በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ አሥር

መላእክትንና አጋንንትን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?

መላእክትንና አጋንንትን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?

1. ስለ መላእክት ማወቅ ያለብን ለምንድን ነው?

ይሖዋ ስለ ቤተሰቡ እንድናውቅ ይፈልጋል። መላእክት የአምላክ ቤተሰብ አባላት ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ መላእክትን ‘የአምላክ ልጆች’ በማለት ይጠራቸዋል። (ኢዮብ 38:7) የመላእክት ሥራ ምንድን ነው? በጥንት ዘመን ሰዎችን የረዱት እንዴት ነበር? በዛሬው ጊዜስ እኛን ሊረዱን ይችላሉ?—ተጨማሪ ሐሳብ 8⁠ን ተመልከት።

2. መላእክትን የፈጠረው ማን ነው? ቁጥራቸውስ ምን ያህል ነው?

2 በመጀመሪያ መላእክትን የፈጠረው ማን እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል። ቆላስይስ 1:16፣ ይሖዋ ኢየሱስን ከፈጠረ በኋላ ‘በሰማያትና በምድር ያሉ ሌሎች ነገሮችን በሙሉ’ እንደፈጠረ ይገልጻል። ይህም መላእክትን ይጨምራል። መላእክት ቁጥራቸው ምን ያህል ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መላእክት እንዳሉ ይናገራል።—መዝሙር 103:20፤ ራእይ 5:11

3. ኢዮብ 38:4-7 ስለ መላእክት ምን ይገልጽልናል?

3 በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ምድርን ከመፍጠሩ በፊት መላእክትን እንደፈጠረ ይናገራል። መላእክት ምድር ስትፈጠር ምን ተሰማቸው? የኢዮብ መጽሐፍ እንደተደሰቱ ይገልጽልናል። መላእክት ይሖዋን በአንድነት የሚያገለግሉና እርስ በርስ የሚቀራረቡ የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው።—ኢዮብ 38:4-7

መላእክት የአምላክን አገልጋዮች ይረዳሉ

4. መላእክት የሰው ልጆች የሚያደርጉትን ነገር በትኩረት እንደሚከታተሉ እንዴት ማወቅ እንችላለን?

4 መላእክት ምንጊዜም የሰው ልጆች የሚያደርጉትን ነገር በትኩረት ይከታተላሉ፤ እንዲሁም ይሖዋ ለምድርና ለሰው ልጆች ካለው ዓላማ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማወቅ ይጓጓሉ። (ምሳሌ 8:30, 31፤ 1 ጴጥሮስ 1:11, 12) በመሆኑም አዳምና ሔዋን ሲያምፁ በጣም አዝነው መሆን አለበት። በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች ይሖዋን እንደማይታዘዙ ሲመለከቱ ደግሞ ይበልጥ እንደሚያዝኑ የታወቀ ነው። አንድ ሰው ንስሐ ገብቶ ወደ አምላክ ሲመለስ ግን በጣም ይደሰታሉ። (ሉቃስ 15:10) መላእክት በተለይ አምላክን የሚያገለግሉ ሰዎችን በትኩረት ይከታተላሉ። ይሖዋ፣ በምድር ላይ ያሉ አገልጋዮቹን ለመርዳትና ለመጠበቅ በመላእክት ይጠቀማል። (ዕብራውያን 1:7, 14) እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

“አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ዘጋ።” —ዳንኤል 6:22

5. በጥንት ዘመን መላእክት የአምላክን አገልጋዮች የረዱት እንዴት ነው?

5 ይሖዋ፣ ሰዶምና ገሞራ የተባሉትን ከተሞች ባጠፋ ጊዜ ሁለት መላእክትን ልኮ ሎጥንና ልጆቹን ከጥፋቱ አድኗል። (ዘፍጥረት 19:15, 16) በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ካለፉ በኋላ ነቢዩ ዳንኤል የአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ተጥሎ ነበር፤ ይሁንና በዚህ ጊዜ ምንም ጉዳት አልደረሰበትም፤ ምክንያቱም ‘አምላክ መልአኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ዘግቶ’ ነበር። (ዳንኤል 6:22) ሐዋርያው ጴጥሮስ በታሰረ ጊዜም ይሖዋ መልአኩን ልኮ ከእስር ቤት አስወጥቶታል። (የሐዋርያት ሥራ 12:6-11) በተጨማሪም መላእክት ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ረድተውታል። ለምሳሌ ከተጠመቀ በኋላ ‘መላእክት ያገለግሉት ነበር።’ (ማርቆስ 1:13) ከዚህም ሌላ ኢየሱስ ከመገደሉ በፊት አንድ መልአክ ‘አበረታቶታል።’—ሉቃስ 22:43

