በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ አራት

ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?

1, 2. (ሀ) የአንድን ታዋቂ ሰው ስም ታውቃለህ ማለት ግለሰቡን በሚገባ ታውቀዋለህ ማለት ነው? አብራራ። (ለ) ሰዎች ስለ ኢየሱስ ምን ይላሉ?

በዓለም ላይ ብዙ ታዋቂ ሰዎች አሉ። አንተም የአንድ ታዋቂ ሰው ስም ታውቅ ይሆናል። የዚህን ሰው ስም ታውቃለህ ማለት ግን ግለሰቡን በደንብ ታውቀዋለህ ማለት አይደለም። ስለ ግለሰቡ ሕይወትም ሆነ ስለ ባሕርይው በሚገባ ላታውቅ ትችላለህ።

2 ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ የኖረው ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ቢሆንም እንኳ ስለ እሱ ሳትሰማ አትቀርም። ይሁንና ብዙ ሰዎች ስለ ኢየሱስ ማንነት ምንም አያውቁም። አንዳንድ ሰዎች በአንድ ወቅት የኖረ ጥሩ ሰው እንደሆነ፣ አንዳንዶች ደግሞ ነቢይ እንደሆነ ይናገራሉ፤ ሌሎች ደግሞ እግዚአብሔር ነው ይላሉ። አንተስ ምን ትላለህ?—ተጨማሪ ሐሳብ 12⁠ን ተመልከት።

3. ይሖዋ አምላክንና ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

3 ስለ ኢየሱስ እውነቱን ማወቅህ አስፈላጊ ነው። ለምን? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ አለባቸው።” (ዮሐንስ 17:3) ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ እውነቱን ካወቅክ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም መኖር ትችላለህ። (ዮሐንስ 14:6) በተጨማሪም ስለ ኢየሱስ ሕይወትና ለሌሎች ያሳይ ስለነበረው ባሕርይ ማወቅህ አንተም የእሱን ምሳሌ እንድትከተል ይረዳሃል። (ዮሐንስ 13:34, 35) ምዕራፍ 1 ላይ ስለ አምላክ እውነቱን ተምረናል። አሁን ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ምን እንደሚያስተምር እንመለከታለን።

መሲሑን አገኘነው!

4. “መሲሕ” እና “ክርስቶስ” የሚሉት ቃላት ምን ያሳያሉ?

4 ኢየሱስ ከመወለዱ ከብዙ ዓመታት በፊት ይሖዋ መሲሑን ወይም ክርስቶስን እንደሚልክ ቃል ገብቶ ነበር። “መሲሕ” የሚለው ቃል ከዕብራይስጥ የተወሰደ ሲሆን “ክርስቶስ” የሚለው ቃል ደግሞ ከግሪክኛ የተወሰደ ነው። ሁለቱም የማዕረግ ስሞች፣ አምላክ መሲሕ እንደሚመርጥና ልዩ ኃላፊነት እንደሚሰጠው ያሳያሉ። መሲሑ፣ አምላክ ቃል የገባቸው ነገሮች በሙሉ እንዲፈጸሙ ያደርጋል። ይሁንና ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት ብዙ ሰዎች ‘መሲሑ ማን ይሆን?’ የሚል ጥያቄ ያነሱ ነበር።

5. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስን በተመለከተ ምን ተረድተው ነበር?

5 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት፣ ኢየሱስ አስቀድሞ በትንቢት የተነገረለት መሲሕ እንደሆነ ተረድተው ነበር። (ዮሐንስ 1:41) ለምሳሌ ስምዖን ጴጥሮስ፣ ኢየሱስን “አንተ ክርስቶስ . . . ነህ” ብሎት ነበር። (ማቴዎስ 16:16) ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነ በእርግጠኝነት ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

6. ይሖዋ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የመሲሑን ማንነት እንዲያውቁ የረዳቸው እንዴት ነው?

6 ኢየሱስ ከመወለዱ ከረጅም ጊዜ በፊት የአምላክ ነቢያት የመሲሑን ማንነት ለማወቅ የሚረዱ ዝርዝር መረጃዎችን ጽፈዋል። እነዚህ መረጃዎች መሲሑን ለይቶ ለማወቅ የሚረዱት እንዴት ነው? ሰው ወደሚበዛበት የአውቶቡስ መናኸሪያ ሄደህ የማታውቀውን ሰው እንድትቀበል ተነገረህ እንበል። አንድ ሰው፣ ስለምትቀበለው ግለሰብ ዝርዝር መረጃ ቢሰጥህ ይህን ሰው በቀላሉ ልትለየው ትችላለህ። በተመሳሳይም ይሖዋ፣ መሲሑ ስለሚያደርጋቸውና ስለሚያጋጥሙት ነገሮች በትንቢት ተናግሯል። እነዚህ ትንቢቶች መፈጸማቸው ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነ ማወቅ እንዲችሉ ረድቷቸዋል።

7. ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነ የሚያረጋግጡት ሁለት ትንቢቶች የትኞቹ ናቸው?

