በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 62

ስለ ትሕትና የተሰጠ ጠቃሚ ትምህርት

ስለ ትሕትና የተሰጠ ጠቃሚ ትምህርት

ማቴዎስ 17:22–18:5 ማርቆስ 9:30-37 ሉቃስ 9:43-48

  • ኢየሱስ ሞቱን አስመልክቶ በድጋሚ ተናገረ

  • ከዓሣ አፍ በወጣ ሳንቲም ግብር ከፈለ

  • በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጠው ማን ነው?

ኢየሱስ በቂሳርያ ፊልጵስዩስ ክልል በተአምራዊ ሁኔታ ከተለወጠና ጋኔን ይዞት የነበረውን ልጅ ከፈወሰ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም አቀና። የተጓዘው ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ብቻ ነው፤ ምክንያቱም ስለ ጉዞው “ማንም እንዲያውቅ አልፈለገም።” (ማርቆስ 9:30) ይህም ስለ ሞቱ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለማውራትና ከዚያ በኋላ ለሚጠብቃቸው ሥራ እነሱን ለማዘጋጀት ተጨማሪ አጋጣሚ ይሰጠዋል። “የሰውን ልጅ ለሰዎች አሳልፈው ይሰጡታል፤ እነሱም ይገድሉታል፤ እሱም በሦስተኛው ቀን ይነሳል” አላቸው።—ማቴዎስ 17:22, 23

ደቀ መዛሙርቱ ይህ ጉዳይ አዲስ ሊሆንባቸው አይገባም። ጴጥሮስ ሊቀበለው ባይፈልግም እንኳ ኢየሱስ እንደሚገደል ከዚህ በፊት ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 16:21, 22) ሦስቱ ሐዋርያት ደግሞ ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ ሲለወጥ የተመለከቱ ከመሆኑም ሌላ “ከዚህ ዓለም ተለይቶ ስለሚሄድበት” ሁኔታ የተደረገውን ውይይት ሰምተዋል። (ሉቃስ 9:31) በዚህ ወቅት ተከታዮቹ፣ ኢየሱስ የተናገረው ነገር ሙሉ በሙሉ ባይገባቸውም ባነሳው ሐሳብ “በጣም አዘኑ።” (ማቴዎስ 17:23) ያም ቢሆን ስለ ጉዳዩ ተጨማሪ ጥያቄ ለማቅረብ አልደፈሩም።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ የኢየሱስ አገልግሎት ማዕከልና የበርካታ ሐዋርያቱ መኖሪያ ወደሆነችው ቅፍርናሆም ደረሱ። በዚያም የቤተ መቅደሱን ግብር የሚሰበስቡ ሰዎች ወደ ጴጥሮስ መጡ። ከዚያም ጴጥሮስን “መምህራችሁ የቤተ መቅደሱን ግብር አይከፍልም?” ብለው ጠየቁት፤ እንዲህ ያሉት ይህን ሰበብ አድርገው ኢየሱስን ሊከሱት ፈልገው ሊሆን ይችላል።—ማቴዎስ 17:24

ጴጥሮስ “ይከፍላል” በማለት መልስ ሰጠ። ኢየሱስ ቤት ውስጥ ቢሆንም የተከናወነውን ነገር አውቋል። ስለዚህ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ጉዳዩን እስኪያነሳ ሳይጠብቅ “ስምዖን ምን ይመስልሃል? የምድር ነገሥታት ቀረጥ ወይም ግብር የሚቀበሉት ከማን ነው? ከልጆቻቸው ወይስ ከሌሎች?” ብሎ ጠየቀው። ጴጥሮስም “ከሌሎች” ብሎ መለሰ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “እንግዲያው ልጆቹ ግብር ከመክፈል ነፃ ናቸው” አለው።—ማቴዎስ 17:25, 26