6. (ሀ) በዛሬው ጊዜም መላእክት የአምላክን አገልጋዮች ይረዳሉ የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

6 በዛሬው ጊዜ መላእክት እንደ ቀድሞው ዘመን ሥጋዊ አካል ለብሰው ለሰው ልጆች አይገለጡም። ሆኖም አምላክ አገልጋዮቹን ለመርዳት አሁንም ቢሆን በመላእክት ይጠቀማል። መጽሐፍ ቅዱስ “የይሖዋ መልአክ በሚፈሩት ዙሪያ ይሰፍራል፤ ደግሞም ይታደጋቸዋል” ይላል። (መዝሙር 34:7) በዛሬው ጊዜ የመላእክት ጥበቃ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? እኛን መጉዳት የሚፈልጉ ኃይለኛ ጠላቶች ስላሉ ነው። ጠላቶቻችን እነማን ናቸው? የመጡት ከየት ነው? ሊጎዱን የሚሞክሩትስ እንዴት ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት አዳምና ሔዋን ከተፈጠሩ በኋላ የተከናወነውን ነገር እንመልከት።

በዓይን የማይታዩ ጠላቶቻችን

7. ሰይጣን ብዙ ሰዎችን ምን ማድረግ ችሏል?

7 በምዕራፍ 3 ላይ አንድ መልአክ በአምላክ ላይ እንዳመፀና ሌሎችን መግዛት ፈልጎ እንደነበር ተመልክተናል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን መልአክ ሰይጣን ዲያብሎስ በማለት ይጠራዋል። (ራእይ 12:9) ሰይጣን ሌሎችም በአምላክ ላይ እንዲያምፁ ማድረግ ፈለገ። በመሆኑም ሔዋንን ያታለላት ሲሆን ከዚያ ጊዜ ወዲህ ብዙ ሰዎችን አታሏል። ይሁንና እንደ አቤል፣ ሄኖክና ኖኅ ያሉ ሰዎች ለይሖዋ ታማኝ ሆነዋል።—ዕብራውያን 11:4, 5, 7

8. (ሀ) አንዳንድ መላእክት አጋንንት የሆኑት እንዴት ነው? (ለ) አጋንንት ከጥፋት ውኃው ለመትረፍ ምን አደረጉ?

8 በኖኅ ዘመን አንዳንድ መላእክት በአምላክ ላይ ያመፁ ከመሆኑም ሌላ ሰው ሆነው በምድር ላይ ለመኖር ሲሉ በሰማይ ያለውን መኖሪያቸውን ትተዋል። ለምን? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ያደረጉት ሚስት ማግባት ፈልገው እንደሆነ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 6:2ን አንብብ።) ሆኖም እነዚህ መላእክት እንዲህ ማድረጋቸው ስህተት ነበር። (ይሁዳ 6) በዚያ ዘመን የኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች ልክ እንደ እነዚህ ክፉ መላእክት ምግባረ ብልሹና ዓመፀኛ ሆነው ነበር። በመሆኑም ይሖዋ የጥፋት ውኃ በማምጣት ክፉዎቹን ሰዎች አጠፋቸው። ታማኝ አገልጋዮቹን ግን ከዚህ ጥፋት አድኗቸዋል። (ዘፍጥረት 7:17, 23) ክፉ የሆኑት መላእክት ከጥፋት ውኃው ለመትረፍ ወደ ሰማይ ተመልሰው ሄዱ። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ክፉ መላእክት አጋንንት በማለት ይጠራቸዋል። ከሰይጣን ጎን በመቆም በአምላክ ላይ ዓምፀዋል፤ በመሆኑም ዲያብሎስ ገዢያቸው ሆኗል።—ማቴዎስ 9:34

9. (ሀ) አጋንንት ወደ ሰማይ ተመልሰው ሲሄዱ ምን ሁኔታ ገጠማቸው? (ለ) ቀጥሎ ምን እንመለከታለን?

9 አጋንንት በማመፃቸው፣ ይሖዋ ዳግመኛ የእሱ ቤተሰብ አባላት እንዲሆኑ አልፈቀደላቸውም። (2 ጴጥሮስ 2:4) በዛሬው ጊዜ አጋንንት ሥጋዊ አካል መልበስ ባይችሉም እንኳ ‘መላውን ዓለም እያሳሳቱ ነው።’ (ራእይ 12:9፤ 1 ዮሐንስ 5:19) አጋንንት ብዙ ሰዎችን የሚያታልሉት ወይም የሚያሳስቱት እንዴት እንደሆነ እንመልከት።—2 ቆሮንቶስ 2:11ን አንብብ።

አጋንንት ሰዎችን የሚያታልሉት እንዴት ነው?