7 ከእነዚህ ትንቢቶች መካከል ሁለቱን እንመልከት። አንደኛው፣ ኢየሱስ ከመወለዱ ከ700 ዓመት በፊት ሚክያስ የተናገረው ትንቢት ነው፤ ነቢዩ ሚክያስ፣ መሲሑ ቤተልሔም ተብላ በምትጠራ ትንሽ ከተማ ውስጥ እንደሚወለድ ተናግሮ ነበር። (ሚክያስ 5:2) ኢየሱስ የተወለደውም በዚህች ከተማ ውስጥ ነው! (ማቴዎስ 2:1, 3-9) ሁለተኛው ደግሞ ዳንኤል መሲሑ በ29 ዓ.ም. እንደሚገለጥ ወይም በይፋ እንደሚታወቅ የተናገረው ትንቢት ነው። (ዳንኤል 9:25) ኢየሱስ አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ እንደሆነ በግልጽ የሚያሳዩ ሌሎች ብዙ ትንቢቶችም አሉ።—ተጨማሪ ሐሳብ 13⁠ን ተመልከት።

ኢየሱስ በተጠመቀበት ጊዜ መሲሕ ወይም ክርስቶስ ሆኗል

8, 9. ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጥ ምን ነገር ተከናውኗል?

8 ይሖዋ የኢየሱስን መሲሕነት የሚያረጋግጥ ነገር አድርጓል። አጥማቂው ዮሐንስ መሲሑ ማን እንደሆነ ማወቅ እንዲችል ምልክት እንደሚያሳየው ይሖዋ ቃል ገብቶለት ነበር። በ29 ዓ.ም. ዮሐንስ ኢየሱስን በዮርዳኖስ ወንዝ ባጠመቀበት ጊዜ ይህን ምልክት ማየት ችሏል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃው ወጣ፤ እነሆ፣ ሰማያት ተከፈቱ፤ የአምላክም መንፈስ በእሱ ላይ እንደ ርግብ ሲወርድ አየ። ደግሞም ‘በእሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው’ የሚል ድምፅ ከሰማያት ተሰማ።” (ማቴዎስ 3:16, 17) ዮሐንስ ይህን ምልክት ሲያይና ሲሰማ ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ችሏል። (ዮሐንስ 1:32-34) በዚያ ዕለት ይሖዋ መንፈሱን በኢየሱስ ላይ ሲያፈስ ኢየሱስ መሲሕ ሆነ። አምላክ ኢየሱስን ንጉሥና መሪ እንዲሆን መርጦታል።—ኢሳይያስ 55:4

9 የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እንዲሁም ይሖዋ ራሱ የተናገረው ነገርና ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት የታየው ምልክት ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነ ያረጋግጣሉ። ይሁንና ኢየሱስ የመጣው ከየት ነው? ደግሞስ ምን ዓይነት ሰው ነበር? እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ እንመልከት።

ኢየሱስ የመጣው ከየት ነው?

10. ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ስለነበረው ሕይወት መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

10 ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ለብዙ ዘመናት በሰማይ እንደኖረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ሚክያስ፣ መሲሑ “ምንጩ ከጥንት” እንደሆነ ተናግሮ ነበር። (ሚክያስ 5:2) ኢየሱስ ራሱ፣ ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት በሰማይ ይኖር እንደነበር በተደጋጋሚ ጊዜ ተናግሯል። (ዮሐንስ 3:13⁠ን፤ 6:38, 62⁠ን እና 17:4, 5ን አንብብ።) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊትም እንኳ ከይሖዋ ጋር ልዩ ዝምድና ነበረው።

11. ይሖዋ ኢየሱስን በጣም ይወደዋል የምንለው ለምንድን ነው?