የኢየሱስ አባት የአጽናፈ ዓለሙ ንጉሥ ሲሆን በቤተ መቅደሱ የሚመለከውም እሱ ነው። በመሆኑም የአምላክ ልጅ የቤተ መቅደስ ግብር እንዲከፍል ሕጉ አይጠብቅበትም። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦ “እንቅፋት እንዳንሆንባቸው ወደ ባሕሩ ሄደህ መንጠቆ ጣል፤ ከዚያም መጀመሪያ የምትይዘውን ዓሣ አፉን ስትከፍት አንድ የብር ሳንቲም [ስታቴር፣ ወይም ቴትራድራክማ] ታገኛለህ። ሳንቲሙን ወስደህ ለእኔና ለአንተ ክፈል።”—ማቴዎስ 17:27

ብዙም ሳይቆይ ደቀ መዛሙርቱ አንድ ላይ ተሰባሰቡ፤ በመንግሥቱ ታላቅ የሚሆነው ማን እንደሆነ ኢየሱስን ሊጠይቁት አስበዋል። ቀደም ሲል እነዚሁ ሰዎች ኢየሱስን ስለ ወደፊቱ ጊዜ መጠየቅ ፈርተው ነበር። ኢየሱስ ምን እያሰቡ እንዳለ አውቋል። ወደ ቅፍርናሆም ሲመለሱ ከኋላው ቀረት ብለው ሲከራከሩ የነበረው ስለዚሁ ጉዳይ ነው። በመሆኑም “በመንገድ ላይ ስትከራከሩ የነበረው ስለ ምን ጉዳይ ነው?” በማለት ጠየቃቸው። (ማርቆስ 9:33) ደቀ መዛሙርቱ የሚከራከሩት ከመካከላቸው ማን ታላቅ እንደሆነ ስለነበር መልስ ለመስጠት አፍረው ዝም አሉ። በመጨረሻ ግን ሐዋርያት ሲወያዩበት የነበረውን ነገር በማውጣት “በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጠው ማን ነው?” ብለው ጠየቁት።—ማቴዎስ 18:1

ደቀ መዛሙርቱ፣ ወደ ሦስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ኢየሱስ ያከናወነውን ነገር ሲመለከቱና ትምህርቱን ሲያዳምጡ ቆይተው በመካከላቸው እንዲህ ያለ ክርክር መነሳቱ በጣም የሚያስገርም ነው። ለነገሩ ፍጹማን አይደሉም። እንዲሁም ባደጉበት ሃይማኖት ውስጥ ሥልጣንና ማዕረግ ከፍ ተደርገው ይታያሉ። ከዚህም በተጨማሪ ለጴጥሮስ የመንግሥቱ “ቁልፎች” እንደሚሰጡት ኢየሱስ ቃል ከገባ ብዙም አልቆየም። ታዲያ ጴጥሮስ ከሌሎቹ የላቀ እንደሆነ ተሰምቶት ይሆን? ያዕቆብና ዮሐንስ ደግሞ ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ ሲለወጥ ስለተመለከቱ እነሱም ተመሳሳይ ስሜት አድሮባቸው ይሆናል።

ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ኢየሱስ ይህን አስተሳሰብ ለማረም ወዲያውኑ እርምጃ ወሰደ። አንድ ትንሽ ልጅ ጠርቶ በመካከላቸው ካቆመ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “ካልተመለሳችሁና እንደ ልጆች ካልሆናችሁ በምንም ዓይነት ወደ መንግሥተ ሰማያት አትገቡም። ስለዚህ በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጠው እንደዚህ ትንሽ ልጅ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ነው፤ እንዲሁም እንደዚህ ያለውን ትንሽ ልጅ በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔንም ይቀበላል።”—ማቴዎስ 18:3-5

እንዴት ያለ ግሩም የማስተማሪያ ዘዴ ነው! ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በመቆጣት ስግብግቦች ወይም የሥልጣን ጥመኞች እንደሆኑ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ በሚታይ ነገር አስተማራቸው። ልጆች ራሳቸውን ከፍ ከፍ የማድረግና ለሥልጣን የመጓጓት ዝንባሌ የላቸውም። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱም ስለ ራሳቸው እንዲህ ዓይነት አመለካከት ማዳበር እንዳለባቸው አመልክቷል። ኢየሱስ ትምህርቱን ሲደመድም ተከታዮቹን “ታላቅ የሚባለው ራሱን ከሁላችሁ እንደሚያንስ አድርጎ የሚቆጥር ነው” አላቸው።—ሉቃስ 9:48