በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 132

“ይህ በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነበር”

“ይህ በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነበር”

ማቴዎስ 27:45-56 ማርቆስ 15:33-41 ሉቃስ 23:44-49 ዮሐንስ 19:25-30

  • ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ሞተ

  • ኢየሱስ ሲሞት የተፈጸሙ እንግዳ ክንውኖች

አሁን ከቀኑ “ስድስት ሰዓት” ሆኗል። “አገሩ በሙሉ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በጨለማ ተሸፈነ።” (ማርቆስ 15:33) እንግዳ የሆነውና ጭንቅ የሚለው ይህ ጨለማ የተከሰተው በፀሐይ ግርዶሽ ሳቢያ አይደለም። ምክንያቱም የፀሐይ ግርዶሽ የሚፈጠረው አዲስ ጨረቃ በምትኖርበት ጊዜ ነው፤ አሁን የፋሲካ ወቅት ሲሆን በዚህ ጊዜ ደግሞ ጨረቃ ሙሉ ነች። ከዚህም ሌላ ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ከሚቆየው የፀሐይ ግርዶሽ በተለየ ይህ ጨለማ የቆየው ረዘም ላለ ጊዜ ነው። ስለዚህ ምድሪቱ በጨለማ እንድትሸፈን ያደረገው አምላክ ነው!

በኢየሱስ ላይ ሲያላግጡ የቆዩት ሰዎች በዚህ ወቅት ምን እንደሚሰማቸው አስበው። አካባቢው በጨለማ በተሸፈነበት ሰዓት አራት ሴቶች ወደ መከራ እንጨቱ ቀረቡ። እነሱም የኢየሱስ እናት፣ ሰሎሜ፣ መግደላዊቷ ማርያምና የትንሹ ያዕቆብ እናት የሆነችው ማርያም ናቸው።

ሐዋርያው ዮሐንስ በሐዘን ከተደቆሰችው የኢየሱስ እናት ጋር ሆኖ ‘በመከራው እንጨት አጠገብ’ ቆሟል። ማርያም ወልዳና ተንከባክባ ያሳደገችው ልጇ ተሰቅሎ ሲሠቃይ እየተመለከተች ነው። በዚህ ወቅት “ትልቅ ሰይፍ” በውስጧ ያለፈ ያህል ተሰምቷት መሆን አለበት። (ዮሐንስ 19:25፤ ሉቃስ 2:35) ኢየሱስ በከፍተኛ ሥቃይ ላይ ቢሆንም የእናቱ ነገር አሳስቦታል። እንደምንም ተጣጥሮ በጭንቅላቱ ወደ ዮሐንስ በማመልከት እናቱን “ልጅሽ ይኸውልሽ!” አላት። ከዚያም ወደ ማርያም በመጠቆም ዮሐንስን “እናትህ ይህችውልህ!” አለው።—ዮሐንስ 19:26, 27

በዚህ መንገድ ኢየሱስ፣ እናቱን እንዲንከባከባት ይበልጥ ለሚወደው ሐዋርያ በአደራ ሰጠው፤ በዚህ ወቅት ማርያም መበለት ሳትሆን አትቀርም። ኢየሱስ፣ ወንድሞቹ ይኸውም የማርያም ሌሎች ልጆች በእሱ ገና እንዳላመኑ ያውቃል። በመሆኑም የእናቱ ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ፍላጎትም እንዲሟላ ዝግጅት እያደረገ ነው። ይህ እንዴት ያለ ጥሩ ምሳሌ ነው!

