በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 121

“አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ”

“አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ”

ዮሐንስ 16:1-33

  • ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር የሚቆየው ለጥቂት ጊዜ ነው

  • የሐዋርያቱ ሐዘን ወደ ደስታ ይለወጣል

ኢየሱስና ሐዋርያቱ ፋሲካን ከበሉበት በሰገነት ላይ የሚገኝ ክፍል ወጥተው ለመሄድ ተዘጋጅተዋል። ኢየሱስ ብዙ ምክር ከሰጣቸው በኋላ “ይህን ሁሉ የነገርኳችሁ እንዳትሰናከሉ ብዬ ነው” በማለት አክሎ ተናገረ። እንዲህ ዓይነት ማስጠንቀቂያ መስጠት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? እንዲህ አላቸው፦ “ሰዎች ከምኩራብ ያባርሯችኋል። እንዲያውም እናንተን የሚገድል ሁሉ ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት እንዳቀረበ አድርጎ የሚያስብበት ሰዓት ይመጣል።”—ዮሐንስ 16:1, 2

ሐዋርያቱ ይህን ሐሳብ ሲሰሙ ተረብሸው መሆን አለበት። ዓለም እንደሚጠላቸው ቀደም ሲል የነገራቸው ቢሆንም ሊገደሉ እንደሚችሉ በቀጥታ ገልጾ አያውቅም። ለምን? “ከእናንተ ጋር ስለነበርኩ እነዚህን ነገሮች በመጀመሪያ አልነገርኳችሁም” አላቸው። (ዮሐንስ 16:4) አሁን ግን ከእነሱ ሊለይ ስለሆነ ይህን መረጃ በመስጠት እያስታጠቃቸው ነው። ይህን ማድረጉ በኋላ ላይ እንዳይሰናከሉ ሊረዳቸው ይችላል።

ኢየሱስ ቀጥሎ “አሁን ግን ወደ ላከኝ ልሄድ ነው፤ ሆኖም ከመካከላችሁ ‘ወዴት ነው የምትሄደው?’ ብሎ የጠየቀኝ የለም” አላቸው። እርግጥ ነው፣ ወዴት እንደሚሄድ በዚሁ ምሽት ጥያቄ አቅርበውለት ነበር። (ዮሐንስ 13:36፤ 14:5፤ 16:5) በዚህ ወቅት ግን ስለ ስደት የተናገረው ሐሳብ ስላስደነገጣቸው በሐዘን ተውጠዋል። በመሆኑም ወደፊት ስለሚያገኘው ክብር ወይም ይህ ለእውነተኛ አገልጋዮች ምን ትርጉም እንደሚኖረው አልጠየቁትም። ኢየሱስ “እነዚህን ነገሮች ስለነገርኳችሁ ልባችሁ በሐዘን ተሞልቷል” አለ።—ዮሐንስ 16:6

ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “እኔ የምሄደው ለእናንተው ጥቅም ነው። ምክንያቱም እኔ ካልሄድኩ ረዳቱ በምንም ዓይነት ወደ እናንተ አይመጣም፤ ከሄድኩ ግን እሱን ወደ እናንተ እልከዋለሁ።” (ዮሐንስ 16:7) ደቀ መዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስን መቀበል የሚችሉት ኢየሱስ ከሞተና ወደ ሰማይ ከሄደ ብቻ ነው፤ ከዚያ በኋላ በየትኛውም የምድር ክፍል ለሚገኙ ተከታዮቹ ረዳት እንዲሆን የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ይልክላቸዋል።

መንፈስ ቅዱስ “ስለ ኃጢአት፣ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ ለዓለም አሳማኝ ማስረጃ ያቀርባል።” (ዮሐንስ 16:8) በእርግጥም ዓለም በአምላክ ልጅ አለማመኑ ይጋለጣል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ማረጉ፣ ጻድቅ እንደሆነ አሳማኝ ማስረጃ የሚያቀርብ ከመሆኑም ሌላ “የዚህ ዓለም ገዢ” የሆነው ሰይጣን ሊፈረድበት የሚገባው ለምን እንደሆነ ያሳያል።—ዮሐንስ 16:11

ኢየሱስ በመቀጠል “ገና ብዙ የምነግራችሁ ነገር አለኝ፤ አሁን ግን ልትሸከሙት አትችሉም” አለ። መንፈስ ቅዱስን ሲያፈስባቸው ይህ መንፈስ “ወደ እውነት ሁሉ” ይመራቸዋል፤ እነሱም በዚህ እውነት መሠረት መኖር ይችላሉ።—ዮሐንስ 16:12, 13

