በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 81

ኢየሱስና አብ አንድ የሆኑት እንዴት ነው?

ኢየሱስና አብ አንድ የሆኑት እንዴት ነው?

ዮሐንስ 10:22-42

  • “እኔና አብ አንድ ነን”

  • ኢየሱስ ‘ራስህን አምላክ አድርገሃል’ በሚል የተሰነዘረበት ክስ ሐሰት መሆኑን ገለጸ

ኢየሱስ ለመታደስ በዓል (ወይም ሃኑካ) ወደ ኢየሩሳሌም መጥቷል። ይህ በዓል የሚከበረው ቤተ መቅደሱ ለይሖዋ አምልኮ እንደገና መወሰኑን ለማሰብ ነው። ሶርያዊው ንጉሥ አንታይከስ አራተኛ (ኢፒፋነስ) በአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ በሚገኘው ታላቅ መሠዊያ ላይ ሌላ መሠዊያ አቁሞ ነበር። ከጊዜ በኋላ የአንድ አይሁዳዊ ካህን ልጆች፣ ኢየሩሳሌምን በድጋሚ በመቆጣጠር ቤተ መቅደሱ ለይሖዋ አምልኮ እንደገና እንዲወሰን አደረጉ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ በየዓመቱ ኪስሌው 25 ላይ ይህ በዓል ይከበራል፤ ኪስሌው በኅዳር መገባደጃና በታኅሣሥ መጀመሪያ አካባቢ ባለው ጊዜ ላይ ያርፋል።

ይህ አየሩ የሚቀዘቅዝበት ወቅት ነው። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚገኘውንና መጠለያ ያለውን የሰለሞን መተላለፊያ እያቋረጠ ነው። በዚያም አይሁዳውያን ከበቡትና “እስከ መቼ ድረስ ልባችንን ታንጠለጥላለህ? አንተ ክርስቶስ ከሆንክ በግልጽ ንገረን” አሉት። (ዮሐንስ 10:22-24) ኢየሱስ ምን ምላሽ ይሰጥ ይሆን? “እኔ ነግሬአችኋለሁ፤ እናንተ ግን አታምኑም” በማለት መለሰላቸው። ኢየሱስ በውኃ ጉድጓድ አጠገብ ላገኛት ሳምራዊት እንዳደረገው እሱ ክርስቶስ መሆኑን በቀጥታ አልነገራቸውም። (ዮሐንስ 4:25, 26) ሆኖም “አብርሃም ከመወለዱ በፊት እኔ ነበርኩ” ባለ ጊዜ ማንነቱን ገልጾላቸዋል።—ዮሐንስ 8:58

ኢየሱስ፣ መሲሑ እንደሚፈጽማቸው በትንቢት የተነገሩትን ነገሮች እሱ ካከናወናቸው ሥራዎች ጋር በማወዳደር እሱ ክርስቶስ መሆኑን ሕዝቡ ራሱ መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ ፈልጓል። መሲሕ መሆኑን ለማንም እንዳይናገሩ ደቀ መዛሙርቱን አንዳንድ ጊዜ ያስጠነቀቃቸው ለዚህ ነው። አሁን ግን ጠላቶቹ ለሆኑት ለእነዚህ አይሁዳውያን “በአባቴ ስም እየሠራኋቸው ያሉት ሥራዎች ስለ እኔ ይመሠክራሉ። ሆኖም እናንተ . . . አታምኑም” በማለት በቀጥታ ነገራቸው።—ዮሐንስ 10:25, 26

እሱ፣ ክርስቶስ መሆኑን ያላመኑት ለምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ በጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም። በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ እነሱም ይከተሉኛል። የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፤ መቼም ቢሆን ጥፋት አይደርስባቸውም፤ ከእጄ የሚነጥቃቸውም የለም። አባቴ የሰጠኝ በጎች ከሌሎች ነገሮች ሁሉ ይበልጣሉ።” ኢየሱስ ቀጥሎም ከአባቱ ጋር ምን ያህል የቀረበ ግንኙነት እንዳለው ሲገልጽ “እኔና አብ አንድ ነን” አላቸው። (ዮሐንስ 10:26-30) ኢየሱስ በምድር አባቱ ደግሞ በሰማይ ስለሆነ ቃል በቃል ከአብ ጋር አንድ እንደሆኑ እየገለጸ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የዓላማ አንድነት እንዳላቸው መናገሩ ነው።