11 ይሖዋ ኢየሱስን በጣም ይወደዋል። ምክንያቱም አምላክ ከሁሉ በፊት የፈጠረው ኢየሱስን ነው። በመሆኑም ኢየሱስ “የፍጥረት ሁሉ በኩር” ተብሎ ተጠርቷል። * (ቆላስይስ 1:15) በተጨማሪም ይሖዋ በቀጥታ የፈጠረው እሱን ብቻ በመሆኑ በጣም ይወደዋል። “አንድያ ልጁ” ተብሎ የተጠራውም ለዚህ ነው። (ዮሐንስ 3:16) ከዚህም ሌላ አምላክ ሌሎች ነገሮችን ሁሉ ለመፍጠር የተጠቀመው በኢየሱስ ነው። (ቆላስይስ 1:16) ደግሞም ይሖዋ ለመላእክትም ሆነ ለሰው ልጆች መልእክትና መመሪያ ለማስተላለፍ ስለተጠቀመበት ‘ቃል’ ተብሎ የተጠራው ኢየሱስ ብቻ ነው።—ዮሐንስ 1:14

12. ኢየሱስና አምላክ እኩል እንዳልሆኑ እንዴት እናውቃለን?

12 አንዳንድ ሰዎች ‘ኢየሱስና እግዚአብሔር እኩል ናቸው’ ይላሉ። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ አያስተምርም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ኢየሱስን እንደፈጠረው ስለሚናገር ኢየሱስ መጀመሪያ አለው። የሁሉም ነገር ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ ግን መጀመሪያ የለውም። (መዝሙር 90:2) የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ከአምላክ ጋር እኩል ለመሆን አስቦ አያውቅም። መጽሐፍ ቅዱስ አብ ከወልድ እንደሚበልጥ በግልጽ ይናገራል። (ዮሐንስ 14:28ን አንብብ፤ 1 ቆሮንቶስ 11:3) “ሁሉን ቻይ አምላክ” ይሖዋ ብቻ ነው። (ዘፍጥረት 17:1) በጽንፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የበለጠ ሥልጣንና ኃይል ያለው እሱ ነው።—ተጨማሪ ሐሳብ 14⁠ን ተመልከት።

13. መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “የማይታየው አምላክ አምሳል” ብሎ የሚጠራው ለምንድን ነው?

13 ይሖዋና ልጁ ኢየሱስ፣ ሰማይና ምድር ከመፈጠራቸው በፊት ለረጅም ዓመታት አብረው ሠርተዋል። እርስ በርስ በጣም ይዋደዳሉ! (ዮሐንስ 3:35፤ 14:31) ኢየሱስ የአባቱን ባሕርያት በማሳየት ሙሉ በሙሉ እሱን በመምሰሉ መጽሐፍ ቅዱስ “የማይታየው አምላክ አምሳል” በማለት ይጠራዋል።—ቆላስይስ 1:15

14. ኢየሱስ ሰው ሆኖ ሊወለድ የቻለው እንዴት ነው?

14 የይሖዋ ተወዳጅ ልጅ የሆነው ኢየሱስ፣ በሰማይ ያለውን ቦታ ትቶ ወደ ምድር ለመምጣትና ሰው ሆኖ ለመወለድ ፈቃደኛ ሆኗል። ኢየሱስ ሰው ሆኖ ሊወለድ የቻለው እንዴት ነው? ይሖዋ የልጁን ሕይወት ማርያም ወደተባለች አንዲት ድንግል ማህፀን ተአምራዊ በሆነ መንገድ አዛወረው። በመሆኑም ኢየሱስ የተወለደው ከሰብዓዊ አባት አይደለም። ስለዚህ ማርያም ኃጢአት የሌለበት ፍጹም ልጅ የወለደች ሲሆን ስሙንም ኢየሱስ ብላ ጠራችው።—ሉቃስ 1:30-35

ኢየሱስ ምን ዓይነት ሰው ነበር?

15. ስለ ይሖዋ ይበልጥ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

15 የማቴዎስን፣ የማርቆስን፣ የሉቃስንና የዮሐንስን መጻሕፍት በማንበብ ስለ ኢየሱስ፣ ስለ ሕይወቱና ስለ ባሕርያቱ ብዙ ትምህርት ማግኘት ትችላለህ። እነዚህ መጻሕፍት ወንጌሎች በመባል ይታወቃሉ። ኢየሱስ ልክ እንደ አባቱ ስለሆነ ስለ ኢየሱስ የምታነበው ነገር ስለ ይሖዋ ይበልጥ እንድታውቅ ይረዳሃል። ኢየሱስ “እኔን ያየ ሁሉ አብንም አይቷል” ያለው ለዚህ ነው።—ዮሐንስ 14:9

16. ኢየሱስ ካስተማራቸው ትምህርቶች አንዱ ምንድን ነው? ኢየሱስ ያስተማረው የማንን ትምህርት ነው?

