በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 50

ስደት ቢኖርም ለመስበክ መዘጋጀት

ስደት ቢኖርም ለመስበክ መዘጋጀት

ማቴዎስ 10:16–11:1 ማርቆስ 6:12, 13 ሉቃስ 9:6

  • ኢየሱስ ሐዋርያቱን አሠልጥኖ ላካቸው

ሐዋርያቱ፣ ሁለት ሁለት ሆነው በስብከቱ ሥራ ሲካፈሉ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ኢየሱስ ግሩም ሥልጠና ሰጣቸው። ሆኖም ሥልጠናው በዚህ አላበቃም። ተቃዋሚዎች እንደሚያጋጥሟቸው በደግነት ሲያስጠነቅቃቸው እንዲህ አለ፦ “እነሆ፣ በተኩላዎች መካከል እንዳሉ በጎች እልካችኋለሁ፤ . . . ሰዎች ለፍርድ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ በምኩራቦቻቸውም ይገርፏችኋል፤ ስለዚህ ራሳችሁን ከእነሱ ጠብቁ። ደግሞም በእኔ ምክንያት በገዢዎችና በነገሥታት ፊት ያቀርቧችኋል።”—ማቴዎስ 10:16-18

በእርግጥም የኢየሱስ ተከታዮች ከባድ ስደት ሊደርስባቸው ይችላል፤ ያም ቢሆን የሚከተለውን የሚያረጋጋ ተስፋ ሰጣቸው፦ “አሳልፈው ሲሰጧችሁ እንዴት ወይም ምን ብለን እንመልሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ የምትናገሩት ነገር በዚያኑ ሰዓት ይሰጣችኋልና፤ በምትናገሩበት ጊዜ ብቻችሁን አይደላችሁም፤ ይልቁንም በእናንተ የሚናገረው የአባታችሁ መንፈስ ነው።” ኢየሱስ አክሎም እንዲህ አለ፦ “ወንድም ወንድሙን፣ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሳሉ፤ ደግሞም ያስገድሏቸዋል። በስሜ የተነሳም ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል፤ እስከ መጨረሻው የጸና ግን ይድናል።”—ማቴዎስ 10:19-22

የስብከቱ ሥራ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በመሆኑ ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ እስር ቤት ሳይገቡ ሥራውን ለማከናወን እንዲችሉ አስተዋይ መሆናቸው አስፈላጊ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ገለጸ። እንዲህ አላቸው፦ “በአንድ ከተማ ስደት ሲያደርሱባችሁ ወደ ሌላ ከተማ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁ፣ የሰው ልጅ እስከሚመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተሞችና መንደሮች ፈጽሞ አታዳርሱም።”—ማቴዎስ 10:23

ኢየሱስ ለ12 ሐዋርያቱ የሰጣቸው መመሪያ፣ ማስጠንቀቂያና ማበረታቻ ምንኛ ጠቃሚ ነው! ኢየሱስ ይህን ሐሳብ የተናገረው እሱ ከሞተና ትንሣኤ ካገኘ በኋላ በስብከቱ ሥራ የሚካፈሉ ሰዎችንም በአእምሮው ይዞ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም። ደቀ መዛሙርቱን የሚጠሏቸው፣ ሐዋርያቱ እንዲሰብኩ በተላኩባቸው ቦታዎች ያሉ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ‘ሁሉም ሰዎች’ መሆናቸው ይህን ይጠቁማል። በተጨማሪም ሐዋርያት በገሊላ በተካሄደውና ለአጭር ጊዜ በቆየው በዚህ የስብከት ዘመቻ ሲካፈሉ በገዢዎችና በነገሥታት ፊት እንደቀረቡ ወይም የቤተሰባቸው አባላት ለሞት አሳልፈው እንደሰጧቸው የሚገልጽ ዘገባ አናገኝም።

ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረው የወደፊቱን ጊዜ በአእምሮው ይዞ እንደሆነ በግልጽ መመልከት ይቻላል። “የሰው ልጅ እስከሚመጣ ድረስ” ደቀ መዛሙርቱ የስብከቱን ሥራ እንደማያጠናቅቁ የተናገረውን ሐሳብ እንመልከት። ይህን ሲል፣ ክብር የተላበሰው ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክ የተሾመ ፈራጅ ሆኖ ከመምጣቱ በፊት ደቀ መዛሙርቱ ስለ አምላክ መንግሥት የመስበኩን ሥራ እንደማይጨርሱ መናገሩ ነው።

ሐዋርያቱ የስብከቱን ሥራ ሲያከናውኑ ተቃውሞ ቢያጋጥማቸው ሊያስገርማቸው አይገባም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “ደቀ መዝሙር ከአስተማሪው፣ ባሪያም ከጌታው አይበልጥም” ብሏል። ኢየሱስ መናገር የፈለገው ነገር ግልጽ ነው። እሱ ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩ፣ ግፍና ስደት እንደደረሰበት ሁሉ እነሱም እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። ያም ቢሆን ኢየሱስ “ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ፤ ከዚህ ይልቅ ነፍስንም ሆነ ሥጋን በገሃነም ሊያጠፋ የሚችለውን ፍሩ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል።—ማቴዎስ 10:24, 28

በዚህ ረገድ ኢየሱስ ጥሩ ምሳሌ ትቷል። ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ኃይል ባለቤት ለሆነው ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት ከማጉደል ይልቅ እስከ ሞት በድፍረት ጸንቷል። የአንድን ሰው “ነፍስ” (ወደፊት ሕይወት የማግኘት ተስፋውን) ማጥፋት አሊያም ግለሰቡን ከሞት አስነስቶ የዘላለም ሕይወት መስጠት የሚችለው ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ነው። ይህ ሐሳብ ሐዋርያቱን ምንኛ የሚያበረታታ ነው!

ኢየሱስ፣ አምላክ ለተከታዮቹ ያለውን ፍቅራዊ አሳቢነት ለማስረዳት የሚከተለውን ምሳሌ ተጠቅሟል፦ “ሁለት ድንቢጦች የሚሸጡት አነስተኛ ዋጋ ባላት ሳንቲም አይደለም? ሆኖም ከእነሱ አንዷም እንኳ አባታችሁ ሳያውቅ መሬት ላይ አትወድቅም። . . . ስለዚህ አትፍሩ፤ እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ።”—ማቴዎስ 10:29, 31

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሚያውጁት መልእክት ቤተሰብን ይከፋፍላል፤ ምክንያቱም አንዳንዶቹ ሲቀበሉት ሌሎቹ ላይቀበሉት ይችላሉ። ኢየሱስ “በምድር ላይ ሰላም ለማስፈን የመጣሁ አይምሰላችሁ” ብሏል። በእርግጥም አንድ የቤተሰብ አባል የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመቀበል ደፋር መሆን ይኖርበታል። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ሁሉ ለእኔ ሊሆን አይገባም፤ ከእኔ ይልቅ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ሁሉ ለእኔ ሊሆን አይገባም።”—ማቴዎስ 10:34, 37

አንዳንዶች ግን ደቀ መዛሙርቱን ጥሩ አድርገው ይቀበሏቸዋል። ኢየሱስ እንዲህ በማለት ተናገረ፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ የእኔ ደቀ መዝሙር በመሆኑ ምክንያት ከእነዚህ ከትናንሾቹ ለአንዱ አንድ ብርጭቆ ቀዝቃዛ ውኃ የሚሰጥ ሁሉ በምንም ዓይነት ዋጋውን አያጣም።”—ማቴዎስ 10:42

ሐዋርያቱ ከኢየሱስ መመሪያ፣ ማስጠንቀቂያና ማበረታቻ ካገኙ በኋላ “በሄዱበት ሁሉ ምሥራቹን እየተናገሩና የታመሙትን እየፈወሱ ከመንደር ወደ መንደር በመሄድ ክልሉን አዳረሱ።”—ሉቃስ 9:6