አይሁዳውያኑ ኢየሱስ በተናገረው ነገር በጣም ስለተናደዱ አሁንም ሊወግሩት ድንጋይ አነሱ። ኢየሱስ ግን በዚህ አልተደናገጠም። “ከአብ ዘንድ ብዙ መልካም ሥራዎች አሳየኋችሁ። ታዲያ የምትወግሩኝ ከእነዚህ ሥራዎች መካከል በየትኛው የተነሳ ነው?” አላቸው። እነሱም “እኛ የምንወግርህ ስለ መልካም ሥራህ ሳይሆን . . . ራስህን አምላክ በማድረግ አምላክን ስለተዳፈርክ ነው” ሲሉ መለሱለት። (ዮሐንስ 10:31-33) ኢየሱስ፣ አምላክ እንደሆነ ፈጽሞ ተናግሮ አያውቅም፤ ታዲያ አይሁዳውያን እንዲህ ብለው የከሰሱት ለምንድን ነው?

አይሁዳውያኑ፣ አምላክ ብቻ እንዳለው የሚሰማቸው ዓይነት ኃይል ኢየሱስ ያለው መሆኑን ስለተናገረ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ስለ በጎቹ ሲናገር “የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ” ብሏል፤ ይህን ደግሞ ማንም ሰው ሊያደርገው አይችልም። (ዮሐንስ 10:28) አይሁዳውያን፣ ኢየሱስ ሥልጣኑን የተቀበለው ከአባቱ መሆኑን በግልጽ እንደተናገረ አላስተዋሉም።

ኢየሱስ የሰነዘሩት ክስ ሐሰት መሆኑን ለመግለጽ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፦ “በሕጋችሁ [በመዝሙር 82:6] ላይ ‘“እናንተ አማልክት ናችሁ” አልኩ’ ተብሎ ተጽፎ የለም? የአምላክ ቃል ያወገዛቸውን እሱ ‘አማልክት’ ብሎ ከጠራቸው . . . አብ የቀደሰኝንና ወደ ዓለም የላከኝን እኔን፣ ‘የአምላክ ልጅ ነኝ’ ስላልኩ ‘አምላክን ትዳፈራለህ’ ትሉኛላችሁ?”—ዮሐንስ 10:34-36

ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ፍርደ ገምድል ፈራጆችን እንኳ “አማልክት” ብለው ይጠሯቸዋል። ታዲያ ኢየሱስ “የአምላክ ልጅ ነኝ” በማለቱ እነዚህ አይሁዳውያን ሊተቹት ይችላሉ? ኢየሱስ ሊያሳምናቸው የሚችል ማስረጃ ጠቀሰ፦ “እኔ የአባቴን ሥራ እየሠራሁ ካልሆነ አትመኑኝ። የአባቴን ሥራ እየሠራሁ ከሆነ ግን እኔን ባታምኑኝ እንኳ ሥራዬን እመኑ፤ ይህም አብ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለው እንዲሁም እኔም ከአብ ጋር አንድነት እንዳለኝ እንድታውቁና ይህን ይበልጥ እያወቃችሁ እንድትሄዱ ነው።”—ዮሐንስ 10:37, 38

አይሁዳውያን ይህን ሲሰሙ ኢየሱስን ሊይዙት ሞከሩ፤ ሆኖም በድጋሚ አመለጣቸው። ከዚያም ኢየሩሳሌምን ለቆ ወጣና ዮሐንስ ከአራት ዓመት ገደማ በፊት ማጥመቅ ወደጀመረበት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ ተሻገረ። ይህ ቦታ ከገሊላ ባሕር ደቡባዊ ዳርቻ ብዙም የሚርቅ አይመስልም።

ብዙ ሰዎች ወደ ኢየሱስ መጥተው “ዮሐንስ አንድም ተአምራዊ ምልክት አላደረገም፤ ሆኖም ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ነገር ሁሉ እውነት ነበር” አሉ። (ዮሐንስ 10:41) በመሆኑም ብዙ አይሁዳውያን በኢየሱስ አመኑ።