በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 9

በመጨረሻ ልጅ ወለዱ!

በመጨረሻ ልጅ ወለዱ!

አብርሃምና ሣራ ተጋብተው ለረጅም ጊዜ ኖረዋል። በዑር የነበራቸውን ምቹ ቤት ትተው በድንኳን እየኖሩ ነበር። ሆኖም ሣራ በይሖዋ ትታመን ስለነበር አላጉረመረመችም።

ሣራ ልጅ ማግኘት በጣም ትፈልግ ስለነበር አብርሃምን ‘አገልጋዬ አጋር ልጅ ብትወልድ ልጁ እንደ ራሴ ልጅ ይሆናል’ አለችው። ከጊዜ በኋላ አጋር ወንድ ልጅ ወለደች። የልጁ ስም እስማኤል ይባላል።

ከብዙ ዓመታት በኋላ ማለትም አብርሃም 99 ዓመት፣ ሣራ ደግሞ 89 ዓመት ሲሆናቸው ሦስት እንግዶች ወደ እነአብርሃም ቤት መጡ። አብርሃም እንግዶቹን ዛፍ ሥር እንዲያርፉና ምግብ እንዲበሉ ጠየቃቸው። እነዚህ እንግዶች እነማን እንደሆኑ ታውቃለህ? መላእክት ነበሩ! እነሱም አብርሃምን ‘በሚቀጥለው ዓመት በዚህ ጊዜ ሚስትህ ወንድ ልጅ ትወልዳለች’ አሉት። ሣራ ድንኳኑ ውስጥ ሆና የሚሉትን ትሰማ ነበር። ይህን ስትሰማ ‘አሁን እንዲህ ካረጀሁ በኋላ ልጅ መውለድ እችላለሁ?’ ብላ በማሰብ ሳቀች።

በቀጣዩ ዓመት ልክ የይሖዋ መልአክ እንደተናገረው ሣራ ወንድ ልጅ ወለደች። አብርሃም ልጁን ይስሐቅ ብሎ ስም አወጣለት፤ ይስሐቅ ማለት “ሳቅ” ማለት ነው።

ይስሐቅ አምስት ዓመት አካባቢ ሲሆነው ሣራ፣ እስማኤል በይስሐቅ ላይ ሲያሾፍበት አየች። ልጇን ለመጠበቅ ስትል አጋርንና እስማኤልን እንዲያባርራቸው አብርሃምን ጠየቀችው። አብርሃም መጀመሪያ ላይ እንደዚህ ማድረግ አልፈለገም ነበር። ሆኖም ይሖዋ ለይስሐቅ ጥበቃ ማድረግ ስለፈለገ አብርሃምን እንዲህ አለው፦ ‘ሣራ የምትልህን ስማ። እስማኤልን እኔ እንከባከበዋለሁ። የገባሁልህ ቃል የሚፈጸመው ግን በይስሐቅ በኩል ነው።’

“ሣራም የተስፋን ቃል የሰጠው እሱ ታማኝ እንደሆነ አድርጋ ስላሰበች . . . ዘር ለመፀነስ በእምነት ኃይል አገኘች።”—ዕብራውያን 11:11