በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 101

በቢታንያ በስምዖን ቤት የተደረገ ግብዣ

በቢታንያ በስምዖን ቤት የተደረገ ግብዣ

ማቴዎስ 26:6-13 ማርቆስ 14:3-9 ዮሐንስ 11:55–12:11

  • ኢየሱስ፣ ኢየሩሳሌም አቅራቢያ ወደምትገኘው ቢታንያ ተመለሰ

  • ማርያም ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት በኢየሱስ ላይ አፈሰሰች

ኢየሱስ ከኢያሪኮ ከወጣ በኋላ ወደ ቢታንያ አቀና። እዚያ ለመድረስ አቀበታማ በሆነ አስቸጋሪ መንገድ ላይ 20 ኪሎ ሜትር ያህል መጓዝ ይጠይቃል። ኢያሪኮ ከባሕር ጠለል በታች 250 ሜትር ገደማ ላይ የምትገኝ ሲሆን ቢታንያ ደግሞ ከባሕር ጠለል በላይ 610 ሜትር ያህል ከፍታ ላይ ትገኛለች። አልዓዛርና ሁለት እህቶቹ የሚኖሩት ከኢየሩሳሌም 3 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በደብረ ዘይት ተራራ ምሥራቃዊ አቀበት ላይ በምትገኘው ቢታንያ የተባለች ትንሽ መንደር ነው።

በርካታ አይሁዳውያን ለፋሲካ በዓል ኢየሩሳሌም ገብተዋል። እነዚህ ሰዎች ከበዓሉ ቀደም ብለው የመጡት “የመንጻት ሥርዓት ለመፈጸም” ነው፤ ምናልባትም አስከሬን ነክተው ወይም ደግሞ ሌላ የሚያረክስ ነገር አድርገው ሊሆን ይችላል። (ዮሐንስ 11:55፤ ዘኁልቁ 9:6-10) ቀደም ብለው ከመጡት አንዳንዶቹ በቤተ መቅደሱ ተሰባስበዋል። ሰዎቹ ኢየሱስ ለፋሲካ በዓል ይመጣ እንደሆነ እየተወያዩ ነው።—ዮሐንስ 11:56

ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ ብዙ ውዝግብ ተነስቷል። አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስን ይዘው ሊገድሉት ፈልገዋል። እንዲያውም “ኢየሱስን መያዝ እንዲችሉ እሱ ያለበትን ቦታ የሚያውቅ ሁሉ እንዲጠቁማቸው” አዘዋል። (ዮሐንስ 11:57) እነዚህ መሪዎች፣ አልዓዛርን ከሞት ካስነሳው በኋላ ኢየሱስን ሊገድሉት ሞክረው ነበር። (ዮሐንስ 11:49-53) በመሆኑም አንዳንዶች፣ የኢየሱስ መምጣት ቢያጠራጥራቸው የሚያስገርም አይደለም።

ኢየሱስ “የፋሲካ በዓል ከመድረሱ ከስድስት ቀን በፊት” ይኸውም ዓርብ ዕለት ወደ ቢታንያ መጣ። (ዮሐንስ 12:1) በዚህ ዕለት ፀሐይ ስትጠልቅ አዲስ ቀን (ኒሳን 8) ይጀምራል፤ ይህ ቀን ሰንበት ነው። በመሆኑም ኢየሱስ ሰንበት ከመጀመሩ በፊት ጉዞውን አጠናቋል። የአይሁድ ሕግ በሰንበት ረጅም መንገድ መጓዝን ይከለክላል፤ ስለዚህ ኢየሱስ በሰንበት ይኸውም ዓርብ ፀሐይ ከጠለቀችበት ጊዜ አንስቶ ቅዳሜ ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ከኢያሪኮ ተነስቶ መጓዝ አይችልም ነበር። ኢየሱስ ቀደም ሲል እንዳደረገው አሁንም ወደ አልዓዛር ቤት ሳይሄድ አልቀረም።

በቢታንያ የሚኖረው ስምዖን፣ አልዓዛርን ጨምሮ ኢየሱስንና አብረውት ያሉትን ሰዎች ቅዳሜ ምሽት ራት ጋበዛቸው። ስምዖን “የሥጋ ደዌ በሽተኛ” ተብሎ የተጠራው ቀደም ሲል ይህ በሽታ ስለነበረበት ሊሆን ይችላል፤ ኢየሱስ በሆነ ወቅት ላይ ፈውሶት ይሆናል። ታታሪ የሆነችው ማርታ እንደተለመደው እንግዶቹን እያስተናገደች ነው። ማርያም ደግሞ ለኢየሱስ ልዩ ትኩረት ሰጥታለች፤ በዚህ ጊዜ ያደረገችው ነገር ክርክር አስነሳ።

ማርያም፣ “ግማሽ ሊትር ገደማ የሚሆን . . . ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ይኸውም ንጹሕ ናርዶስ” የያዘ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ከፈተች። (ዮሐንስ 12:3) ይህ ሽቶ በጣም ውድ ነው፤ እንዲያውም ዋጋው የአንድ ዓመት ደሞዝ (300 ዲናር) ያህል ነው! ማርያም ዘይቱን በኢየሱስ ራስና እግር ላይ ካፈሰሰች በኋላ እግሩን በፀጉሯ አበሰች። የዘይቱ መዓዛ ቤቱን አወደው።

በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ተቆጥተው “ይህ ዘይት እንዲህ የሚባክነው ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁ። (ማርቆስ 14:4) የአስቆሮቱ ይሁዳም “ይህ ዘይት በ300 ዲናር ተሸጦ ገንዘቡ ለድሆች ያልተሰጠው ለምንድን ነው?” በማለት ተቃውሞውን ገለጸ። (ዮሐንስ 12:5) ይሁዳ እንዲህ ያለው ለድሆች አስቦ ሳይሆን እሱ ጋ ከሚቀመጠው የደቀ መዛሙርቱ የገንዘብ ሣጥን የመስረቅ ልማድ ስላለው ነው።

ኢየሱስ ግን ማርያምን በመደገፍ እንዲህ አለ፦ “ይህችን ሴት ለምን ታስቸግሯታላችሁ? እሷ ለእኔ መልካም ነገር አድርጋለች። ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ እኔን ግን ሁልጊዜ አታገኙኝም። ይህች ሴት ዘይቱን በሰውነቴ ላይ ስታፈስ እኔን ለቀብር ማዘጋጀቷ ነው። እውነት እላችኋለሁ፣ በመላው ዓለም ይህ ምሥራች በሚሰበክበት ቦታ ሁሉ ይህች ሴት ያደረገችውም መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል።”—ማቴዎስ 26:10-13

ኢየሱስ ቢታንያ ከደረሰ አንድ ቀን ስላለፈ እዚያ እንዳለ የሚገልጽ ወሬ ተሰራጨ። ብዙ አይሁዳውያን ኢየሱስን ብቻ ሳይሆን “እሱ ከሞት ያስነሳውን አልዓዛርንም” ለማየት ወደ ስምዖን ቤት መጡ። (ዮሐንስ 12:9) በዚህ ጊዜ የካህናት አለቆቹ ኢየሱስን እና አልዓዛርን ለመግደል ተማከሩ። እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች፣ ብዙ ሰዎች በኢየሱስ እያመኑ ያሉት አልዓዛር ከሞት በመነሳቱ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። የሃይማኖት መሪዎቹ ምንኛ ክፉ ናቸው!