ መንገድ በመስፈራቸው ተጨማሪ ትምህርት በማግኘት ተባርከዋል። ስለዚህ ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ የስንዴውንና የእንክርዳዱን ምሳሌ ትርጉም እንዲነግራቸው ላቀረቡት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ እንዲህ አለ፦

“ጥሩውን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻው ዓለም ነው። ጥሩው ዘር ደግሞ የመንግሥቱ ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱ ግን የክፉው ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱን የዘራው ጠላት፣ ዲያብሎስ ነው። መከሩ የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ሲሆን አጫጆቹ ደግሞ መላእክት ናቸው።”—ማቴዎስ 13:37-39

ኢየሱስ እያንዳንዱን የምሳሌውን ገጽታ ለይቶ ከገለጸ በኋላ ምሳሌውን አብራራ። በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ላይ አጫጆቹ ወይም መላእክት፣ እንክርዳድ የተባሉትን አስመሳይ ክርስቲያኖች ከእውነተኛዎቹ “የመንግሥቱ ልጆች” ይለያሉ። “ጻድቃን” የሚሰበሰቡ ሲሆን ውሎ አድሮም “በአባታቸው መንግሥት . . . ደምቀው ያበራሉ።” ‘የክፉው ልጆችስ’ ምን ይሆናሉ? ዕጣቸው ጥፋት ስለሚሆን “በዚያም ያለቅሳሉ፤ ጥርሳቸውንም ያፋጫሉ” መባሉ የሚያስገርም አይደለም።—ማቴዎስ 13:41-43

ኢየሱስ በመቀጠል ለደቀ መዛሙርቱ ሦስት ተጨማሪ ምሳሌዎችን ነገራቸው። በመጀመሪያ እንዲህ አለ፦ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻ ውስጥ ከተደበቀ ውድ ሀብት ጋር ይመሳሰላል፤ አንድ ሰው ባገኘው ጊዜ ሸሸገው፤ ከመደሰቱም የተነሳ ሄዶ ያለውን ሁሉ በመሸጥ እርሻውን ገዛው።”—ማቴዎስ 13:44

ቀጥሎም እንዲህ አለ፦ “መንግሥተ ሰማያት ጥሩ ዕንቁ ከሚፈልግ ተጓዥ ነጋዴ ጋር ይመሳሰላል። ከፍተኛ ዋጋ ያለው አንድ ዕንቁ ባገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ወዲያውኑ በመሸጥ ዕንቁውን ገዛው።”—ማቴዎስ 13:45, 46

በሁለቱም ምሳሌዎች ላይ ኢየሱስ ያጎላው በጣም ውድ ዋጋ ያለውን ነገር ለማግኘት ሲባል መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ መሆንን ነው። ነጋዴው፣ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ዕንቁ ለመግዛት ሲል “ያለውን ሁሉ” ወዲያውኑ ሸጧል። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ውድ ስለሆነው ዕንቁ የተሰጠውን ምሳሌ መረዳት ይችላሉ። በእርሻ ውስጥ የተደበቀ ውድ ሀብት ያገኘው ሰውም ይህን ሀብት እጁ ለማስገባት ሲል ‘ያለውን ሁሉ ሸጧል።’ ሁለቱም ሰዎች ውድ ዋጋ ያለው ነገር ይኸውም የራሳቸው ሊያደርጉትና ትልቅ ቦታ ሊሰጡት የሚገባ ነገር አግኝተዋል። የወሰዱት እርምጃ አንድ ሰው መንፈሳዊ ጥማቱን ለማርካት ሲል ከሚከፍለው መሥዋዕት ጋር ሊነጻጸር ይችላል። (ማቴዎስ 5:3) ኢየሱስ እነዚህን ምሳሌዎች ሲናገር ከሰሙት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ፣ መንፈሳዊ ጥማታቸውን ለማርካትና የእሱ እውነተኛ ተከታዮች ለመሆን ሲሉ ከፍተኛ መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ መሆናቸውን አሳይተዋል።—ማቴዎስ 4:19, 20፤ 19:27

በመጨረሻም ኢየሱስ መንግሥተ ሰማያት፣ የተለያየ ዓይነት ዓሣ ከሰበሰበ መረብ ጋር እንደሚመሳሰል ገልጿል። (ማቴዎስ 13:47) ዓሣዎቹ ሲለዩ ጥሩ ጥሩው በዕቃ ውስጥ ተቀመጠ፤ መጥፎ መጥፎው ግን ተጣለ። ኢየሱስ በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ላይም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ እንደሚኖር ይኸውም መላእክት ክፉዎችን ከጻድቃን እንደሚለዩ ተናገረ።

ኢየሱስ የመጀመሪያ ደቀ መዛሙርቱን “ሰው አጥማጆች” እንዲሆኑ በጠራቸው ወቅት መንፈሳዊውን ዓሣ የማጥመድ ሥራ ጀምሯል። (ማርቆስ 1:17) ይሁንና ስለ መረቡ የተናገረው ምሳሌ ፍጻሜውን የሚያገኘው ወደፊት ይኸውም “በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” ላይ እንደሆነ ገልጿል። (ማቴዎስ 13:49) በመሆኑም ኢየሱስን እያዳመጡ ያሉት ሐዋርያትና ሌሎች ደቀ መዛሙርት፣ ወደፊት በጣም አስገራሚ ነገሮች እንደሚፈጸሙ ማስተዋል ይችላሉ።

ኢየሱስ ጀልባ ላይ ሆኖ ምሳሌዎችን ሲናገር የሰሙት ሰዎች ሌላም ጥቅም አግኝተዋል። ኢየሱስ ‘ብቻቸውን በሚሆኑበት ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ ሁሉንም ነገር ለማብራራት’ ፈቃደኛ መሆኑን አሳይቷል። (ማርቆስ 4:34) ኢየሱስ “ከከበረ ሀብት ማከማቻው አዲስና አሮጌ ዕቃ ከሚያወጣ የቤት ጌታ ጋር ይመሳሰላል።” (ማቴዎስ 13:52) እነዚህን ምሳሌዎች የተናገረው የማስተማር ችሎታውን ለማሳየት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በምንም እንደማይተመን ውድ ሀብት የሆኑ እውነቶችን ለደቀ መዛሙርቱ እያካፈላቸው ነው። በእርግጥም ተወዳዳሪ የሌለው “የሕዝብ አስተማሪ” ነው።