በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 82

ኢየሱስ በፔሪያ ያከናወነው አገልግሎት

ኢየሱስ በፔሪያ ያከናወነው አገልግሎት

ሉቃስ 13:22–14:6

  • በጠባብ በር ለመግባት ተጋድሎ ማድረግ

  • ኢየሱስ መገደል ያለበት በኢየሩሳሌም ነው

ኢየሱስ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ሰዎችን ሲያስተምርና ሲፈውስ ቆይቷል። ከዚያም የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግሮ በፔሪያ አውራጃ ከከተማ ወደ ከተማ እየሄደ ማስተማር ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ግን ወደ ኢየሩሳሌም ይመለሳል።

ኢየሱስ በፔሪያ ሳለ አንድ ሰው “ጌታ ሆይ፣ የሚድኑት ጥቂቶች ናቸው?” ብሎ ጠየቀው። ሰውየው፣ የሚድኑት ብዙዎች ናቸው ወይስ ጥቂቶች ስለሚለው ጉዳይ በሃይማኖት መሪዎቹ መካከል ውዝግብ እንዳለ ሳያውቅ አይቀርም። ኢየሱስ፣ ምን ያህል ሰዎች እንደሚድኑ ከመግለጽ ይልቅ ለመዳን ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናገረ። “በጠባቡ በር ለመግባት ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጉ” አላቸው። በእርግጥም ጥረትና ትግል ያስፈልጋል። ለምን? “እላችኋለሁ፦ ብዙዎች ለመግባት ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን አይችሉም” በማለት ኢየሱስ ተናግሯል።—ሉቃስ 13:23, 24

ከዚያም፣ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በምሳሌ ለማስረዳት እንዲህ አለ፦ “የቤቱ ባለቤት ተነስቶ አንዴ በሩን ከዘጋው በኋላ ውጭ ቆማችሁ ‘ጌታ ሆይ፣ ክፈትልን’ እያላችሁ በሩን ብታንኳኩ . . . ‘ከየት እንደመጣችሁ አላውቅም። እናንተ ክፉ አድራጊዎች ሁሉ፣ ከእኔ ራቁ!’ ይላችኋል።”—ሉቃስ 13:25-27

ይህ ምሳሌ፣ ዘግይቶ በመምጣቱ በሩ ተዘግቶና ተቆልፎ የጠበቀው ሰው የሚያጋጥመውን ችግር ያሳያል፤ ግለሰቡ የዘገየው ለራሱ አመቺ በሆነው ጊዜ ስለመጣ ሊሆን ይችላል። ሁኔታው ባይመቸውም እንኳ ቀደም ብሎ መምጣት ነበረበት። ኢየሱስ በዚያ ሆኖ ካስተማረው ነገር ጥቅም ማግኘት ይችሉ የነበሩ ብዙዎች የሚያጋጥማቸው ሁኔታ ይህ ግለሰብ ካጋጠመው ጋር ይመሳሰላል። እውነተኛው አምልኮ በሕይወታቸው ውስጥ ዋነኛውን ቦታ እንዲይዝ ሳያደርጉ ቀርተዋል። ኢየሱስ እንዲያገለግላቸው የተላከላቸው አብዛኞቹ ሰዎች አምላክ ያደረገላቸውን የመዳን ዝግጅት ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። እነዚህ ሰዎች ወደ ውጭ ሲጣሉ ‘እንደሚያለቅሱና ጥርሳቸውን እንደሚያፋጩ’ ተናግሯል። በሌላ በኩል ግን “ከምሥራቅና ከምዕራብ እንዲሁም ከሰሜንና ከደቡብ” ይኸውም ከሁሉም ብሔራት የመጡ ሰዎች “በአምላክ መንግሥት በማዕድ ይቀመጣሉ።”—ሉቃስ 13:28, 29

ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ከኋለኞች [ለምሳሌ አይሁዳውያን ካልሆኑና ዝቅ ተደርገው ከሚታዩ አይሁዳውያን] መካከል ፊተኞች የሚሆኑ፣ ከፊተኞች [ማለትም የአብርሃም ዘሮች በመሆናቸው ከሚኮሩ የሃይማኖት መሪዎች] መካከልም ኋለኞች የሚሆኑ አሉ።” (ሉቃስ 13:30) “ኋለኞች” እንደሚሆኑ መገለጹ እንዲህ ያሉ አመስጋኝ ያልሆኑ ሰዎች የአምላክን መንግሥት ፈጽሞ እንደማይወርሱ የሚያሳይ ነው።