10. አጋንንት ሰዎችን የሚያታልሉት እንዴት ነው?

10 አጋንንት ሰዎችን ለማታለል የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። አንዳንድ ሰዎች በቀጥታ ከአጋንንት ጋር ለመገናኘት ይሞክራሉ፤ ሌሎች ደግሞ በጠንቋዮች ወይም ምትሃታዊ ኃይል አላቸው በሚባሉ ሰዎች አማካኝነት ከአጋንንት ጋር ይገናኛሉ። በዚህ መንገድ ከአጋንንት ጋር የሚደረገው ግንኙነት አጋንንታዊ ወይም መናፍስታዊ ድርጊት በመባል ይታወቃል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ከአጋንንት ጋር ንክኪ ካለው ከማንኛውም ነገር እንድንርቅ ያዘናል። (ገላትያ 5:19-21) ለምን? አንድ ሰው እንስሳትን ለመያዝ ወጥመድ እንደሚያዘጋጅ ሁሉ አጋንንትም የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅመው ሰዎችን ለማጥመድና ለመቆጣጠር ይሞክራሉ።—ተጨማሪ ሐሳብ 26⁠ን ተመልከት።

11. ጥንቆላ ምንድን ነው? ከጥንቆላ ልንርቅ የሚገባውስ ለምንድን ነው?

11 አጋንንት የሚጠቀሙበት አንዱ ዘዴ ጥንቆላ ነው። ጥንቆላ ሲባል በአጋንንት ኃይል ተጠቅሞ ስለወደፊቱ ጊዜ ወይም ስለማይታወቅ ነገር ለማወቅ መሞከር ማለት ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ከዋክብትን በመመልከት፣ አሻራ በማንበብ ወይም ሌሎች ነገሮችን በመጠቀም ሰዎች ወደፊት ምን እንደሚገጥማቸው ሊጠነቁል ይችላል። ብዙ ሰዎች እነዚህ ነገሮች ምንም ጉዳት እንደሌላቸው ቢያስቡም እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው። እነዚህ ድርጊቶች በጣም አደገኛ ናቸው። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ጠንቋዮች የሚጠነቁሉት በአጋንንት ኃይል እንደሆነ ይናገራል። የሐዋርያት ሥራ 16:16-18 “የጥንቆላ ጋኔን ያደረባት” አንዲት ሴት ትጠነቁል እንደነበር ይናገራል። ሐዋርያው ጳውሎስ ጋኔኑን ካስወጣላት በኋላ ልጅቷ ስለወደፊቱ ጊዜ የመናገር ችሎታዋን አጥታለች።

12. (ሀ) ከሞቱ ሰዎች ጋር ለመገናኘት መሞከር አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የአምላክ አገልጋዮች ከአጋንንት ጋር ንክኪ ባላቸው ልማዶች የማይካፈሉት ለምንድን ነው?