ኢየሱስ ቀጥሎ “ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ” ማለቱ ሐዋርያቱን ግራ አጋባቸው። ምን ማለቱ እንደሆነ እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። ኢየሱስም ስለዚህ ጉዳይ ሊጠይቁት እንደፈለጉ ስለተረዳ እንዲህ ሲል አብራራላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ እናንተ ታለቅሳላችሁ እንዲሁም ዋይ ዋይ ትላላችሁ፤ ዓለም ግን ይደሰታል፤ እናንተ ታዝናላችሁ፤ ሆኖም ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል።” (ዮሐንስ 16:16, 20) በማግስቱ ከሰዓት በኋላ ኢየሱስ ሲገደል የሃይማኖት መሪዎቹ ደስ ይላቸዋል፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ያዝናሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከሞት ሲነሳ ሐዘናቸው ወደ ደስታ ይለወጣል! የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ሲያፈስባቸው ደግሞ ይበልጥ ይደሰታሉ።

ኢየሱስ የሐዋርያቱን ሁኔታ በምጥ ላይ ካለች ሴት ጋር በማነጻጸር እንዲህ አለ፦ “አንዲት ሴት የመውለጃዋ ሰዓት ደርሶ ስታምጥ ትጨነቃለች፤ ሕፃኑን ከወለደች በኋላ ግን አንድ ሰው ወደ ዓለም በመምጣቱ ከደስታዋ የተነሳ ሥቃይዋን ሁሉ ትረሳለች።” ከዚያም እንደሚከተለው በማለት ሐዋርያቱን አበረታታቸው፦ “እናንተም አሁን አዝናችኋል፤ ሆኖም እንደገና ስለማያችሁ ልባችሁ በደስታ ይሞላል፤ ደስታችሁን ደግሞ ማንም አይነጥቃችሁም።”—ዮሐንስ 16:21, 22

እስከዚህ ጊዜ ድረስ ሐዋርያቱ በኢየሱስ ስም ልመና አቅርበው አያውቁም። አሁን ግን “በዚያ ቀን አብን በስሜ ትለምናላችሁ” አላቸው። ይህን ሲል አብ መልስ ሊሰጣቸው ፈቃደኛ እንዳልሆነ መግለጹ ነው? አይደለም። እንዲያውም ኢየሱስ “እናንተ እኔን ስለወደዳችሁኝና የአምላክ ተወካይ ሆኜ እንደመጣሁ ስላመናችሁ አብ ራሱ ይወዳችኋል” አላቸው።—ዮሐንስ 16:26, 27

ኢየሱስ ለሐዋርያቱ የሰጣቸው ማበረታቻ ድፍረት እንዲያገኙ ሳይረዳቸው አልቀረም፤ በመሆኑም “ከአምላክ ዘንድ እንደመጣህ እናምናለን” አሉት። ይህ እምነታቸው በቅርቡ ይፈተናል። ኢየሱስ ብዙም ሳይቆይ ምን እንደሚያጋጥማቸው ሲገልጽ “እነሆ፣ ሁላችሁም ወደየቤታችሁ የምትበታተኑበትና እኔን ብቻዬን ትታችሁ የምትሄዱበት ሰዓት ቀርቧል” አለ። ይሁንና የሚከተለውን ማረጋገጫ ሰጣቸው፦ “እነዚህን ነገሮች የነገርኳችሁ በእኔ አማካኝነት ሰላም እንዲኖራችሁ ነው። በዓለም ሳላችሁ መከራ ይደርስባችኋል፤ ነገር ግን አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” (ዮሐንስ 16:30-33) ኢየሱስ ሐዋርያቱን ይተዋቸዋል ማለት አይደለም። እሱ ዓለምን እንዳሸነፈው ሁሉ እነሱም ዓለምን ማሸነፍ እንደሚችሉ እርግጠኛ ነው፤ ሐዋርያቱ፣ ዓለምን የሚያሸንፉት ሰይጣንና የእሱ ዓለም ንጹሕ አቋማቸውን እንዲያጎድፉ ለማድረግ ቢሞክሩም እነሱ የአምላክን ፈቃድ በታማኝነት በመፈጸም ነው።