በዚህ ጊዜ አንዳንድ ፈሪሳውያን ወደ ኢየሱስ መጥተው “ሄሮድስ [አንቲጳስ] ሊገድልህ ስለሚፈልግ ከዚህ ውጣና ሂድ” ብለው መከሩት። ኢየሱስ በፍጥነት ክልሉን ለቆ እንዲወጣ ለማድረግ ሲል ይህን ወሬ ያስወራው ንጉሥ ሄሮድስ ራሱ ሊሆን ይችላል። ሄሮድስ፣ በመጥምቁ ዮሐንስ ግድያ ውስጥ እጁ እንደነበረበት ሁሉ አሁን ደግሞ ሌላ ነቢይ እንዳያስገድል ፈርቶ ይሆናል። ኢየሱስ ግን ፈሪሳውያኑን “ሄዳችሁ ያንን ቀበሮ ‘ዛሬና ነገ አጋንንትን አስወጣለሁ እንዲሁም ሰዎችን እፈውሳለሁ፤ በሦስተኛውም ቀን ሥራዬን አጠናቅቃለሁ’ በሉት” አላቸው። (ሉቃስ 13:31, 32) ኢየሱስ ሄሮድስን “ቀበሮ” ብሎ የጠራው ቀበሮዎች ተንኮለኛ መሆናቸውን አስቦ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ሄሮድስም ሆነ ማንኛውም ሰው በኢየሱስ ላይ ተጽዕኖ ሊያደርግ ወይም ሊያጣድፈው አይችልም። አባቱ የሰጠውን ሥራ የሚያከናውነው በሰው ሳይሆን በአምላክ ፕሮግራም መሠረት ነው።

ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም የሚጓዝበትን ምክንያት ሲገልጽ “ነቢይ ከኢየሩሳሌም ውጭ ሊገደል” እንደማይችል ተናግሯል። (ሉቃስ 13:33) መሲሑ በዚያች ከተማ መገደል እንዳለበት የሚገልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የለም፤ ታዲያ ኢየሱስ በዚያ እንደሚገደል የተናገረው ለምንድን ነው? ምክንያቱም 71 አባላት ያሉት የሳንሄድሪን ከፍተኛ ሸንጎ የሚገኘው የብሔሩ ዋና ከተማ በሆነችው በኢየሩሳሌም ነው፤ እንዲሁም የሐሰት ነቢያት በመሆናቸው የተከሰሱ ሰዎች ለፍርድ የሚቀርቡት በዚህች ከተማ ነው። በተጨማሪም እንስሳት መሥዋዕት የሚደረጉት እዚያ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ በሌላ ቦታ መገደሉ ተገቢ እንዳልሆነ ተገንዝቧል።

ኢየሱስ እንዲህ በማለት በሐዘን ተናገረ፦ “ኢየሩሳሌም፣ ኢየሩሳሌም፣ ነቢያትን የምትገድል፤ ወደ እሷ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግር፤ ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ እኔም ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግኩ! እናንተ ግን አልፈለጋችሁም። እነሆ፣ ቤታችሁ ለእናንተ የተተወ ይሆናል።” (ሉቃስ 13:34, 35) ብሔሩ የአምላክን ልጅ አለመቀበሉ ከሚያስከትለው መዘዝ ማምለጥ አይችልም!

ኢየሱስ ኢየሩሳሌም ከመድረሱ በፊት ከፈሪሳውያን መሪዎች አንዱ ቤቱ ጋበዘው፤ ቀኑ ሰንበት ነው። በቤቱ ውስጥ፣ ሰውነት የሚያሳብጥ በሽታ የያዘው አንድ ሰው ተገኝቷል (ይህ ብዙውን ጊዜ በእጅና በእግር ውስጥ ከልክ በላይ ፈሳሽ እንዲጠራቀም የሚያደርግ በሽታ ነው)፤ የተጋበዙት ሰዎች ኢየሱስ ከዚህ ሰው ጋር በተያያዘ ምን እንደሚያደርግ በትኩረት እየተከታተሉ ነው። ኢየሱስ፣ ፈሪሳውያንንና ሕግ አዋቂዎቹን “በሰንበት መፈወስ በሕግ ተፈቅዷል ወይስ አልተፈቀደም?” ሲል ጠየቃቸው።—ሉቃስ 14:3

ማንም መልስ አልሰጠውም። ኢየሱስ ሰውየውን ከፈወሰው በኋላ “ከእናንተ መካከል ልጁ ወይም በሬው በሰንበት ቀን የውኃ ጉድጓድ ውስጥ ቢወድቅ ወዲያውኑ ጎትቶ የማያወጣው ማን ነው?” ሲል ጠየቃቸው። (ሉቃስ 14:5) ላቀረበው አሳማኝ ነጥብ አሁንም መልስ መስጠት አልቻሉም።