በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 80

ጥሩው እረኛ እና የበጎች ጉረኖዎች

ጥሩው እረኛ እና የበጎች ጉረኖዎች

ዮሐንስ 10:1-21

  • ኢየሱስ ስለ ጥሩው እረኛና ስለ ጉረኖዎቹ ተናገረ

ኢየሱስ በይሁዳ ማስተማሩን ቀጥሏል፤ አድማጮቹ በቀላሉ ሊረዱት የሚችሉትን ነገር ይኸውም በጎችንና ጉረኖዎችን ተጠቀመ። ሆኖም እየተናገረ ያለው በምሳሌያዊ መንገድ ነው። አይሁዳውያኑ “ይሖዋ እረኛዬ ነው። የሚጎድልብኝ ነገር የለም። በለመለመ መስክ ያሳርፈኛል” የሚለውን የዳዊት መዝሙር አስታውሰው ይሆናል። (መዝሙር 23:1, 2) በሌላ መዝሙር ላይ ደግሞ ዳዊት ለብሔሩ የሚከተለውን ግብዣ አቅርቧል፦ “ሠሪያችን በሆነው በይሖዋ ፊት እንንበርከክ። እሱ አምላካችን ነውና፤ እኛ ደግሞ በመስኩ የተሰማራን ሕዝቦች።” (መዝሙር 95:6, 7) አዎን በሕጉ ሥር ያሉ እስራኤላውያን ከጥንት ጀምሮ በበጎች መንጋ ይመሰሉ ነበር።

እነዚህ ‘በጎች’ በሙሴ ሕግ ቃል ኪዳን ሥር ስለተወለዱ ‘በጉረኖ’ ውስጥ ያሉ ያህል ነው። ሕጉ፣ አይሁዳውያንን በዚህ ቃል ኪዳን ውስጥ ያልተካተቱ ሕዝቦች ካሏቸው ብልሹ ልማዶች ስለሚለያቸው እንደ አጥር ሆኖ አገልግሏል። አንዳንድ እስራኤላውያን ግን የአምላክን መንጋ በድለዋል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በበሩ ሳይሆን በሌላ በኩል ዘሎ ወደ በጎቹ ጉረኖ የሚገባ ሌባና ዘራፊ ነው። በበሩ በኩል የሚገባ ግን የበጎቹ እረኛ ነው።”—ዮሐንስ 10:1, 2

ሕዝቡ፣ መሲሕ ወይም ክርስቶስ ነኝ ብለው የተነሱ ሰዎችን አስታውሰው ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሰዎች እንደ ሌባና ዘራፊ ናቸው። ሕዝቡ ሊከተሉ የሚገባው እንዲህ ያሉ አታላዮችን ሳይሆን ‘የበጎቹን እረኛ’ ነው።

ኢየሱስ ይህን እረኛ በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “በር ጠባቂውም ለእሱ ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰማሉ። የራሱን በጎች በየስማቸው ጠርቶ እየመራ ያወጣቸዋል። የራሱ የሆኑትን ሁሉ ካወጣ በኋላ ከፊት ከፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል። እንግዳ የሆነውን ግን ይሸሹታል እንጂ በምንም ዓይነት አይከተሉትም፤ ምክንያቱም የእንግዳ ሰዎችን ድምፅ አያውቁም።”—ዮሐንስ 10:3-5

መጥምቁ ዮሐንስ ልክ እንደ በር ጠባቂ በመሆን፣ በሕጉ ሥር ያሉት በበግ የተመሰሉ ሰዎች ሊከተሉት የሚገባው ኢየሱስን እንደሆነ ቀደም ሲል አሳውቋል። በገሊላ እንዲሁም በዚህ በይሁዳ ያሉ አንዳንድ በጎች የኢየሱስን ድምፅ አውቀውታል። ታዲያ ኢየሱስ ‘እየመራ የሚያወጣቸው’ ወዴት ነው? እሱን መከተልስ ምን ያስገኛል? ይህን ምሳሌ የሰሙ አንዳንዶች፣ ኢየሱስ ‘ምን እያላቸው እንዳለ ስላልገባቸው’ ግር ብሏቸው ሊሆን ይችላል።—ዮሐንስ 10:6

