በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 3

አዳምና ሔዋን አምላክን ሳይታዘዙ ቀሩ

አዳምና ሔዋን አምላክን ሳይታዘዙ ቀሩ

አንድ ቀን ሔዋን ብቻዋን እያለች አንድ እባብ አነጋገራት። ‘አምላክ ከማንኛውም ዛፍ እንዳትበሉ ከልክሏችኋል?’ ብሎ ጠየቃት። ሔዋንም ‘ከአንዱ ዛፍ በስተቀር ከሌሎቹ ዛፎች ሁሉ መብላት እንችላለን። ከዚያ ዛፍ ፍሬ ከበላን ግን እንሞታለን’ አለችው። እባቡም ‘አትሞቱም። እንዲያውም ከዚያ ዛፍ ከበላችሁ እንደ አምላክ ትሆናላችሁ’ አላት። እባቡ የተናገረው ነገር እውነት ነበር? በፍጹም፣ ውሸት ነበር። ሔዋን ግን እባቡን አመነችው። ሔዋን ፍሬውን ትኩር ብላ ስትመለከተው የመብላት ፍላጎቷ እየጨመረ ሄደ። ከዚያም ፍሬውን ወስዳ በላች፤ ለአዳምም ሰጠችው። አዳም፣ አምላክን ካልታዘዙ እንደሚሞቱ ያውቅ የነበረ ቢሆንም ፍሬውን በላ።

ቀኑ እየመሸ ሲሄድ ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን አነጋገራቸው። እሱን ሳይታዘዙ የቀሩት ለምን እንደሆነ ጠየቃቸው። ሔዋን በእባቡ አሳበበች፤ አዳም ደግሞ በሔዋን አሳበበ። አዳምና ሔዋን ስላልታዘዙ ይሖዋ ከአትክልት ስፍራው አስወጣቸው። ተመልሰው መግባት እንዳይችሉ በአትክልት ስፍራው መግቢያ ላይ መላእክትንና የሚሽከረከር የነበልባል ሰይፍ አስቀመጠ።

ሔዋንን ያነጋገራት እባቡ ራሱ አልነበረም። ይሖዋ እባብን መናገር እንዲችል አድርጎ አልፈጠረውም። እባቡን እንዲናገር ያደረገው አንድ ክፉ መልአክ ነው። ይሖዋ ለሔዋን ውሸት የነገራትን ይህን መልአክም እንደሚቀጣው ተናግሯል። ይህ ክፉ መልአክ ሰይጣን ዲያብሎስ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን እንዲህ ያደረገው ሔዋንን ለማታለል ብሎ ነው። ወደፊት ሰይጣን ሰዎችን ማታለሉን እንዳይቀጥል ይሖዋ ያጠፋዋል።

“ዲያብሎስ . . . ከመጀመሪያው አንስቶ ነፍሰ ገዳይ ነበር፤ በእሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት ውስጥ ጸንቶ አልቆመም።”—ዮሐንስ 8:44 የግርጌ ማስታወሻ