በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ አሥራ ስምንት

ራሴን ለአምላክ መወሰንና መጠመቅ ይኖርብኛል?

ራሴን ለአምላክ መወሰንና መጠመቅ ይኖርብኛል?

1. እስካሁን ካገኘኸው እውቀት አንጻር የትኛውን ጥያቄ ልታነሳ ትችላለህ?

ይህን መጽሐፍ ስታጠና በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ተምረሃል፤ ከእነዚህ መካከል አምላክ የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጠን የገባልን ቃልየሞቱ ሰዎች የሚገኙበት ሁኔታየትንሣኤ ተስፋ ይገኙበታል። (መክብብ 9:5፤ ሉቃስ 23:43፤ ዮሐንስ 5:28, 29፤ ራእይ 21:3, 4) የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀምረህ ይሆናል፤ እንዲሁም እውነተኛውን ሃይማኖት የሚከተሉት እነሱ እንደሆኑ ተገንዝበህ ይሆናል። (ዮሐንስ 13:35) በተጨማሪም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት በመመሥረት እሱን ለማገልገል ወስነህ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ‘አምላክን ለማገልገል ምን ማድረግ ይኖርብኛል?’ ብለህ ታስብ ይሆናል።

2. ኢትዮጵያዊው ለመጠመቅ የፈለገው ለምንድን ነው?

2 በኢየሱስ ዘመን የኖረ አንድ ኢትዮጵያዊ ተመሳሳይ ስሜት ተሰምቶት ነበር። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደቀ መዝሙሩ ፊልጶስ ለዚህ ሰው ሰበከለት። ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነ ማስረጃ እየጠቀሰ አስረዳው። ኢትዮጵያዊው በሰማው ነገር ልቡ በጣም ስለተነካ ወዲያውኑ “ውኃ ይኸውና፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” በማለት ተናገረ።—የሐዋርያት ሥራ 8:26-36

3. (ሀ) ኢየሱስ ለተከታዮቹ ምን ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል? (ለ) አንድ ሰው መጠመቅ ያለበት እንዴት ነው?

3 ይሖዋን ማገልገል የምትፈልግ ከሆነ መጠመቅ እንደሚኖርብህ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምራል። ኢየሱስ ተከታዮቹን ‘ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’ ሲል አዟቸዋል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ኢየሱስ ራሱም በመጠመቅ ምሳሌ ትቶልናል። መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን ያጠመቀው ውኃ በመርጨት ወይም ራሱ ላይ በማፍሰስ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ሙሉ በሙሉ ውኃው ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ነው። (ማቴዎስ 3:16) በዛሬው ጊዜም አንድ ክርስቲያን ሲጠመቅ ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ መግባት ወይም መጥለቅ አለበት።

4. መጠመቅህ ምን ያሳያል?

4 ጥምቀት የአምላክ ወዳጅ መሆንና እሱን ማገልገል እንደምትፈልግ ለሌሎች በይፋ የምታሳይበት መንገድ ነው። (መዝሙር 40:7, 8) በመሆኑም ‘ለመጠመቅ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

እውቀትና እምነት

5. (ሀ) ከመጠመቅህ በፊት ምን ማድረግ አለብህ? (ለ) በስብሰባዎች ላይ መገኘትህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

5 ከመጠመቅህ በፊት ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ማወቅ አለብህ። መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናህ መሆኑ ይህን እያደረግክ እንዳለ ያሳያል። (ዮሐንስ 17:3ን አንብብ።) ይሁንና ይህ ብቻ በቂ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስለ ይሖዋ ፈቃድ በሚገልጸው ‘ትክክለኛ እውቀት መሞላት’ እንዳለብን ይናገራል። (ቆላስይስ 1:9) የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንድትመሠርት ይረዱሃል። በመሆኑም በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ መገኘትህ በጣም አስፈላጊ ነው።—ዕብራውያን 10:24, 25

ከመጠመቅህ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት አለብህ

6. ከመጠመቅህ በፊት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያህል እውቀት ሊኖርህ ይገባል?

