በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 21

አሥረኛው መቅሰፍት

አሥረኛው መቅሰፍት

ሙሴ ወደ ፈርዖን ተመልሶ እንደማይመጣ ተናገረ። ሆኖም ከፈርዖን ፊት ከመውጣቱ በፊት እንዲህ አለው፦ ‘እኩለ ሌሊት ላይ ከፈርዖን ልጅ ጀምሮ እስከ ባሪያው ልጅ ድረስ በግብፅ ያለ የበኩር ልጅ በሙሉ ይሞታል።’

ይሖዋ ለእስራኤላውያን ልዩ ራት አዘጋጅተው እንዲበሉ ነገራቸው። እንዲህ አላቸው፦ ‘አንድ ዓመት የሆነው በግ ወይም ፍየል አርዳችሁ ደሙን የቤታችሁ መግቢያ ላይ ቀቡት። ሥጋውን ጥበሱና ካልቦካ ቂጣ ጋር ብሉት። ልብሳችሁን ለብሳችሁና ጫማችሁን አድርጋችሁ ለጉዞ ተዘጋጁ። በዚህ ሌሊት ነፃ አወጣችኋለሁ።’ እስራኤላውያን ምን ያህል ተደስተው ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስበው።

እኩለ ሌሊት ላይ የይሖዋ መልአክ በግብፅ ወዳሉ ቤቶች በሙሉ ሄደ። መግቢያቸው ላይ ደም ባልተቀባባቸው ቤቶች ውስጥ ያሉት የበኩር ልጆች ሞቱ። ሆኖም መልአኩ ደም የተቀባባቸውን ቤቶች አልፎ ሄደ። በእያንዳንዱ የግብፃውያን ቤተሰብ ውስጥ ያለ የበኩር ልጅ ሁሉ ሞተ። ሆኖም ከእስራኤላውያን ልጆች መካከል አንዳቸውም አልሞቱም።

በዚህ ጊዜ የፈርዖን ልጅም ጭምር ሞተ። ፈርዖን ከዚህ በላይ ሊቋቋም አልቻለም። ወዲያውኑ ሙሴንና አሮንን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ ‘ተነሱ። ከዚህ ውጡ። አምላካችሁን አምልኩ። እንስሶቻችሁንም ይዛችሁ ሂዱ!’

ጨረቃዋ ሙሉ ሆና ትታይ በነበረበት በዚያ ሌሊት እስራኤላውያን በቤተሰብና በነገድ ተከፋፍለው ከግብፅ ወጡ። በዚያ ጊዜ ከግብፅ የወጡት እስራኤላውያን ወንዶች 600,000 ሲሆኑ በርካታ ሴቶችና ልጆችም ነበሩ። በተጨማሪም ከእስራኤላውያን ጋር ይሖዋን ለማምለክ የመረጡ ሌሎች ብዙ ሰዎች አብረዋቸው ሄዱ። በመጨረሻ እስራኤላውያን ነፃ ወጡ!

እስራኤላውያን ይሖዋ እንዴት እንዳዳናቸው ማስታወስ እንዲችሉ በየዓመቱ ያንን ልዩ ራት እንዲመገቡ ትእዛዝ ተሰጣቸው። ይህ ልዩ ራት ፋሲካ ይባላል።

“በሕይወት ያቆየሁህ ኃይሌን በአንተ ለማሳየትና ስሜ በመላው ምድር እንዲታወጅ ለማድረግ ነው።”—ሮም 9:17