በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 20

ስድስቱ መቅሰፍቶች

ስድስቱ መቅሰፍቶች

ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው ‘ሕዝቤን የማትለቅ ከሆነ በግብፅ ላይ ተናካሽ ዝንብ አመጣለሁ’ በማለት አምላክ የተናገረውን መልእክት ነገሩት። ተናካሽ ዝንቦች የግብፃውያንን ቤቶች በሙሉ ወረሩ። አገሪቱ በሙሉ በተናካሽ ዝንቦች ተሞላች። እስራኤላውያን በሚኖሩበት በጎሸን ምድር ግን ምንም ተናካሽ ዝንብ አልነበረም። ከዚህኛው ማለትም ከአራተኛው መቅሰፍት ጀምሮ ያሉት መቅሰፍቶች የጎዱት ግብፃውያንን ብቻ ነው። ፈርዖን ሙሴንና አሮንን ‘እነዚህን ዝንቦች እንዲያስወግድልኝ ይሖዋን ለምኑልኝ። ሕዝቡን እለቃለሁ’ አላቸው። ሆኖም ይሖዋ ተናካሽ ዝንቦቹን ሲያስወግድላቸው ፈርዖን ሐሳቡን ቀየረ። ፈርዖን ከስህተቱ የሚማረው መቼ ይሆን?

ይሖዋም ‘ፈርዖን ሕዝቤን የማይለቅ ከሆነ የግብፃውያን እንስሳት ታመው ይሞታሉ’ አለ። በቀጣዩ ቀን እንስሳቱ መሞት ጀመሩ። የእስራኤላውያን እንስሳት ግን አልሞቱም። በዚህ ጊዜም ቢሆን ፈርዖን ሕዝቡን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም።

ከዚያም ይሖዋ ሙሴን አመድ ይዞ ወደ ፈርዖን በመሄድ አመዱን አየር ላይ እንዲበትነው ነገረው። አመዱ አቧራ ሆኖ አየሩን ሞላውና በግብፃውያኑ ሁሉ ላይ አረፈ። በዚህ የተነሳ በግብፃውያንና በእንስሶቻቸው ሁሉ ላይ የሚያም ቁስል ወጣ። ፈርዖን ግን አሁንም እስራኤላውያንን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም።

ይሖዋ ሙሴን ወደ ፈርዖን መልሶ በመላክ ይህን መልእክት እንዲነግረው አዘዘው፦ ‘አሁንም ሕዝቤን አትለቅም ማለት ነው? ነገ በምድሪቱ ላይ በረዶ ይዘንባል።’ በቀጣዩ ቀን ይሖዋ በረዶ፣ ነጎድጓድና እሳት ላከ። ከዚያ በፊት በግብፅ ላይ እንዲህ ያለ ኃይለኛ ዝናብ ዘንቦ አያውቅም። ዛፎቹና ተክሎቹ በሙሉ ወደሙ፤ በጎሸን ያሉት ተክሎች ግን ምንም አልሆኑም። ፈርዖንም ‘ይሖዋ ይህን እንዲያስቆምልኝ ለምኑልኝ! ከዚያ መሄድ ትችላላችሁ’ አለ። ሆኖም ልክ በረዶውና ዝናቡ እንዳቆመ ፈርዖን ሐሳቡን ቀየረ።

ከዚያም ሙሴ ‘ከበረዶው የተረፈውን ተክል አንበጦች ይበሉታል’ አለ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ አንበጦች መጥተው በእርሻውና በዛፎቹ ላይ የቀረውን በሙሉ በሉት። በዚህ ጊዜ ፈርዖን ‘ይሖዋ እነዚህን አንበጦች እንዲያስወግድልኝ ለምኑልኝ’ አለ። ፈርዖን ግን ይሖዋ አንበጦቹን ካስወገዳቸው በኋላም ሕዝቡን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም።

ይሖዋ ሙሴን ‘እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ’ አለው። ወዲያውኑም ሰማዩ ሙሉ በሙሉ ጨለመ። ለሦስት ቀን ያህል ግብፃውያን ምንም ነገር ማየት አልቻሉም። እስራኤላውያን በሚኖሩበት አካባቢ ግን ብርሃን ነበር።

ፈርዖን ሙሴን እንዲህ አለው፦ ‘አንተና ሕዝብህ መሄድ ትችላላችሁ። እንስሶቻችሁን ግን እዚሁ ትታችሁ ሂዱ።’ ሙሴም ‘ለአምላካችን መሥዋዕት አድርገን ስለምናቀርባቸው እንስሶቻችንን መውሰድ አለብን’ አለው። በዚህ ጊዜ ፈርዖን በጣም ተናደደ። ‘ከፊቴ ጥፋ! ከዚህ በኋላ አጠገቤ ብትደርስ እገድልሃለሁ’ በማለት ጮኸበት።

“እናንተም በጻድቁና በክፉው እንዲሁም አምላክን በሚያገለግለውና በማያገለግለው ሰው መካከል ያለውን ልዩነት ዳግመኛ ታያላችሁ።”—ሚልክያስ 3:18