6 እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ከመጠመቅህ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ በሙሉ ጠንቅቀህ እንድታውቅ አይጠብቅብህም። ኢትዮጵያዊው ሰው የተጠመቀው ሁሉንም ነገር ስላወቀ አይደለም። (የሐዋርያት ሥራ 8:30, 31) ደግሞም ስለ አምላክ የምንማረው ለዘላለም ነው። (መክብብ 3:11) ሆኖም ከመጠመቅህ በፊት መሠረታዊ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ማወቅና አምነህ መቀበል ይኖርብሃል።—ዕብራውያን 5:12

7. መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ የረዳህ እንዴት ነው?

7 መጽሐፍ ቅዱስ “ያለ እምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም” ይላል። (ዕብራውያን 11:6) በመሆኑም ከመጠመቅህ በፊት እምነት ሊኖርህ ይገባል። በጥንቷ የቆሮንቶስ ከተማ የነበሩ ሰዎች፣ የኢየሱስ ተከታዮች ያስተምሩ የነበረውን ትምህርት እንደሰሙና በዚህም የተነሳ ‘አምነው እንደተጠመቁ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 18:8) አንተም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ አምላክ ቃል በገባቸው ነገሮች ላይ እንዲሁም ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ሊያወጣን በሚችለው በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ እምነት እንዲኖርህ ረድቶሃል።—ኢያሱ 23:14፤ የሐዋርያት ሥራ 4:12፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለሌሎች ተናገር

8. የተማርከውን ነገር ለሌሎች እንድትናገር የሚያነሳሳህ ምንድን ነው?

8 ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ እያወቅክ ስትሄድ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምን ያህል እንደጠቀመህ ስትመለከት እምነትህ እየጠነከረ ይሄዳል። ይህም እየተማርክ ያለኸውን ነገር ለሌሎች ለመንገር ያነሳሳሃል። (ኤርምያስ 20:9፤ 2 ቆሮንቶስ 4:13) ይሁንና መንገር ያለብህ ለእነማን ነው?

እምነት፣ የተማርከውን ነገር ለሌሎች እንድትናገር ያነሳሳሃል

9, 10. (ሀ) የተማርከውን ነገር ለእነማን መንገር ትችላለህ? (ለ) ከጉባኤው ጋር በስብከቱ ሥራ መካፈል ከፈለግክ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

9 እየተማርክ ስላለኸው ነገር ለቤተሰብህ፣ ለጓደኞችህ፣ ለጎረቤቶችህ እንዲሁም አብረውህ ለሚሠሩ ሰዎች ለመንገር ትፈልግ ይሆናል። ይህ ጥሩ ነገር ነው፤ ሆኖም እንዲህ ማድረግ ያለብህ በደግነትና በፍቅር ነው። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ከጉባኤው ጋር አብረህ መስበክ ትጀምራለህ። ለዚህ ዝግጁ እንደሆንክ ሲሰማህ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስጠናህን ሰው፣ ከጉባኤው ጋር አብረህ በስብከቱ ሥራ መካፈል እንደምትፈልግ ልትነግረው ትችላለህ። እሱም ዝግጁ እንደሆንክ ከተሰማውና የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሕይወትህ ውስጥ ተግባራዊ ካደረግክ አንተና አስጠኚህ ከሁለት የጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር ተገናኝታችሁ ትወያያላችሁ።