12 አጋንንት ሰዎችን ለማጥመድ የሚጠቀሙበት ሌላም ዘዴ አለ። የሞቱ ሰዎችን ማነጋገር እንደሚቻል እንዲሁም የሞቱ ሰዎች የሆነ ቦታ እየኖሩ እንደሆነና ከእኛ ጋር መገናኘት እንደሚችሉ ወይም ሊረዱን እንደሚችሉ እንድናምን ለማድረግ ይሞክራሉ። ለምሳሌ አንድ ሰው፣ ጓደኛውን ወይም ዘመዱን በሞት ቢያጣ ‘ከሞቱ ሰዎች ጋር መነጋገር እችላለሁ’ ወደሚል መናፍስት ጠሪ ሊሄድ ይችላል። መናፍስት ጠሪው ለዚህ ሰው ስለሞተው ጓደኛው ወይም ዘመዱ አስገራሚ ነገር ሊነግረው አልፎ ተርፎም የሞተውን ሰው ድምፅ አስመስሎ ሊያነጋግረው ይችላል። (1 ሳሙኤል 28:3-19) ግለሰቡ ከሞተው ሰው ጋር እየተነጋገረ እንዳለ አድርጎ ቢያስብም የሚገናኘው ከሟቹ ጋር ሳይሆን ከአጋንንት ጋር ነው። ከቀብር ጋር የተያያዙ ብዙ ልማዶች ‘የሞቱ ሰዎች የሆነ ቦታ እየኖሩ ነው’ በሚለው እምነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ከእነዚህ ልማዶች መካከል በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የሚካሄድ ጭፈራ፣ ተዝካር፣ ሙት ዓመት፣ ለሙታን መሥዋዕት ማቅረብና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች ልማዶች ይገኙበታል። ክርስቲያኖች እንዲህ ባሉት ልማዶች ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ቤተሰቦቻቸው ወይም ጎረቤቶቻቸው ሊነቅፏቸው፣ ሊሰድቧቸውና ሊያገሏቸው ይችላሉ። ይሁንና ክርስቲያኖች እንዲህ ባሉ ልማዶች የማይካፈሉት አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ሌላ ቦታ እንደማይኖር ስለሚያውቁ ነው። ከሞቱ ሰዎች ጋር መነጋገር አንችልም፤ እንዲሁም የሞቱ ሰዎች ሊረዱንም ሆነ ሊጎዱን አይችሉም። (መዝሙር 115:17) ስለዚህ በጣም መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ከሞቱ ሰዎች ወይም ከአጋንንት ጋር ለመገናኘት ፈጽሞ ጥረት አታድርግ፤ እንዲሁም ከአጋንንት ጋር ንክኪ ባላቸው ልማዶች ፈጽሞ አትካፈል።—ዘዳግም 18:10, 11ን አንብብ፤ ኢሳይያስ 8:19

13. በአንድ ወቅት አጋንንትን በጣም ይፈሩ የነበሩ ሰዎች ምን ማድረግ ችለዋል?

13 አጋንንት ሰዎችን ማታለል ብቻ ሳይሆን በፍርሃት እንዲዋጡ ያደርጋሉ። ሰይጣንና አጋንንቱ፣ አምላክ እነሱን ከምድር ላይ እንደሚያስወግዳቸውና ‘የቀራቸው ጊዜ ጥቂት’ እንደሆነ ስለሚያውቁ ከምንጊዜውም በላይ ጨካኝና ቁጡ ሆነዋል። (ራእይ 12:12, 17) ሆኖም በአንድ ወቅት አጋንንትን በጣም ይፈሩ የነበሩ ሰዎች ከዚህ ፍርሃት መላቀቅ ችለዋል። ይህን ማድረግ የቻሉት እንዴት ነው?

አጋንንትን መቃወምና ከአጋንንት ተጽዕኖ መላቀቅ የሚቻለው እንዴት ነው?

14. በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደኖሩት ክርስቲያኖች ከአጋንንት ተጽዕኖ መላቀቅ የምንችለው እንዴት ነው?

14 መጽሐፍ ቅዱስ አጋንንትን መቃወምና ከአጋንንት ተጽዕኖ መላቀቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይነግረናል። ለምሳሌ ያህል፣ በኤፌሶን ከተማ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች የአምላክን ቃል ከመማራቸው በፊት በአጋንንታዊ ድርጊቶች ይካፈሉ ነበር። እነዚህ ሰዎች ከአጋንንት ተጽዕኖ መላቀቅ የቻሉት እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አስማት ይሠሩ ከነበሩት መካከል ብዙዎች መጽሐፎቻቸውን አንድ ላይ ሰብስበው በማምጣት በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉ።” (የሐዋርያት ሥራ 19:19) እነዚህ ሰዎች ክርስቲያን መሆን ስለፈለጉ ለአስማት ይጠቀሙባቸው የነበሩትን መጻሕፍት በሙሉ አቃጥለዋል። በዛሬው ጊዜም ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። አንድ ሰው ይሖዋን ማገልገል ከፈለገ ከአጋንንት ጋር ንክኪ ያለውን ማንኛውንም ነገር ማስወገድ ይኖርበታል። ይህም መጻሕፍትን፣ መጽሔቶችን፣ ኮከብ ቆጠራን (ሆሮስኮፕን)፣ ፊልሞችን፣ ሙዚቃዎችንና ጨዋታዎችን ይጨምራል፤ እንዲሁም አስማትንና አጋንንትን ምንም ጉዳት እንደማያመጡ ወይም አስደሳች እንደሆኑ አድርገው የሚያቀርቡ ፖስተሮችን ያካትታል። በተጨማሪም ሰዎች ራሳቸውን ከአጋንንት ለመከላከል ሲሉ የሚያደርጓቸውን እንደ ክታብ ያሉ ነገሮችንም ማስወገድን ይጨምራል።—1 ቆሮንቶስ 10:21

15. ሰይጣንን እና አጋንንቱን ለመቃወም ምን ማድረግ ያስፈልገናል?

