በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 119

ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት

ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት

ዮሐንስ 14:1-31

  • ኢየሱስ ቦታ ለማዘጋጀት ይሄዳል

  • ረዳት እንደሚያገኙ ለተከታዮቹ ቃል ገባላቸው

  • አብ ከኢየሱስ ይበልጣል

ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ካቋቋመ በኋላ አሁንም ከሐዋርያቱ ጋር በሰገነት ላይ በሚገኘው ክፍል ውስጥ ነው። እንዲህ ሲል አበረታታቸው፦ “ልባችሁ አይረበሽ። በአምላክ እመኑ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ።”—ዮሐንስ 13:36፤ 14:1

ኢየሱስ፣ ታማኝ ሐዋርያቱ እሱ በመሄዱ መሸበር የሌለባቸው ለምን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ አላቸው፦ “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ ቦታ አለ። . . . ሄጄ ቦታ ባዘጋጀሁላችሁ ጊዜ እኔ ባለሁበት እናንተም እንድትሆኑ እንደገና መጥቼ እኔ ወዳለሁበት እወስዳችኋለሁ።” ሐዋርያቱ ግን ወደ ሰማይ ስለ መሄድ እያወራ እንደሆነ አልገባቸውም። በመሆኑም ቶማስ “ጌታ ሆይ፣ ወዴት እንደምትሄድ አናውቅም። ታዲያ መንገዱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?” በማለት ጠየቀው።—ዮሐንስ 14:2-5

ኢየሱስም “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ” አለው። አንድ ሰው በሰማይ ወደሚገኘው የኢየሱስ አባት ቤት መግባት የሚችለው ክርስቶስንና ትምህርቶቹን የሚቀበል እንዲሁም የእሱን አርዓያ የሚከተል ከሆነ ብቻ ነው። ኢየሱስ “በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” አለ።—ዮሐንስ 14:6

በጥሞና እያዳመጠ ያለው ፊልጶስ “ጌታ ሆይ፣ አብን አሳየንና ይበቃናል” በማለት ጠየቀው። ፊልጶስ ይህን ያለው በጥንት ዘመን ሙሴ፣ ኤልያስና ኢሳይያስ የተመለከቱት ዓይነት ራእይ በማሳየት አምላክን እንዲገልጥላቸው ፈልጎ ይመስላል። ይሁንና ሐዋርያት እንዲህ ዓይነቶቹን ራእዮች ከመመልከት የበለጠ አጋጣሚ አግኝተዋል። ኢየሱስ ይህን ሲያጎላ እንዲህ ብሎ መለሰ፦ “ፊልጶስ፣ ከእናንተ ጋር ይህን ያህል ረጅም ጊዜ ኖሬም እንኳ አላወቅከኝም? እኔን ያየ ሁሉ አብንም አይቷል።” ኢየሱስ የአባቱን ባሕርይ ፍጹም በሆነ መንገድ ያንጸባረቀ በመሆኑ ከእሱ ጋር መኖርና እሱን መመልከት አብን እንደ መመልከት ይቆጠራል። እርግጥ ነው፣ አብ ከወልድ ይበልጣል፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “የምነግራችሁን ነገር የምናገረው ከራሴ አመንጭቼ አይደለም” ብሏል። (ዮሐንስ 14:8-10) ኢየሱስ ለሚያስተምረው ትምህርት ሊከበር የሚገባው አባቱ መሆኑን እየገለጸ እንደሆነ ሐዋርያቱ ማስተዋል ይችላሉ።

የኢየሱስ ሐዋርያት፣ ጌታ አስደናቂ ሥራዎችን ሲያከናውን ተመልክተዋል፤ እንዲሁም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ሲያውጅ ሰምተዋል። አሁን ደግሞ “በእኔ የሚያምን ሁሉ እኔ የምሠራቸውን ሥራዎች ይሠራል፤ እንዲያውም እኔ ወደ አብ ስለምሄድ እሱ ከእነዚህ የበለጡ ሥራዎች ይሠራል” አላቸው። (ዮሐንስ 14:12) ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ እሱ ካከናወናቸው የላቁ ተአምራት እንደሚፈጽሙ መናገሩ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አገልግሎታቸውን ከእሱ አንጻር ለረጅም ጊዜና በጣም ሰፊ በሆነ ክልል ውስጥ እንደሚያከናውኑ እንዲሁም ለብዙ ሰዎች እንደሚሰብኩ መግለጹ ነው።