10 ከጉባኤ ሽማግሌዎቹ ጋር የምትወያዩበት ዓላማ ምንድን ነው? እነዚህ ሽማግሌዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርቶች በትክክል እንደተረዳህና እንደምታምንባቸው፣ በዕለት ተዕለት ሕይወትህ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ እንደምታደርግ እንዲሁም የይሖዋ ምሥክር የመሆን ልባዊ ፍላጎት እንዳለህ ማወቅ ይፈልጋሉ። ሽማግሌዎች አንተን ጨምሮ ሁሉንም የጉባኤው አባላት ለመርዳት ዝግጁ እንደሆኑ አስታውስ፤ በመሆኑም እነሱን ማነጋገር ሊያስፈራህ አይገባም። (የሐዋርያት ሥራ 20:28፤ 1 ጴጥሮስ 5:2, 3) ከሽማግሌዎቹ ጋር ከተነጋገርክ በኋላ ሽማግሌዎቹ ከጉባኤው ጋር መስበክ ለመጀመር ዝግጁ መሆን አለመሆንህን ያሳውቁሃል።

11. ከጉባኤው ጋር መስበክ ከመጀመርህ በፊት ለውጥ ማድረግህ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

11 ሽማግሌዎቹ ከጉባኤው ጋር መስበክ ከመጀመርህ በፊት አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ እንደሚኖርብህ ይነግሩህ ይሆናል። እነዚህን ለውጦች ማድረግህ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ለሌሎች ስለ አምላክ የምንናገረው ይሖዋን ወክለን ነው፤ በመሆኑም እሱን በሚያስከብር መንገድ መኖር አለብን።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ገላትያ 5:19-21

ንስሐ መግባትና መመለስ

12. ሁሉም ሰው ንስሐ መግባት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

12 ከመጠመቅህ በፊት ማድረግ ያለብህ ሌላም ነገር አለ። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሐ ግቡ፣ ተመለሱም” በማለት ተናግሯል። (የሐዋርያት ሥራ 3:19) ንስሐ መግባት ሲባል ምን ማለት ነው? ከዚህ በፊት በሠራነው መጥፎ ነገር ከልብ ማዘን ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ቀደም ሲል የፆታ ብልግና ትፈጽም ከነበረ ንስሐ መግባት ያስፈልግሃል። በሕይወት ዘመንህ በሙሉ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ስትጥር የነበረ ቢሆንም እንኳ ንስሐ መግባት ይኖርብሃል፤ ምክንያቱም ሁላችንም ኃጢአተኞች ስለሆንን አምላክ ይቅር እንዲለን መለመን አለብን።—ሮም 3:23፤ 5:12

13. ‘መመለስ’ ሲባል ምን ማለት ነው?

13 ታዲያ ባደረግከው ነገር ማዘንህ ብቻ በቂ ነው? አይደለም። ጴጥሮስ ‘መመለስ’ እንደሚያስፈልግህም ተናግሯል። ይህም ቀደም ሲል የነበረህን መጥፎ አኗኗር ትተህ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ይጠይቅብሃል። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ መኪና እየነዳህ ወደ አንድ ቦታ ለመጀመሪያ ጊዜ እየሄድክ ነው እንበል። የተወሰነ መንገድ ከሄድክ በኋላ እየተጓዝክ ያለኸው በተሳሳተ አቅጣጫ እንደሆነ አወቅክ። በዚህ ጊዜ ምን ታደርጋለህ? ፍጥነትህን ቀንሰህ ታቆማለህ፤ ከዚያም መኪናህን አዙረህ በመመለስ በትክክለኛው አቅጣጫ ትጓዛለህ። በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና፣ ከአንዳንድ ልማዶች ወይም ነገሮች ጋር በተያያዘ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግህ ልትገነዘብ ትችላለህ። በዚህ ጊዜ ‘ለመመለስ’ ማለትም አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ ለመለወጥና ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ ሁን።

ራስህን ለአምላክ ወስን

ይሖዋን ለማገልገል ቃል ገብተሃል?

14. ራስህን ለአምላክ የምትወስነው እንዴት ነው?

14 ከመጠመቅህ በፊት ልትወስደው የሚገባህ ሌላው አስፈላጊ እርምጃ ራስህን ለይሖዋ መወሰን ነው። ራስህን ለይሖዋ ስትወስን፣ እሱን ብቻ ለማምለክ እንዲሁም በሕይወትህ ውስጥ የእሱን ፈቃድ ለማስቀደም በጸሎት ቃል ትገባለህ።—ዘዳግም 6:15

15, 16. አንድ ሰው ራሱን ለአምላክ እንዲወስን የሚያነሳሳው ምንድን ነው?

