በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 8

አብርሃምና ሣራ አምላክን ታዘዋል

አብርሃምና ሣራ አምላክን ታዘዋል

በባቤል አቅራቢያ የምትገኝ ዑር የምትባል አንዲት ከተማ ነበረች፤ በከተማዋ የሚኖሩ ሰዎች ይሖዋን ሳይሆን ሌሎች አማልክትን ያመልኩ ነበር። ሆኖም በዚህች ከተማ የሚኖር ይሖዋን ብቻ የሚያመልክ አንድ ሰው ነበር። ይህ ሰው አብርሃም ይባላል።

ይሖዋ አብርሃምን ‘ቤትህንና ዘመዶችህን ትተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ’ አለው። ከዚያም አምላክ እንዲህ ብሎ ቃል ገባለት፦ ‘ብዙ ሕዝብ ትሆናለህ፤ እንዲሁም በአንተ አማካኝነት ለምድር ሕዝቦች ሁሉ ጥሩ ነገር አደርግላቸዋለሁ።’

አብርሃም፣ ይሖዋ ወዴት እንደሚልከው ባያውቅም በይሖዋ ታምኗል። ስለዚህ አብርሃም፣ ሚስቱ ሣራ፣ አባቱ ታራ እንዲሁም የወንድሙ ልጅ ሎጥ ዕቃቸውን ይዘው በታዛዥነት ረጅሙን ጉዞ ጀመሩ።

አብርሃምና ቤተሰቡ ይሖዋ ሊያሳያቸው ወደፈለገው ቦታ ሲደርሱ አብርሃም 75 ዓመቱ ነበር። ያ ቦታ የከነአን ምድር ይባል ነበር። እዚያ ከደረሱ በኋላ አምላክ አብርሃምን አነጋገረው፤ ‘ይህን የምታየውን ቦታ ሁሉ ለልጆችህ እሰጣቸዋለሁ’ ብሎ ቃል ገባለት። አብርሃምና ሣራ ግን አርጅተው የነበረ ሲሆን ምንም ልጅ አልነበራቸውም። ታዲያ ይሖዋ የገባውን ቃል የሚፈጽመው እንዴት ነው?

“አብርሃም . . . ወደፊት ርስት አድርጎ ወደሚቀበለው ስፍራ በመሄድ በእምነት ታዘዘ፤ ወዴት እንደሚሄድ ባያውቅም ይኖርበት የነበረውን ስፍራ ለቆ ወጣ።”—ዕብራውያን 11:8