በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 115

ኢየሱስ የሚያከብረው የመጨረሻ ፋሲካ ተቃረበ

ኢየሱስ የሚያከብረው የመጨረሻ ፋሲካ ተቃረበ

ማቴዎስ 26:1-5, 14-19 ማርቆስ 14:1, 2, 10-16 ሉቃስ 22:1-13

  • የአስቆሮቱ ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ ገንዘብ ተከፈለው

  • ሁለት ሐዋርያት ለፋሲካ ዝግጅት አደረጉ

ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ አራት ሐዋርያቱን አስተምሮ መጨረሱ ነው፤ ሐዋርያቱ ወደፊት በመንግሥቱ ስለሚገኝበት ጊዜና ስለ ሥርዓቱ መደምደሚያ ላነሱት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ቆይቷል።

ኒሳን 11 ምንኛ ሥራ የበዛበት ዕለት ነው! ኢየሱስ ሐዋርያቱን “እንደምታውቁት ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ ይከበራል፤ የሰው ልጅም በእንጨት ላይ እንዲሰቀል አልፎ ይሰጣል” አላቸው፤ ይህን ያለው በቢታንያ ለማደር ወደዚያ እየተመለሱ እያለ ሊሆን ይችላል።—ማቴዎስ 26:2

ኢየሱስ ቀጣዩን ቀን ማለትም ረቡዕን ያሳለፈው ከሐዋርያቱ ጋር ብቻ ሳይሆን አይቀርም። ማክሰኞ ዕለት የሃይማኖት መሪዎቹን በሕዝብ ፊት አውግዟቸውና ሥራቸውን አጋልጦ ነበር። በመሆኑም ሊገድሉት ፈልገዋል። ኢየሱስ በሚቀጥለው ቀን ምሽት ይኸውም ኒሳን 14 ሲጀምር ከሐዋርያቱ ጋር ሆኖ የሚያከብረውን የፋሲካ በዓል ምንም ነገር እንዲያስተጓጉልበት ስላልፈለገ ኒሳን 12 በሕዝብ ፊት አልታየም።

ይሁንና የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ከፋሲካ በፊት እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም። ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰበሰቡ። ለምን? ኢየሱስ ስላጋለጣቸው ተበሳጭተዋል። አሁን “የተንኮል ዘዴ በመጠቀም ኢየሱስን ለመያዝና ለመግደል ሴራ ጠነሰሱ።” ታዲያ ይህን የሚያደርጉት መቼና እንዴት ነው? “በሕዝቡ መካከል ሁከት እንዳይፈጠር በበዓሉ ወቅት መሆን የለበትም” ተባባሉ። (ማቴዎስ 26:4, 5) ብዙዎች ኢየሱስን ስለሚወዱት የሃይማኖት መሪዎቹ ሕዝቡን ፈርተዋል።

በዚህ መሃል አንድ ሰው ወደ ሃይማኖት መሪዎቹ መጣ። ሰውየው ከኢየሱስ ሐዋርያት አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ መሆኑ ሳያስገርማቸው አልቀረም! ሰይጣን በይሁዳ ልብ ውስጥ ኢየሱስን አሳልፎ የመስጠት ሐሳብ አሳድሯል! ይሁዳ “እሱን አሳልፌ ብሰጣችሁ ምን ትሰጡኛላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። (ማቴዎስ 26:15) “እነሱም በጉዳዩ ተደስተው የብር ገንዘብ ሊሰጡት ተስማሙ።” (ሉቃስ 22:5) ለመሆኑ ምን ያህል? ምንም ሳያንገራግሩ 30 የብር ሳንቲሞች ለመስጠት ፈቃደኛ ሆኑ። የአንድ ባሪያ ዋጋ 30 ሰቅል መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። (ዘፀአት 21:32) የሃይማኖት መሪዎቹ ለአስቆሮቱ ይሁዳ ለመስጠት የተስማሙት ገንዘብ፣ ኢየሱስን እንደሚንቁትና ዝቅ አድርገው እንደሚመለከቱት ያሳያል። ከዚህ በኋላ ይሁዳ “ሕዝብ በሌለበት እሱን አሳልፎ መስጠት የሚችልበትን ምቹ አጋጣሚ ይፈልግ ጀመር።”—ሉቃስ 22:6

ኒሳን 13፣ ረቡዕ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ይጀምራል፤ በመሆኑም ኢየሱስ በቢታንያ ሲያድር ይህ ስድስተኛውና የመጨረሻው ቀን ነው። በማግስቱ ለፋሲካ በዓል የመጨረሻ ዝግጅቶች መከናወን አለባቸው። ኒሳን 14 ከጀመረ በኋላ የሚታረደውንና ሙሉውን የሚጠበሰውን በግ ማምጣት ያስፈልጋል። በዓሉን የሚያከብሩት የት ነው? ዝግጅቱን የሚያደርግላቸውስ ማን ይሆን? ኢየሱስ ስለዚህ ጉዳይ በዝርዝር አልነገራቸውም። በመሆኑም ይሁዳ ይህን መረጃ ለካህናት አለቆቹ መስጠት አይችልም።

ሐሙስ ቀትር ላይ ሳይሆን አይቀርም፣ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ዮሐንስን “ሄዳችሁ ፋሲካን እንድንበላ አዘጋጁልን” ብሎ ከቢታንያ ላካቸው። እነሱም “የት እንድናዘጋጅ ትፈልጋለህ?” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ከተማው ስትገቡ የውኃ እንስራ የተሸከመ ሰው ታገኛላችሁ። እሱን ተከትላችሁ ወደሚገባበት ቤት ሂዱ። የቤቱንም ባለቤት ‘መምህሩ “ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ የት ነው?” ብሎሃል’ በሉት። ሰውየውም የተሰናዳ ሰፊ ሰገነት ያሳያችኋል፤ በዚያ አዘጋጁ።”—ሉቃስ 22:8-12

የቤቱ ባለቤት፣ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ በዓሉን በእሱ ቤት ለማክበር እንደሚጠይቀው ጠብቆ ይሆናል። ሁለቱ ሐዋርያት ኢየሩሳሌም ሲደርሱ ሁሉም ነገር ኢየሱስ እንዳለው ሆኖ አገኙት። ስለዚህ እነዚህ ሐዋርያት፣ በጉን እንዲሁም የፋሲካን ራት የሚበሉት 13 ሰዎች ማለትም ኢየሱስና 12 ሐዋርያቱ የሚያስፈልጓቸውን ሌሎች ነገሮች በሙሉ አዘጋጁ።