ኢየሱስ እንዲህ ሲል አብራራላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በጎቹ የሚገቡበት በር እኔ ነኝ። አስመሳይ ሆነው በእኔ ስም የመጡ ሁሉ ሌቦችና ዘራፊዎች ናቸው፤ በጎቹ ግን አልሰሟቸውም። በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል የሚገባ ሁሉ ይድናል፤ ይገባል፤ ይወጣል፤ መሰማሪያም ያገኛል።”—ዮሐንስ 10:7-9

ኢየሱስ እየተናገረ ያለው አዲስ ነገር እንደሆነ ግልጽ ነው። አድማጮቹ፣ ለዘመናት ወደቆየው የሕጉ ቃል ኪዳን የሚያስገባው በር ኢየሱስ እንዳልሆነ ያውቃሉ። በመሆኑም እሱ ‘እየመራ የሚያወጣቸው’ በጎች ሌላ ጉረኖ ውስጥ እንደሚገቡ እየተናገረ መሆን አለበት። ታዲያ ምን ይሰጣቸዋል?

ኢየሱስ የሥራ ድርሻውን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ሲሰጥ እንዲህ አለ፦ “እኔ የመጣሁት ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው ነው። እኔ ጥሩ እረኛ ነኝ፤ ጥሩ እረኛ ሕይወቱን ለበጎቹ ሲል አሳልፎ ይሰጣል።” (ዮሐንስ 10:10, 11) ኢየሱስ ከዚህ ቀደም ደቀ መዛሙርቱን “አንተ ትንሽ መንጋ አትፍራ፤ አባታችሁ መንግሥት ሊሰጣችሁ ወስኗልና” በማለት አጽናንቷቸዋል። (ሉቃስ 12:32) አዎን ኢየሱስ ወደ አዲስ ጉረኖ እየመራ የሚወስደው፣ የዚህን “ትንሽ መንጋ” አባላት መሆን አለበት፤ ይህን የሚያደርገውም “ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው” ነው። የዚህ መንጋ አባል መሆን እንዴት ያለ ታላቅ በረከት ነው!

ኢየሱስ ንግግሩን በዚህ አላበቃም። ቀጥሎ እንዲህ አለ፦ “ከዚህ ጉረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነሱንም ማምጣት አለብኝ፤ ድምፄንም ይሰማሉ፤ ሁሉም አንድ መንጋ ይሆናሉ፤ አንድ እረኛም ይኖራቸዋል።” (ዮሐንስ 10:16) ኢየሱስ ስለ እነዚህ “ሌሎች በጎች” ሲናገር “ከዚህ ጉረኖ ያልሆኑ” ብሏቸዋል። በመሆኑም መንግሥቱን ከሚወርሰው “ትንሽ መንጋ” በተለየ ጉረኖ ውስጥ የሚገኙ መሆን አለባቸው። በእነዚህ ሁለት ጉረኖዎች ወይም የበግ በረቶች ውስጥ የሚገኙት በጎች የተለያየ ተስፋ አላቸው። ያም ቢሆን በሁለቱም ጉረኖዎች ውስጥ ያሉት በጎች ኢየሱስ ከሚጫወተው ሚና ጥቅም ያገኛሉ። ኢየሱስ “ሕይወቴን . . . አሳልፌ ስለምሰጣት አብ ይወደኛል” ብሏል።—ዮሐንስ 10:17

ከሕዝቡ መካከል ብዙዎቹ “ይህ ሰው ጋኔን አለበት፤ አእምሮውን ስቷል” አሉ። ሌሎቹ ግን በትኩረት እያዳመጡት እንዳሉና ጥሩውን እረኛ መከተል እንደሚፈልጉ አሳዩ። “ጋኔን የያዘው ሰው እንዲህ አይናገርም። ጋኔን የዓይነ ስውራንን ዓይን ሊከፍት ይችላል እንዴ?” አሉ። (ዮሐንስ 10:20, 21) ይህን ያሉት ኢየሱስ ቀደም ሲል የፈወሰውን ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደ ሰው በአእምሯቸው ይዘው እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።