16 ብዙ ሰዎች ኢየሱስን “መምህር” በማለት ይጠሩት ነበር። (ዮሐንስ 1:38፤ 13:13) ኢየሱስ ካስተማራቸው በጣም አስፈላጊ ትምህርቶች አንዱ ‘የመንግሥቱ ምሥራች’ ነው። ይህ መንግሥት ምንድን ነው? ከሰማይ ሆኖ መላውን ምድር የሚገዛ የአምላክ መስተዳድር ነው፤ ይህ መንግሥት አምላክን ለሚታዘዙ ሰዎች በረከት ያመጣል። (ማቴዎስ 4:23) ኢየሱስ ያስተማረው ከአባቱ የተማረውን ነው። “የማስተምረው ትምህርት የራሴ ሳይሆን ከላከኝ የመጣ ነው” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 7:16) ኢየሱስ የአባቱን ፍላጎት ስለሚያውቅ የአምላክ መንግሥት መላውን ምድር እንደሚገዛ የሚገልጸውን ምሥራች ለሰው ልጆች አስተምሯል።

17. ኢየሱስ ያስተምር የነበረው የት ነው? ኢየሱስ ሌሎችን ለማስተማር ከፍተኛ ጥረት ያደረገው ለምንድን ነው?

17 ኢየሱስ ያስተምር የነበረው የት ነው? ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ አስተምሯል። በገጠራማ አካባቢዎች፣ በከተሞች፣ በመንደሮች፣ በገበያ ቦታዎች፣ በአምልኮ ቦታዎችና በመኖሪያ ቤቶች ውስጥ ያስተምር ነበር። ሰዎች እሱ ወዳለበት እስኪመጡ ድረስ ከመጠበቅ ይልቅ አብዛኛውን ጊዜ እነሱ ወዳሉበት ይሄድ ነበር። (ማርቆስ 6:56፤ ሉቃስ 19:5, 6) ኢየሱስ ጊዜውንና ጉልበቱን ሳይቆጥብ በትጋት ሰዎችን አስተምሯል። እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው? አምላክ እንዲህ እንዲያደርግ ይፈልግ ስለነበር ነው፤ ኢየሱስ ደግሞ ምንጊዜም አባቱን ይታዘዛል። (ዮሐንስ 8:28, 29) ኢየሱስ ይሰብክ የነበረበት ሌላው ምክንያት ለሰዎች ያዝን ስለነበር ነው። (ማቴዎስ 9:35, 36ን አንብብ።) የሃይማኖት መሪዎቹ ስለ አምላክም ሆነ ስለ መንግሥቱ እውነቱን እንደማያስተምሩ ያውቃል። በመሆኑም በተቻለው መጠን ብዙ ሰዎች ምሥራቹን እንዲሰሙ ይፈልግ ነበር።

ኢየሱስ ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ይሰብክ ነበር

18. ከኢየሱስ ባሕርያት መካከል በጣም የምትወደው የትኞቹን ነው?

18 ኢየሱስ ሰዎችን ይወድ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ያስብላቸው ነበር። ደግና በቀላሉ የሚቀረብ ሰው ነበር። ልጆችም እንኳ ከእሱ ጋር መሆን ያስደስታቸዋል። (ማርቆስ 10:13-16) ኢየሱስ ምንጊዜም ፍትሐዊ ነው። ሙስናንና ግፍን ይጠላል። (ማቴዎስ 21:12, 13) ኢየሱስ ምድር ላይ በኖረበት ጊዜ ሴቶች ምንም መብት አልነበራቸውም፤ ሰዎች ይንቋቸው ነበር። ኢየሱስ ግን ለሴቶች አክብሮት ነበረው። (ዮሐንስ 4:9, 27) በተጨማሪም ኢየሱስ በጣም ትሑት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት የሐዋርያቱን እግር አጥቧል፤ ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ ይህን ሥራ የሚሠሩት የቤት አገልጋዮች ነበሩ።—ዮሐንስ 13:2-5, 12-17

19. ኢየሱስ ሰዎችን ለመርዳት ይፈልግ እንደነበር የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።