15 ይሖዋን ብቻ ለማገልገል ቃል መግባት፣ በቀረው ሕይወትህ ከምትወደው ሰው ጋር ለመኖር ቃል ከመግባት ጋር ይመሳሰላል። አንድ ወንድና አንዲት ሴት መጠናናት ጀምረዋል እንበል። ወንዱ ሴቷን ይበልጥ እያወቃት ሲሄድ በጣም ስለሚወዳት ሊያገባት ይወስናል። ይህ ከባድ ውሳኔ ቢሆንም ስለሚወዳት ይህን ኃላፊነት ለመቀበል ፈቃደኛ ይሆናል።

16 አንተም ስለ ይሖዋ ይበልጥ እያወቅክ ስትሄድ በጣም ትወደዋለህ፤ እንዲሁም እሱን ለማገልገል የተቻለህን ያህል ጥረት ለማድረግ ትነሳሳለህ። ይህም እሱን ለማገልገል ቃል መግባትህን በጸሎት እንድትነግረው ይገፋፋሃል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስን መከተል የሚፈልግ ሁሉ ‘ራሱን መካድ’ እንዳለበት ይናገራል። (ማርቆስ 8:34) ይህ ምን ማለት ነው? ይሖዋ ያወጣቸው መመሪያዎች በሕይወትህ ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ ይይዛሉ ማለት ነው። ከራስህ ፍላጎትና ግብ ይልቅ ቅድሚያ የምትሰጠው ይሖዋ ለሚፈልገው ነገር ይሆናል።—1 ጴጥሮስ 4:2ን አንብብ።

‘የገባሁትን ቃል ጠብቄ መኖር ባልችልስ?’

17. አንዳንዶች ራሳቸውን ለይሖዋ የማይወስኑት ለምን ሊሆን ይችላል?

17 አንዳንድ ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰን አይፈልጉም፤ ‘እሱን ለማገልገል የገባሁትን ቃል ጠብቄ መኖር ባልችልስ?’ የሚል ፍርሃት ያድርባቸዋል። እነዚህ ሰዎች እንዲህ የሚሰማቸው ይሖዋን ማሳዘን ስለማይፈልጉ ወይም ራሳቸውን ለይሖዋ ካልወሰኑ በሚያደርጉት ነገር ይሖዋ እንደማይጠይቃቸው ስለሚያስቡ ሊሆን ይችላል።

18. ‘ይሖዋን ባሳዝነውስ’ የሚለውን ፍርሃት እንድታሸንፍ የሚረዳህ ምንድን ነው?

18 ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ‘እሱን ባሳዝነውስ’ የሚለውን ፍርሃት እንድታሸንፍ ይረዳሃል። ይሖዋን ስለምትወደው ለእሱ የገባኸውን ቃል ለመጠበቅ የተቻለህን ያህል ጥረት ታደርጋለህ። (መክብብ 5:4፤ ቆላስይስ 1:10) የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ በጣም ከባድ እንደሆነ አይሰማህም። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነውና፤ ትእዛዛቱ ደግሞ ከባድ አይደሉም።”—1 ዮሐንስ 5:3

19. ራስህን ለይሖዋ መወሰን ሊያስፈራህ የማይገባው ለምንድን ነው?

19 ራስህን ለይሖዋ ለመወሰን ፍጹም መሆን አያስፈልግህም። ይሖዋ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር እንድናደርግ አይጠብቅብንም። (መዝሙር 103:14) እሱ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ እንድትችል ይረዳሃል። (ኢሳይያስ 41:10) በሙሉ ልብህ በይሖዋ ከታመንክ እሱ “ጎዳናህን ቀና ያደርገዋል።”—ምሳሌ 3:5, 6

ራስህን መወሰንህን በሕዝብ ፊት ማሳወቅ

20. ራስህን ለአምላክ ከወሰንክ በኋላ ልትወስደው የሚገባው ቀጣይ እርምጃ ምንድን ነው?