ጨለማው ሊገፈፍ አካባቢ ኢየሱስ “ተጠማሁ” አለ። ይህን ሲል የቅዱስ መጽሐፉ ቃል እንዲፈጸም እያደረገ ነው። (ዮሐንስ 19:28፤ መዝሙር 22:15) ኢየሱስ፣ ንጹሕ አቋሙ እስከ መጨረሻ ድረስ እንዲፈተን አባቱ ጥበቃውን ከእሱ ላይ እንዳነሳ ሆኖ ተሰምቶታል። ክርስቶስ “ኤሊ፣ ኤሊ፣ ላማ ሳባቅታኒ?” ብሎ ጮኸ፤ ትርጉሙም “አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው። ኢየሱስ የተናገረው በገሊላ በሚነገር የአረማይክ ቋንቋ ሊሆን ይችላል። በአቅራቢያው የቆሙት ሰዎች ምን ማለቱ እንደሆነ ግልጽ ስላልሆነላቸው “አያችሁ! ኤልያስን እየተጣራ ነው” አሉ። ከመካከላቸው አንዱ ሮጦ በመሄድ የኮመጠጠ የወይን ጠጅ ውስጥ ሰፍነግ ከነከረ በኋላ በመቃ ላይ አድርጎ እንዲጠጣ ለኢየሱስ ሰጠው። ሌሎች ግን “ተዉት! እስቲ ኤልያስ መጥቶ ያወርደው እንደሆነ እንይ” አሉ።—ማርቆስ 15:34-36

ከዚያም ኢየሱስ “ተፈጸመ!” ብሎ ጮኸ። (ዮሐንስ 19:30) አዎን፣ አባቱ ወደ ምድር ሲልከው እንዲያከናውነው የሰጠውን ሥራ ሁሉ ፈጽሟል። በመጨረሻም ኢየሱስ “አባት ሆይ፣ መንፈሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” አለ። (ሉቃስ 23:46) በዚህ መንገድ ኢየሱስ የሕይወቱን ኃይል ለይሖዋ ሰጠ፤ ይህን ያደረገው አምላክ እንደገና መልሶ እንደሚሰጠው እርግጠኛ ሆኖ ነው። ከዚያም ክርስቶስ በአምላክ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ራሱን ዘንበል አድርጎ ሞተ።

በዚህ ጊዜ ኃይለኛ የምድር መናወጥ ተከሰተ፤ ዓለቶችም ተሰነጣጠቁ። የምድር መናወጡ በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ከኢየሩሳሌም ውጭ ያሉ መቃብሮች ተከፈቱ፤ አስከሬኖችም ከመቃብሩ ውስጥ ተስፈንጥረው ወጡ። በዚያ የሚያልፉ ሰዎች አስከሬኖቹን ሲያዩ ወደ “ቅድስቲቱ ከተማ” ገብተው የተመለከቱትን ነገር አወሩ።—ማቴዎስ 12:11፤ 27:51-53

ኢየሱስ ሲሞት፣ በአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ ቅድስቱን ከቅድስተ ቅዱሳኑ የሚለየው ትልቅና ወፍራም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ። ይህ አስደናቂ ክንውን አምላክ፣ ልጁን በገደሉት ሰዎች ላይ የተሰማውን ቁጣ ይገልጻል፤ ከዚህም ሌላ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ማለትም ወደ ሰማይ የሚያስገባው መንገድ እንደተከፈተ ያመለክታል።—ዕብራውያን 9:2, 3፤ 10:19, 20

ሰዎቹ ታላቅ ፍርሃት ያደረባቸው መሆኑ የሚያስገርም አይደለም። ግድያውን እንዲያስፈጽም ኃላፊነት የተሰጠው መኮንን “ይህ ሰው በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነበር” አለ። (ማርቆስ 15:39) ይህ መኮንን፣ በጲላጦስ ፊት በተካሄደው ችሎት ላይ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ስለ መሆኑ በተጠየቀበት ወቅት በቦታው ኖሮ ሊሆን ይችላል። አሁን ኢየሱስ ጻድቅ እንደሆነ አልፎ ተርፎም የአምላክ ልጅ እንደሆነ አመነ።

በእነዚህ ያልተለመዱ ክንውኖች ስሜታቸው የተጎዳ ሌሎች ሰዎች የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘንና ኀፍረት ለመግለጽ “ደረታቸውን እየደቁ ወደ ቤታቸው ተመለሱ።” (ሉቃስ 23:48) በርቀት ሆነው ከሚመለከቱት መካከል አንዳንድ ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ይጓዙ የነበሩ በርካታ ሴት ደቀ መዛሙርት ይገኙበታል። እነሱም በእነዚህ አስገራሚ ክንውኖች ስሜታቸው በጥልቅ ተነክቷል።