በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 15

ይሖዋ ዮሴፍን አልረሳውም

ይሖዋ ዮሴፍን አልረሳውም

ዮሴፍ እስር ቤት ውስጥ በነበረበት ወቅት የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ሕልም አለመ፤ የሕልሙን ትርጉም ማንም ሊነግረው አልቻለም። ከፈርዖን አገልጋዮች አንዱ፣ ዮሴፍ ሕልሙን ሊፈታለት እንደሚችል ለፈርዖን ነገረው። ፈርዖንም ወዲያውኑ ዮሴፍን አስጠራው።

ፈርዖን ዮሴፍን ‘ሕልሜን ልትፈታልኝ ትችላለህ?’ ብሎ ጠየቀው። ዮሴፍም እንዲህ አለው፦ ‘ለሰባት ዓመት ያህል በግብፅ ብዙ ምግብ ይኖራል፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ ለሰባት ዓመት ረሃብ ይሆናል። በእነዚህ ዓመታት ሕዝቡ እንዳይራብ ጥበበኛ የሆነ ሰው ምረጥና ምግብ እንዲያከማች አድርግ።’ ፈርዖንም ‘አንተን መርጬሃለሁ! በግብፅ ውስጥ ከእኔ ቀጥሎ ከፍተኛው ባለሥልጣን አንተ ትሆናለህ!’ አለው። ዮሴፍ የፈርዖን ሕልም ምን ትርጉም እንዳለው ያወቀው እንዴት ነው? ይሖዋ ስለረዳው ነው።

በቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት ዮሴፍ ምግብ አከማቸ። ከዚያም ልክ ዮሴፍ እንደተናገረው በመላው ምድር ረሃብ ሆነ። በሁሉም ቦታ ያሉ ሰዎች ከዮሴፍ ምግብ ለመግዛት ወደ ግብፅ ይመጡ ነበር። የዮሴፍ አባት የሆነው ያዕቆብ በግብፅ ምግብ እንዳለ ስለሰማ አሥሩን ልጆቹን ወደ ግብፅ ሄደው ምግብ እንዲገዙ ላካቸው።

የያዕቆብ ልጆች ወደ ዮሴፍ ሄዱ፤ ዮሴፍም ወዲያውኑ አወቃቸው። እነሱ ግን ዮሴፍ መሆኑን አላወቁም ነበር። ዮሴፍ በልጅነቱ በሕልሙ አይቶ እንደነበረው ወንድሞቹ ሰገዱለት። ዮሴፍ ወንድሞቹ ባሕርያቸው ተሻሽሎ መሆን አለመሆኑን ማወቅ ፈልጎ ነበር። ስለዚህ እንዲህ አላቸው፦ ‘ሰላዮች ናችሁ። እዚህ የመጣችሁት አገራችንን እንዴት ማጥቃት እንደምትችሉ ለመሰለል ነው።’ እነሱም እንዲህ አሉት፦ ‘እኛ ሰላዮች አይደለንም! በከነአን የምንኖር 12 ወንድማማቾች ነበርን። አንዱ ወንድማችን ሞቷል፤ ትንሹ ወንድማችን ደግሞ ከአባታችን ጋር ነው።’ በዚህ ጊዜ ዮሴፍ ‘ታናሽ ወንድማችሁን ይዛችሁ ኑ፤ ያኔ አምናችኋለሁ’ አላቸው። ስለዚህ ወደ አባታቸው ተመልሰው ሄዱ።

ቤተሰቡ ምግብ ሲያልቅበት ያዕቆብ ልጆቹን እንደገና ወደ ግብፅ ላካቸው። በዚህ ጊዜ ታናሽ ወንድማቸውን ቢንያምን ይዘውት ሄዱ። ዮሴፍ ወንድሞቹን ለመፈተን ሲል የብር ጽዋውን የቢንያም የእህል ከረጢት ውስጥ ደበቀው፤ ከዚያም ወንድሞቹ ጽዋውን እንደሰረቁ አድርጎ ተናገረ። የዮሴፍ አገልጋዮች ጽዋውን የቢንያም ከረጢት ውስጥ ሲያገኙት ወንድሞቹ በጣም ደነገጡ። ከዚያም በቢንያም ፋንታ እነሱን እንዲቀጣቸው ዮሴፍን ለመኑት።

በዚህ ጊዜ ዮሴፍ ወንድሞቹ እንደተለወጡ አወቀ። ዮሴፍ ስሜቱን መቆጣጠር ስላልቻለ ማልቀስ ጀመረ። ‘እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ። አባቴ አሁንም በሕይወት አለ?’ አላቸው። ወንድሞቹ ዮሴፍ መሆኑን ሲያውቁ በጣም ደነገጡ። እሱም እንዲህ አላቸው፦ ‘በእኔ ላይ ባደረጋችሁት ነገር አትዘኑ። አምላክ ወደዚህ የላከኝ የእናንተን ሕይወት ለማትረፍ ብሎ ነው። አሁን ቶሎ ሂዱና አባቴን ይዛችሁት ኑ።’

የዮሴፍ ወንድሞች ለአባታቸው ዮሴፍን እንዳገኙት ለመንገርና ይዘውት ወደ ግብፅ ለመምጣት ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ከብዙ ዓመታት በኋላ ዮሴፍና አባቱ እንደገና ተገናኙ።

“የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላላችሁ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።”—ማቴዎስ 6:15