በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 17

ሙሴ ይሖዋን ለማምለክ መረጠ

ሙሴ ይሖዋን ለማምለክ መረጠ

የያዕቆብ ቤተሰቦች ወደ ግብፅ ከሄዱ በኋላ እስራኤላውያን ተብለው መጠራት ጀመሩ። ያዕቆብና ዮሴፍ ከሞቱ በኋላ አዲስ ፈርዖን በግብፅ ላይ መግዛት ጀመረ። ይህ ንጉሥ እስራኤላውያን ከግብፃውያን የበለጠ ኃያል እንዳይሆኑ ፈርቶ ነበር። ስለሆነም ፈርዖን እስራኤላውያንን ባሪያዎች አደረጋቸው። ጡብ እንዲሠሩ እንዲሁም በእርሻ ቦታ ላይ እንደ ባሪያ እንዲያገለግሉ አደረገ። ግብፃውያን እንደ ባሪያ ቢያሠሯቸውም የእስራኤላውያን ቁጥር እየጨመረ ሄደ። ፈርዖን ይህ ሁኔታ ስላሳሰበው እስራኤላውያን የሚወልዷቸው ወንዶች ልጆች በሙሉ እንዲገደሉ አዘዘ። እስራኤላውያን ምን ያህል ፈርተው ሊሆን እንደሚችል ልትገምት ትችላለህ?

በዚህ ጊዜ ዮካቤድ የተባለች አንዲት እስራኤላዊት የሚያምር ወንድ ልጅ ወለደች። ልጁ እንዳይገደል ስትል ቅርጫት ውስጥ አድርጋ በአባይ ወንዝ ዳር በሚገኝ ቄጠማ መሃል ደበቀችው። የልጁ እህት የሆነችው ሚርያም በአካባቢው ሆና የሚሆነውን ነገር ትከታተል ነበር።

የፈርዖን ሴት ልጅ ወንዙ ውስጥ ገላዋን ልትታጠብ ስትመጣ ቅርጫቱን አየችው። ቅርጫቱ ውስጥ ያለው ሕፃን እያለቀሰ መሆኑን ስታይ አዘነችለት። ሚርያምም ‘ልጁን እያጠባች የምታሳድግልሽ ሞግዚት ልፈልግልሽ?’ ብላ ጠየቀቻት። የፈርዖን ልጅ በሐሳቡ ስትስማማ ሚርያም እናቷን ዮካቤድን ይዛ መጣች። የፈርዖን ልጅ ዮካቤድን ‘ልጁን ተንከባክበሽ አሳድጊልኝ፤ እኔ ገንዘብ እከፍልሻለሁ’ አለቻት።

ልጁ ሲያድግ ዮካቤድ ወደ ፈርዖን ልጅ አመጣችው፤ የፈርዖን ልጅም ሙሴ ብላ ስም ያወጣችለት ሲሆን እንደ ራሷ ልጅ አድርጋ አሳደገችው። ሙሴ የንጉሥ ልጅ ሆኖ አደገ፤ በመሆኑም የፈለገውን ነገር ሁሉ ማግኘት ይችል ነበር። ሆኖም ሙሴ ይሖዋን አልረሳም። በፈርዖን ቤት ቢያድግም እስራኤላዊ እንጂ ግብፃዊ እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። ስለዚህ ይሖዋን ለማገልገል መረጠ።

ሙሴ 40 ዓመት ሲሞላው እስራኤላውያንን ለመርዳት ወሰነ። አንድ ግብፃዊ አንድን እስራኤላዊ ባሪያ ሲደበድብ አየና ግብፃዊውን መትቶ ገደለው። ከዚያም አሸዋ ውስጥ ደበቀው። ፈርዖን ይህን ሲሰማ ሙሴን ለመግደል ሞከረ። ሆኖም ሙሴ ሸሽቶ ወደ ምድያም ምድር ሄደ። እዚያ ከሄደ በኋላ ይሖዋ ሙሴን ተንከባክቦታል።

‘ሙሴ የፈርዖን የልጅ ልጅ ተብሎ ለመጠራት በእምነት እንቢ አለ፤ ከአምላክ ሕዝብ ጋር መንገላታትን መረጠ።’—ዕብራውያን 11:24, 25