በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 47

አንዲት ልጅ ከሞት ተነሳች!

አንዲት ልጅ ከሞት ተነሳች!

ማቴዎስ 9:18, 23-26 ማርቆስ 5:22-24, 35-43 ሉቃስ 8:40-42, 49-56

  • ኢየሱስ የኢያኢሮስን ልጅ አስነሳት

ኢያኢሮስ፣ ደም ይፈስሳት የነበረችውን ሴት ኢየሱስ እንደፈወሳት ሲመለከት የእሱንም ልጅ ሊያድናት እንደሚችል ተሰምቶት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ይሁንና “እስካሁን ልጄ ሳትሞት አትቀርም” ብሎ አስቧል። (ማቴዎስ 9:18) ታዲያ ኢየሱስ ከዚህ በኋላ ሊረዳት ይችል ይሆን?

ኢየሱስ ከፈወሳት ሴት ጋር እየተነጋገረ ሳለ ከኢያኢሮስ ቤት የመጡ ሰዎች ኢያኢሮስን “ልጅህ ሞታለች! ከዚህ በኋላ መምህሩን ለምን ታስቸግረዋለህ?” አሉት።—ማርቆስ 5:35

ይህ እንዴት ያለ ከባድ መርዶ ነው! ኢያኢሮስ በማኅበረሰቡ ዘንድ በጣም የተከበረ ሰው ቢሆንም አሁን ግን ምንም ማድረግ አይችልም። አንዲት ልጁን በሞት አጥቷል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሲነጋገሩ ስለሰማቸው ወደ ኢያኢሮስ ዞረና “አትፍራ፤ ብቻ እመን” በማለት አበረታታው።—ማርቆስ 5:36

ከዚያም ኢየሱስ ከኢያኢሮስ ጋር በመሆን ወደ ቤቱ አመራ። በቦታው ሲደርሱ ከፍተኛ ትርምስ ተመለከቱ። በዚያ የተሰበሰቡት ሰዎች እያለቀሱ፣ ዋይ ዋይ እያሉና በሐዘን ደረታቸውን እየደቁ ነው። ኢየሱስ ወደ ውስጥ ሲገባ “ልጅቷ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” በማለት አስገራሚ ነገር ተናገረ። (ማርቆስ 5:39) ሰዎቹ ይህን ሲሰሙ ሳቁበት። ልጅቷ እንደሞተች ያውቃሉ። ይሁንና ሰዎችን ከከባድ እንቅልፍ የመቀስቀስ ያህል ኢየሱስ፣ አምላክ የሰጠውን ኃይል በመጠቀም የሞቱትን በቀላሉ ሊያስነሳ እንደሚችል ሊያሳያቸው ነው።

ኢየሱስ ከጴጥሮስ፣ ከያዕቆብ፣ ከዮሐንስና ከሞተችው ልጅ ወላጆች በስተቀር ሁሉንም ወደ ውጭ አስወጣ። ከአምስቱ ሰዎች ጋር ሆኖ ልጅቷ ወዳለችበት ገባ። ከዚያም “የልጅቷን እጅ ይዞ ‘ጣሊታ ቁሚ’ አላት፤ ትርጉሙም ‘አንቺ ልጅ፣ ተነሽ!’ ማለት ነው።” (ማርቆስ 5:41) ልጅቷም ወዲያው ተነስታ መራመድ ጀመረች። ኢያኢሮስና ባለቤቱ ይህን ሲያዩ ምን ያህል በደስታ እንደተዋጡ እስቲ አስበው! ኢየሱስ ለልጅቷ የምትበላው ነገር እንዲሰጧት መናገሩ ልጅቷ በእርግጥ ሕያው መሆኗን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።

ከዚህ ቀደም ኢየሱስ የፈወሳቸውን ሰዎች ስለ ጉዳዩ ለሌሎች እንዳያወሩ ያዝዛቸው ነበር፤ ለኢያኢሮስና ለባለቤቱም ተመሳሳይ መመሪያ ሰጣቸው። ያም ቢሆን እጅግ የተደሰቱት የልጅቷ ወላጆችና ሌሎች ሰዎች ወሬውን “በዚያ አገር ሁሉ በሰፊው” አዳረሱት። (ማቴዎስ 9:26) አንተስ የምትወደው ሰው ከሞት ሲነሳ ብትመለከት ይህን ለማውራት አትጓጓም? ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የምናገኘው ኢየሱስ የፈጸመው ሁለተኛው ትንሣኤ ነው።