በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 27

በይሖዋ ላይ ዓመፁ

በይሖዋ ላይ ዓመፁ

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ ቆሬ፣ ዳታን፣ አቤሮንና ሌሎች 250 ሰዎች በሙሴና በአሮን ላይ ዓመፁ። እንዲህም አሏቸው፦ ‘አላበዛችሁትም እንዴ! አንተ መሪያችን የሆንከው ለምንድን ነው? አሮንስ ሊቀ ካህናት የሆነው ለምንድን ነው? ይሖዋ ከእናንተ ጋር ብቻ ነው እንዴ? ከእኛም ጋር ነው።’ ይሖዋ ግን በዚህ አልተደሰተም። እነዚህ ሰዎች ልክ በራሱ ላይ እንዳመፁ አድርጎ ነበር የቆጠረው!

ሙሴም ቆሬንና ተባባሪዎቹን እንዲህ አላቸው፦ ‘ነገ የዕጣን ማጨሻዎቻችሁ ላይ ዕጣን ጨምራችሁ ወደ ማደሪያው ድንኳን ኑ። ይሖዋ ማንን እንደሚመርጥ እናያለን።’

በቀጣዩ ቀን ቆሬና አብረውት የነበሩት 250 ሰዎች ከሙሴ ጋር ለመገናኘት ወደ ማደሪያ ድንኳኑ ሄዱ። ዕጣን ማጨስ የሚፈቀድላቸው ካህናት ብቻ ቢሆኑም ዕጣን አጨሱ። ይሖዋ ሙሴንና አሮንን ‘ከቆሬና ከተባባሪዎቹ ራሳችሁን ለዩ’ አላቸው።

ቆሬ ከሙሴ ጋር ለመገናኘት ወደ ማደሪያ ድንኳኑ የሄደ ቢሆንም ዳታን፣ አቤሮንና ቤተሰቦቻቸው ወደዚያ ለመሄድ ፈቃደኞች አልሆኑም። ይሖዋ እስራኤላውያንን ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳን እንዲርቁ ነገራቸው። እስራኤላውያንም ወዲያውኑ እንደተባሉት አደረጉ። ዳታን፣ አቤሮንና ቤተሰቦቻቸው በድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቆሙ። ከዚያም በድንገት መሬቱ ተሰነጠቀና ዋጣቸው! በማደሪያ ድንኳኑ መግቢያ ላይ የነበሩትን ቆሬንና 250 ተባባሪዎቹን ደግሞ እሳት ከሰማይ ወርዶ አቃጠላቸው።

ይሖዋ በመቀጠል ሙሴን እንዲህ አለው፦ ‘ከእያንዳንዱ ነገድ አለቃ አንድ በትር ውሰድና የነገድ አለቃውን ስም ጻፍበት። ከሌዊ ነገድ በተወሰደው በትር ላይ ደግሞ የአሮንን ስም ጻፍ። ከዚያም በትሮቹን በማደሪያው ድንኳን ውስጥ አስቀምጣቸው፤ እኔ የምመርጠው ሰው በትር አበባ ያወጣል።’

በቀጣዩ ቀን ሙሴ በትሮቹን በሙሉ አምጥቶ ለነገድ አለቆቹ አሳያቸው። የአሮን በትር አበባ አውጥቶና የበሰለ የአልሞንድ ፍሬ አፍርቶ ነበር። በዚህ መንገድ ይሖዋ አሮንን ሊቀ ካህናት እንዲሆን የመረጠው እሱ እንደሆነ ማረጋገጫ ሰጠ።

“በመካከላችሁ ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ እንዲሁም ተገዙ።”—ዕብራውያን 13:17