በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 70

ሲወለድ ጀምሮ ዓይነ ስውር የሆነን ሰው ፈወሰ

ሲወለድ ጀምሮ ዓይነ ስውር የሆነን ሰው ፈወሰ

ዮሐንስ 9:1-18

  • ሲወለድ ጀምሮ ዓይነ ስውር የሆነ ለማኝ ተፈወሰ

ቀኑ ሰንበት ሲሆን ኢየሱስ አሁንም ኢየሩሳሌም ነው። ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በከተማዋ ውስጥ እየተዘዋወሩ እያለ፣ ሲወለድ ጀምሮ ዓይነ ስውር የሆነ ለማኝ ተመለከቱ። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን “ረቢ፣ ይህ ሰው ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደው ማን በሠራው ኃጢአት ነው? በራሱ ኃጢአት ነው ወይስ በወላጆቹ?” ሲሉ ጠየቁት።—ዮሐንስ 9:2

ደቀ መዛሙርቱ፣ ‘አንድ ሰው በእናቱ ማህፀን ውስጥ ሳለ ኃጢአት ሊሠራ ይችል ይሆን?’ ብለው አስበው ይሆናል። ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እሱም ሆነ ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም፤ ሆኖም ይህ የሆነው የአምላክ ሥራ በእሱ እንዲገለጥ ነው።” (ዮሐንስ 9:3) ስለዚህ ሰውየው ዓይነ ስውር የሆነው እሱ አሊያም ወላጆቹ ስህተት በመሥራታቸው ወይም ኃጢአት በመፈጸማቸው አይደለም። አዳም በሠራው ኃጢአት የተነሳ ሁሉም ሰዎች ሲወለዱ ጀምሮ ፍጹማን አይደሉም፤ በመሆኑም እንደ ዓይነ ስውርነት ላሉ እክሎች የተጋለጡ ናቸው። ሆኖም ሰውየው ዓይነ ስውር መሆኑ፣ ኢየሱስ ከዚህ በፊት የታመሙ ሰዎችን በመፈወስ እንዳደረገው ሁሉ አሁንም የአምላክን ሥራ መግለጥ እንዲችል አጋጣሚ ከፍቷል።

ኢየሱስ ይህን ሥራ የማከናወኑን አጣዳፊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “ቀን ሳለ፣ የላከኝን የእሱን ሥራ መሥራት አለብን፤ ማንም ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት ይመጣል። በዓለም እስካለሁ ድረስ የዓለም ብርሃን ነኝ።” (ዮሐንስ 9:4, 5) ኢየሱስ በቅርቡ ሲሞት፣ ምንም ማድረግ ወደማይችልበት የመቃብር ጨለማ ውስጥ ይገባል። እስከዚያው ድረስ ግን ለዓለም የብርሃን ምንጭ ነው።

ይሁንና ኢየሱስ ሰውየውን ይፈውሰው ይሆን? ከሆነስ እንዴት? ኢየሱስ መሬት ላይ እንትፍ በማለት በምራቁ ጭቃ ለወሰ። ከዚያም ጭቃውን በሰውየው ዓይኖች ላይ ከቀባ በኋላ “ሄደህ በሰሊሆም ገንዳ ታጠብ” አለው። (ዮሐንስ 9:7) ሰውየው የታዘዘውን አደረገ። ሄዶ ሲታጠብም ዓይኑ በራ! በሕይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ማየት በመቻሉ ምንኛ ተደስቶ እንደሚሆን አስበው!

ጎረቤቶቹና ዓይነ ስውር እያለ የሚያውቁት ሰዎች ሲያዩት ተገረሙ። “ይህ ሰው ተቀምጦ ይለምን የነበረው አይደለም እንዴ?” አሉ። አንዳንዶች “አዎ፣ እሱ ነው” ሲሉ ሌሎች ግን ሊያምኑ ስላልቻሉ “አይ፣ እሱን ይመስላል እንጂ እሱ አይደለም” ብለው መለሱ። ሰውየው ግን “እኔው ነኝ” አላቸው።—ዮሐንስ 9:8, 9

እነሱም “ታዲያ ዓይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” ሲሉ ጠየቁት። እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ኢየሱስ የተባለው ሰው ጭቃ ለውሶ ዓይኖቼን ቀባና ‘ወደ ሰሊሆም ሄደህ ታጠብ’ አለኝ። እኔም ሄጄ ታጠብኩ፤ ዓይኔም በራልኝ።” በዚህ ጊዜ “ሰውየው የት አለ?” ብለው ጠየቁት። ለማኙም “እኔ አላውቅም” ሲል መለሰ።—ዮሐንስ 9:10-12

ሰዎቹ ዓይነ ስውር የነበረውን ለማኝ ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት፤ እነሱም እንዴት ማየት እንደቻለ ጠየቁት። “ሰውየው ዓይኖቼን ጭቃ ቀባ፤ እኔም ታጠብኩ፤ ከዚያም ማየት ቻልኩ” አላቸው። ፈሪሳውያኑ ከተፈወሰው ለማኝ ጋር አብረው ሊደሰቱ እንደሚገባ የታወቀ ነው። ሆኖም በዚያ ፋንታ አንዳንዶቹ ኢየሱስን አወገዙት። “ይህ ሰው ሰንበትን ስለማያከብር ከአምላክ የመጣ አይደለም” አሉ። ሌሎቹ ደግሞ “ኃጢአተኛ የሆነ ሰው እንዲህ ያሉ ተአምራዊ ምልክቶችን እንዴት ሊፈጽም ይችላል?” በማለት ጠየቁ። (ዮሐንስ 9:15, 16) በመሆኑም በመካከላቸው ክፍፍል ተፈጠረ።

በጉዳዩ ላይ ስላልተስማሙ ዓይኑ የበራለትን ሰው “ይህ ሰው ዓይኖችህን ስላበራልህ ስለ እሱ ምን ትላለህ?” ብለው ጠየቁት። ሰውየው ስለ ኢየሱስ ማንነት እርግጠኛ በመሆኑ “እሱ ነቢይ ነው” በማለት መለሰ።—ዮሐንስ 9:17

ፈሪሳውያኑ ይህን ማመን አልፈለጉም። ኢየሱስና ይህ ሰው ሕዝቡን ለማታለል የዶለቱት ነገር እንዳለ አስበው ይሆናል። በመሆኑም የሰውየውን ወላጆች በእርግጥ ልጃቸው ዓይነ ስውር እንደነበር በመጠየቅ ለጉዳዩ እልባት ማግኘት እንደሚቻል ተሰማቸው።