በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 12

ያዕቆብ ውርስ አገኘ

ያዕቆብ ውርስ አገኘ

ይስሐቅ ርብቃን ሲያገባ 40 ዓመቱ ነበር። ርብቃን በጣም ይወዳት ነበር። ከጊዜ በኋላ ሁለት መንታ ወንዶች ልጆች ወለዱ።

ታላቁ ልጅ ስሙ ኤሳው ነበር፤ ታናሽየው ደግሞ ያዕቆብ ይባላል። ኤሳው ከቤት ውጭ መዋል የሚወድ ጎበዝ የእንስሳት አዳኝ ነበር። ያዕቆብ ግን ቤት ውስጥ መዋል ያስደስተው ነበር።

በዚያ ዘመን አንድ አባት ሲሞት አብዛኛው መሬትና ገንዘብ የሚሰጠው ለታላቁ ልጅ ነበር። ይህ ውርስ ይባላል። በይስሐቅ ቤተሰብ ውስጥ ደግሞ ይህ ውርስ ይሖዋ ለአብርሃም የሰጣቸውን ተስፋዎችም ይጨምር ነበር። ኤሳው፣ ይሖዋ ለአብርሃም ስለሰጠው ተስፋ ብዙም ግድ አልነበረውም፤ ያዕቆብ ግን እነዚህን ተስፋዎች ከፍ አድርጎ ይመለከት ነበር።

አንድ ቀን ኤሳው እንስሳትን ሲያድን ውሎ በጣም ደክሞት ወደ ቤት ተመለሰ። ያዕቆብ እየሠራው የነበረው ጣፋጭ ምግብ ሸተተውና ‘በጣም ርቦኛል! እስቲ ከቀዩ ወጥ ስጠኝ!’ አለው። ከዚያም ያዕቆብ ‘ምግቡን እሰጥሃለሁ፤ መጀመሪያ ግን ውርስህን እንደምትሰጠኝ ቃል ግባልኝ’ አለው። ኤሳውም መልሶ ‘አሁን እኔ የውርስ ነገር አያሳስበኝም! ከፈለግክ ውሰደው። ብቻ የሚበላ ነገር ስጠኝ’ አለው። ኤሳው እንዲህ ማድረጉ ትክክል ይመስልሃል? ትክክል አልነበረም። ኤሳው ለምግብ ሲል በጣም ውድ የሆነ ነገር አሳልፎ ሰጠ።

ይስሐቅ እያረጀ ሲሄድ የበኩር ልጁን ለመባረክ አሰበ። ርብቃ ግን በረከቱን ታናሽየው ልጅ ያዕቆብ እንዲያገኝ አደረገች። ኤሳው ይህን ሲያውቅ በጣም ተናደደና ወንድሙን ለመግደል አሰበ። ይስሐቅና ርብቃ፣ ያዕቆብን ወንድሙ እንዳይገድለው ስለፈሩ ‘የኤሳው ቁጣ እስኪበርድ ድረስ ወደ አጎትህ ወደ ላባ ሄደህ እዚያ ቆይ’ አሉት። ያዕቆብ የወላጆቹን ምክር ሰምቶ ሕይወቱን ለማዳን ሸሸ።

“አንድ ሰው ዓለሙን ሁሉ የራሱ ቢያደርግና ሕይወቱን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ሰው ለሕይወቱ ምትክ የሚሆን ምን ነገር ሊሰጥ ይችላል?”—ማርቆስ 8:36, 37