19 ኢየሱስ የሰዎችን ችግር ያውቅ ስለነበር እነሱን ለመርዳት ጥረት አድርጓል። አምላክ የሰጠውን ኃይል ተጠቅሞ ሰዎችን ተአምራዊ በሆነ መንገድ መፈወሱ ይህን በግልጽ ያሳያል። (ማቴዎስ 14:14) ለምሳሌ ያህል፣ በሥጋ ደዌ የተያዘ አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” ብሎት ነበር። ኢየሱስ የዚህን ሰው ሥቃይ ሲመለከት በጣም አዘነ። በመሆኑም ሰውየውን ሊረዳው ፈለገ። ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ከዳሰሰው በኋላ “እፈልጋለሁ! ንጻ” አለው። የታመመው ሰው ወዲያውኑ ተፈወሰ! (ማርቆስ 1:40-42) ይህ ሰው ምን ያህል ተደስቶ ሊሆን እንደሚችል መገመት ትችላለህ!

ምንጊዜም ለአባቱ ታማኝ ነው

20, 21. ኢየሱስ አምላክን በመታዘዝ ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

20 ኢየሱስ አምላክን በመታዘዝ ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ትቷል። ኢየሱስ ጠላቶቹ የፈጸሙበትን በደል ጨምሮ ብዙ ነገር ቢደርስበትም ለአባቱ ታማኝ ሆኗል። ለምሳሌ ሰይጣን በፈተነው ጊዜ ምንም ኃጢአት አልሠራም። (ማቴዎስ 4:1-11) ከቤተሰቡ አባላት መካከል አንዳንዶቹ እሱ መሲሕ እንደሆነ አያምኑም ነበር፤ እንዲያውም “አእምሮውን ስቷል” በማለት ይናገሩ ነበር፤ ሆኖም ኢየሱስ አምላክ የሰጠውን ሥራ መሥራቱን ቀጥሏል። (ማርቆስ 3:21) ኢየሱስ ጠላቶቹ የጭካኔ ድርጊት ቢፈጽሙበትም ለአምላክ ታማኝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በእነሱ ላይ ጉዳት ለማድረስ አልሞከረም።—1 ጴጥሮስ 2:21-23

21 ኢየሱስ ብዙ ሥቃይ ደርሶበት በግፍ በተገደለበት ወቅትም እንኳ ለይሖዋ ታማኝ ሆኗል። (ፊልጵስዩስ 2:8ን አንብብ።) ኢየሱስ በሞተበት ዕለት ምን ያህል ሥቃይ እንደደረሰበት እስቲ ለማሰብ ሞክር። ከታሰረ በኋላ የሐሰት ምሥክሮች አምላክን ሰድቧል የሚል ክስ ሰነዘሩበት፤ ምግባረ ብልሹ የሆኑ ዳኞች በሐሰት ፈረዱበት፤ ሕዝቡ አሾፈበት፤ ወታደሮቹም ካሠቃዩት በኋላ በእንጨት ላይ ሰቀሉት። ከዚያም “ተፈጸመ!” ብሎ ከተናገረ በኋላ ሞተ። (ዮሐንስ 19:30) ከሦስት ቀን በኋላ ይሖዋ ኢየሱስን ከሞት በማስነሳት መንፈሳዊ አካል ሰጠው። (1 ጴጥሮስ 3:18) ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ኢየሱስ ተመልሶ ወደ ሰማይ ሄደ፤ ከዚያም አምላክ እስኪያነግሠው ድረስ ‘በአምላክ ቀኝ ተቀምጦ’ መጠባበቅ ጀመረ።—ዕብራውያን 10:12, 13

22. ኢየሱስ ለአባቱ ታማኝ መሆኑ ምን መንገድ ከፍቶልናል?

22 ኢየሱስ ለአባቱ እስከ መጨረሻው ታማኝ መሆኑ የይሖዋ ዓላማ እንዲፈጸም ማለትም የሰው ልጆች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም መኖር እንዲችሉ መንገድ ከፍቷል። በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ፣ ኢየሱስ መሞቱ ለዘላለም መኖር የምንችልበትን መንገድ የከፈተልን እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

^ አን.11 ይሖዋ ፈጣሪ በመሆኑ አባት ተብሎ ተጠርቷል። (ኢሳይያስ 64:8) ይሖዋ ኢየሱስን ስለፈጠረው ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ተብሏል። በተጨማሪም መላእክትም ሆኑ ሰው የሆነው አዳም የአምላክ ልጆች ተብለው ተጠርተዋል።—ኢዮብ 1:6፤ ሉቃስ 3:38