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ከተለየ በኋላ አይተዋቸውም፤ “ማንኛውንም ነገር በስሜ ከለመናችሁ እኔ አደርገዋለሁ” በማለት ቃል ገባላቸው። አክሎም “እኔም አብን እጠይቃለሁ፤ እሱም ለዘላለም ከእናንተ ጋር የሚሆን ሌላ ረዳት ይሰጣችኋል፤ እሱም የእውነት መንፈስ ነው” አለ። (ዮሐንስ 14:14, 16, 17) ኢየሱስ፣ ሌላ ረዳት የተባለውን መንፈስ ቅዱስን እንደሚቀበሉ ዋስትና ሰጣቸው። ይህን ረዳት የሚያገኙት በጴንጤቆስጤ ዕለት ነው።

ኢየሱስ “ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዓለም ከቶ አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ ምክንያቱም እኔ እኖራለሁ፤ እናንተም ትኖራላችሁ” በማለት ተናገረ። (ዮሐንስ 14:19) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ሰብዓዊ አካል ለብሶ ለእነሱ የሚገለጥላቸው ከመሆኑም በላይ ከጊዜ በኋላ ከሞት በማስነሳት መንፈሳዊ ፍጡራን ሆነው በሰማይ ከእሱ ጋር እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል።

ኢየሱስ በመቀጠል የሚከተለውን መሠረታዊ ሐቅ ተናገረ፦ “እኔን የሚወደኝ ትእዛዛቴን የሚቀበልና የሚጠብቅ ነው። እኔን የሚወደኝን ሁሉ ደግሞ አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ።” ታዴዎስ እየተባለም የሚጠራው ሐዋርያው ይሁዳ በዚህ ጊዜ “ጌታ ሆይ፣ ለዓለም ሳይሆን ለእኛ ራስህን ለመግለጥ ያሰብከው ለምንድን ነው?” በማለት ጠየቀው። ኢየሱስም “ማንም ሰው እኔን የሚወደኝ ከሆነ ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፣ . . . እኔን የማይወደኝ ሁሉ ቃሌን አይጠብቅም” በማለት መለሰለት። (ዮሐንስ 14:21-24) ከተከታዮቹ በተቃራኒ ዓለም፣ ኢየሱስ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት መሆኑን አይቀበልም።

ኢየሱስ ሊሄድ ነው፤ ታዲያ ደቀ መዛሙርቱ እሱ ያስተማራቸውን ነገር ሁሉ ማስታወስ የሚችሉት እንዴት ነው? ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “አብ በስሜ የሚልከው ረዳት ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ሁሉንም ነገር ያስተምራችኋል እንዲሁም የነገርኳችሁን ነገር ሁሉ እንድታስታውሱ ያደርጋችኋል።” ሐዋርያቱ፣ መንፈስ ቅዱስ ምን ያህል ኃይል እንዳለው ተመልክተዋል፤ በመሆኑም ይህ ማረጋገጫ ያጽናናቸዋል። ኢየሱስ አክሎም “ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ። . . . ልባችሁ አይረበሽ፤ በፍርሃትም አይዋጥ” አላቸው። (ዮሐንስ 14:26, 27) ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሱስ አባት መመሪያና ጥበቃ ስለሚያገኙ የሚረበሹበት ምክንያት የለም።

አምላክ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው የሚያሳይ ማስረጃ በቅርቡ ይመለከታሉ። ኢየሱስ “የዚህ ዓለም ገዢ እየመጣ” እንደሆነ ከተናገረ በኋላ “እሱም በእኔ ላይ ምንም ኃይል የለውም” አለ። (ዮሐንስ 14:30) ዲያብሎስ፣ ይሁዳ ውስጥ መግባትና እሱን መቆጣጠር ችሏል። ኢየሱስ ግን የኃጢአት ዝንባሌ ስለሌለው ሰይጣን በዚህ ተጠቅሞ በአምላክ ላይ ሊያሳምፀው አይችልም። ዲያብሎስ፣ ኢየሱስ ሞቶ እንዲቀር ማድረግም አይችልም። ለምን? ኢየሱስ “አብ ባዘዘኝ መሠረት እየሠራሁ ነው” አለ። በመሆኑም አባቱ ከሞት እንደሚያስነሳው እርግጠኛ ነው።—ዮሐንስ 14:31