15 በኤፌሶን የነበሩት ሰዎች ስለ አስማት የሚናገሩ መጽሐፎቻቸውን ካቃጠሉ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላም ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር መታገል’ እንደሚያስፈልጋቸው ጽፎላቸው ነበር። (ኤፌሶን 6:12) እነዚህ ሰዎች መጽሐፎቻቸውን ያቃጠሉ ቢሆንም አጋንንት እነሱን ለማጥቃት ጥረት ማድረጋቸውን አላቆሙም ነበር። ታዲያ ይህን ጥቃት ለመከላከል ምን ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር? ጳውሎስ “የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ማምከን [ወይም መከላከል] የምትችሉበትን ትልቅ የእምነት ጋሻ አንሱ” ብሏቸዋል። (ኤፌሶን 6:16) ጋሻ በውጊያ ወቅት አንድን ወታደር ከጥቃት እንደሚጠብቀው ሁሉ እምነታችንም ከጥቃት ሊጠብቀን ይችላል። ይሖዋ እንደሚጠብቀን ሙሉ እምነት ካለን ሰይጣንን እና አጋንንቱን መቃወም እንችላለን።—ማቴዎስ 17:20

16. በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?

16 በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ በማንበብ እንዲሁም ይሖዋ ጥበቃ እንደሚያደርግልን በመተማመን ነው። በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ የምንተማመን ከሆነ ሰይጣንና አጋንንቱ ጉዳት ሊያደርሱብን አይችሉም።—1 ዮሐንስ 5:5

17. ከአጋንንት ጥቃት ጥበቃ ለማግኘት ልናደርገው የሚገባን ሌላው ነገር ምንድን ነው?

17 በኤፌሶን የነበሩ ክርስቲያኖች ምን ተጨማሪ ነገር ማድረግ ያስፈልጋቸው ነበር? የሚኖሩባት ከተማ በአጋንንታዊ ድርጊቶች የተሞላች ነበረች። በመሆኑም ጳውሎስ “በማንኛውም ጊዜ . . . መጸለያችሁን ቀጥሉ” ብሏቸዋል። (ኤፌሶን 6:18) ይሖዋ በማንኛውም ጊዜ ጥበቃ እንዲያደርግላቸው እሱን በጸሎት መጠየቅ ነበረባቸው። እኛስ? እኛም ብንሆን የምንኖረው በአጋንንታዊ ድርጊቶች በተሞላ ዓለም ውስጥ ነው። ስለዚህ ልክ እንደ ኤፌሶን ክርስቲያኖች ይሖዋ ጥበቃ እንዲያደርግልን መጸለይ እንዲሁም በምንጸልይበት ጊዜ ስሙን መጠቀም አለብን። (ምሳሌ 18:10ን አንብብ።) ይሖዋ ከሰይጣን እንዲጠብቀን ዘወትር የምንጸልይ ከሆነ ጸሎታችንን ይሰማል።—መዝሙር 145:19፤ ማቴዎስ 6:13

18, 19. (ሀ) ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ጋር የምናደርገውን ውጊያ ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ለየትኛው ጥያቄ መልስ እናገኛለን?

18 ከአጋንንት ጋር ንክኪ ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ካስወገድን እንዲሁም ጥበቃ እንደሚያደርግልን በይሖዋ ከተማመንን ሰይጣንን እና አጋንንቱን መቃወም እንችላለን። ሰይጣንንም ሆነ አጋንንቱን ልንፈራቸው አይገባም። (ያዕቆብ 4:7, 8ን አንብብ።) ይሖዋ ከአጋንንት እጅግ የላቀ ኃይል አለው። በኖኅ ዘመን ቀጥቷቸው ነበር፤ ወደፊት ደግሞ ያጠፋቸዋል። (ይሁዳ 6) ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ጋር የምንዋጋው ብቻችንን ሆነን አይደለም። ይሖዋ በመላእክቱ አማካኝነት ጥበቃ ያደርግልናል። (2 ነገሥት 6:15-17) ይሖዋ ስለሚረዳን ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ጋር የምናደርገውን ውጊያ ማሸነፍ እንደምንችል እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—1 ጴጥሮስ 5:6, 7፤ 2 ጴጥሮስ 2:9

19 ታዲያ ሰይጣንና አጋንንቱ በሰዎች ላይ ብዙ መከራ የሚያደርሱ ከሆነ አምላክ እስካሁን ያላጠፋቸው ለምንድን ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ እንመለከታለን።