20 ራስህን ለይሖዋ ለመወሰን ዝግጁ እንደሆንክ ይሰማሃል? ራስህን ለይሖዋ ከወሰንክ፣ የሚቀጥለውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ትሆናለህ። ይህ እርምጃ ጥምቀት ነው።

21, 22. ‘እምነትህን በይፋ መናገር’ የምትችለው እንዴት ነው?

21 ራስህን ለይሖዋ እንደወሰንክና መጠመቅ እንደምትፈልግ ለጉባኤህ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ አሳውቅ። አስተባባሪው ከተወሰኑ ሽማግሌዎች ጋር መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን እንድትከልስ ዝግጅት ያደርጋል። እነዚህ ሽማግሌዎች ለመጠመቅ ብቁ መሆንህን ካመኑበት በቀጣዩ የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ ላይ መጠመቅ እንደምትችል ያሳውቁሃል። በስብሰባው ላይ ስለ ጥምቀት የሚያብራራ ንግግር ይቀርባል። በመቀጠልም ተናጋሪው ለመጠመቅ የተዘጋጁትን ሰዎች ሁለት ጥያቄዎች ይጠይቃቸዋል። ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ‘እምነትህን በይፋ ትናገራለህ።’—ሮም 10:10

22 ከዚያም ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በመግባት ትጠመቃለህ። ይህም ራስህን ለይሖዋ መወሰንህንና ከዚያ በኋላ የይሖዋ ምሥክር መሆንህን ሌሎች ሰዎች እንዲገነዘቡ ያደርጋል።

መጠመቅህ ምን ያመለክታል?

23. “በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” መጠመቅ ሲባል ምን ማለት ነው?

23 ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ “በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” እንደሚጠመቁ ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 28:19ን አንብብ።) ይህ ምን ማለት ነው? በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ትጠመቃለህ ሲባል የይሖዋን ሥልጣን፣ ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ያለውን ቦታ እንዲሁም አምላክ ፈቃዱን ለመፈጸም በቅዱስ መንፈሱ እንዴት እንደሚጠቀም ትገነዘባለህ ማለት ነው።—መዝሙር 83:18፤ ማቴዎስ 28:18፤ ገላትያ 5:22, 23፤ 2 ጴጥሮስ 1:21

መጠመቅህ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ እንደምትፈልግ ያሳያል

24, 25. (ሀ) ጥምቀት ምን ያመለክታል? (ለ) በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ለየትኛው ጥያቄ መልስ እናገኛለን?

24 ጥምቀት አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነን ነገር ያመለክታል። ውኃ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መግባትህ ለቀድሞው አኗኗርህ እንደሞትክ ወይም ያን ሕይወት እንደተውክ የሚያሳይ ነው። ከውኃው ውስጥ መውጣትህ ደግሞ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ አዲስ ሕይወት እንደጀመርክ የሚያመለክት ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይሖዋን እንደምታገለግል ያሳያል። ራስህን የምትወስነው ለአንድ ግለሰብ፣ ድርጅት ወይም ለአንድ ሥራ እንዳልሆነ አስታውስ። ሕይወትህን የምትወስነው ለይሖዋ ነው።

25 ራስህን መወሰንህ ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንድትመሠርት ይረዳሃል። (መዝሙር 25:14) ይህ ሲባል ግን አንድ ሰው ስለተጠመቀ ብቻ ይድናል ማለት አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ “በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግታችሁ ሥሩ” በማለት ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 2:12) ጥምቀት የመጀመሪያ እርምጃ ብቻ ነው። ታዲያ ከይሖዋ ጋር የመሠረትከውን ወዳጅነት ጠብቀህ መኖር የምትችለው እንዴት ነው? የመጨረሻው ምዕራፍ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።