በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 72

ኢየሱስ 70 ደቀ መዛሙርትን እንዲሰብኩ ላከ

ኢየሱስ 70 ደቀ መዛሙርትን እንዲሰብኩ ላከ

ሉቃስ 10:1-24

  • ኢየሱስ 70 ደቀ መዛሙርትን መርጦ እንዲሰብኩ ላካቸው

ጊዜው 32 ዓ.ም. መገባደጃ አካባቢ ነው፤ ኢየሱስ ከተጠመቀ ሦስት ዓመት ገደማ ሆኖታል። እሱና ደቀ መዛሙርቱ በቅርቡ የዳስ በዓልን በኢየሩሳሌም አክብረዋል። አሁንም በዚያው አካባቢ ሳይሆኑ አይቀሩም። (ሉቃስ 10:38፤ ዮሐንስ 11:1) ለነገሩ ኢየሱስ በቀሩት ስድስት ወራት አብዛኛውን አገልግሎቱን የሚያከናውነው በይሁዳ አሊያም ከዮርዳኖስ ወንዝ ባሻገር በሚገኘው በፔሪያ አውራጃ ነው። በእነዚህ አካባቢዎችም የስብከቱን ሥራ ማከናወን ያስፈልገዋል።

በ30 ዓ.ም. ከተከበረው የፋሲካ በዓል በኋላ ኢየሱስ በይሁዳ ለተወሰኑ ወራት የሰበከ ከመሆኑም ሌላ በሰማርያ በኩል አልፏል። በ31 ዓ.ም. በተከበረው የፋሲካ በዓል አካባቢ በኢየሩሳሌም የሚገኙ አይሁዳውያን ሊገድሉት ሞከሩ። ከዚያ በኋላ ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ኢየሱስ በዋነኝነት ያስተማረው በስተ ሰሜን በምትገኘው በገሊላ ነው። በዚያ ጊዜ ውስጥ ብዙዎች ተከታዮቹ ሆኑ። ኢየሱስ በገሊላ ሳለ ሐዋርያቱን አሠልጥኖ “‘መንግሥተ ሰማያት ቀርቧል’ ብላችሁ ስበኩ” የሚል መመሪያ በመስጠት ልኳቸዋል። (ማቴዎስ 10:5-7) አሁን ደግሞ በይሁዳ የስብከት ዘመቻ አደራጀ።

ኢየሱስ ይህን ዘመቻ የጀመረው 70 ደቀ መዛሙርትን መርጦ ሁለት ሁለት እያደረገ በመላክ ነው። በመሆኑም “አዝመራው ብዙ . . . ሠራተኞቹ ግን ጥቂት” በሆኑበት ክልል ውስጥ 35 ጥንድ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ተሰማሩ። (ሉቃስ 10:2) ኢየሱስ፣ እሱ ሊሄድበት ወዳሰበባቸው ቦታዎች ቀድመውት እንዲሄዱ አደረገ። እነዚህን 70 ደቀ መዛሙርት፣ በሽተኞችን እንዲፈውሱና እሱ እያወጀ ያለውን መልእክት እንዲያሰራጩ አዘዛቸው።

ደቀ መዛሙርቱ በዋነኝነት የሚሰብኩት በምኩራቦች አይደለም። ኢየሱስ፣ ሰዎችን ቤታቸው ድረስ ሄደው እንዲያነጋግሩ ነግሯቸዋል። “ወደ ማንኛውም ቤት ስትገቡ በቅድሚያ ‘ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን’ በሉ። በዚያም ሰላም ወዳድ ሰው ካለ ሰላማችሁ ያርፍበታል” አላቸው። ለሰዎች የሚሰብኩት መልእክትስ ምንድን ነው? ኢየሱስ “‘የአምላክ መንግሥት ወደ እናንተ ቀርቧል’ በሏቸው” የሚል መመሪያ ሰጣቸው።—ሉቃስ 10:5-9

ኢየሱስ ለ70ዎቹ የሰጠው መመሪያ ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት 12ቱን ሐዋርያት በላካቸው ጊዜ ከሰጣቸው መመሪያ ጋር ተመሳሳይ ነው። ጥሩ አድርጎ የሚቀበላቸው ሁሉም ሰው እንዳልሆነ ነገራቸው። ያም ቢሆን እነሱ የሚያከናውኑት ሥራ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎችን ስለሚያዘጋጃቸው ኢየሱስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሲሄድ ብዙዎች ይህን ጌታ ለማግኘትና ከእሱ ለመማር ይጓጓሉ።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ 35ቱ ጥንድ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ወደ ኢየሱስ ተመለሱ። ከዚያም ደስ እያላቸው “ጌታ ሆይ፣ አጋንንት እንኳ በስምህ ተገዙልን” አሉት። ይህ ጥሩ ሪፖርት ኢየሱስን እንዳስደሰተው ምንም አያጠራጥርም፤ ምክንያቱም እንዲህ አላቸው፦ “ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። እነሆ፣ እባቦችንና ጊንጦችን እንድትረግጡ . . . ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ።”—ሉቃስ 10:17-19

ኢየሱስ ይህን ሲል፣ ተከታዮቹ የሚጎዳቸውን ነገር ማሸነፍ እንደሚችሉ ይኸውም በምሳሌያዊ ሁኔታ እባቦችንና ጊንጦችን እንደሚረግጡ ማረጋገጫ መስጠቱ ነው። ከዚህም ሌላ ወደፊት ሰይጣን ከሰማይ እንደሚጣል እርግጠኛ መሆን ይችላሉ። በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ምን እንደሆነ 70ዎቹ እንዲያስተውሉ ሲል “መናፍስት ስለተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፤ ከዚህ ይልቅ ስማችሁ በሰማያት ስለተጻፈ ደስ ይበላችሁ” ብሏቸዋል።—ሉቃስ 10:20

ኢየሱስ በጣም የተደሰተ ሲሆን እነዚህን ተራ አገልጋዮቹን እንዲህ ባለ አስደናቂ መንገድ ስለተጠቀመባቸው አባቱን በሕዝብ ፊት አወድሶታል። ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዞር አለና እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ አሁን የምታዩትን ነገር የሚያዩ ዓይኖች ደስተኞች ናቸው። እላችኋለሁ፣ ብዙ ነቢያትና ነገሥታት እናንተ አሁን የምታዩትን ነገር ለማየት ተመኝተው ነበር፤ ግን አላዩም፤ አሁን የምትሰሙትን ነገር ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ግን አልሰሙም።”—ሉቃስ 10:23, 24