በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 28

የበለዓም አህያ ተናገረች

የበለዓም አህያ ተናገረች

እስራኤላውያን በምድረ በዳ 40 ዓመት ገደማ ቆዩ። በእነዚህ ዓመታት በርካታ ከተሞችን ድል አድርገዋል። አሁን ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ በሚገኘው በሞዓብ ሜዳ ላይ ሰፍረዋል፤ ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚገቡበት ጊዜ በጣም ተቃርቧል። የሞዓብ ንጉሥ የሆነው ባላቅ እስራኤላውያን አገሩን እንዳይወስዱበት ፈርቷል። ስለዚህ በለዓም የሚባል አንድ ሰው ወደ ሞዓብ መጥቶ እስራኤላውያን መጥፎ ነገር እንዲደርስባቸው እንዲረግምለት ጠየቀው።

ይሖዋ ግን በለዓምን ‘እስራኤላውያንን እንዳትረግም’ አለው። ስለዚህ በለዓም ወደ ሞዓብ ለመሄድ ፈቃደኛ አልሆነም። ንጉሥ ባላቅ ለሁለተኛ ጊዜ መልእክተኞችን ልኮ በለዓምን እንዲመጣ ጠየቀው፤ ወደ ሞዓብ ከመጣ የፈለገውን ነገር እንደሚሰጠውም ቃል ገባለት። በለዓም ግን አሁንም እንቢ አለ። በዚህ ጊዜ አምላክ ‘መሄድ ትችላለህ፤ ግን የምትናገረው እኔ እንድትናገር የማዝህን ነገር ብቻ ነው’ አለው።

በለዓም አህያው ላይ ተቀምጦ ወደ ሞዓብ መጓዝ ጀመረ። ይሖዋ እስራኤላውያንን እንዳይረግም ቢያዘውም እሱ ግን እስራኤላውያንን ለመርገም አስቦ ነበር። በለዓም እየተጓዘ ሳለ የይሖዋ መልአክ መንገዱ ላይ ቆመ። በለዓም መልአኩን አላየውም፤ አህያዋ ግን አይታው ነበር። በመጀመሪያ አህያዋ መልአኩን ስታይ ከመንገድ ወጥታ እርሻ ውስጥ ገባች። ለሁለተኛ ጊዜ ስታየው ደግሞ ወደ አንድ ግንብ ተጠግታ የበለዓምን እግር ከግንቡ ጋር አጣበቀችው። ከዚያም መልአኩን ለሦስተኛ ጊዜ ስታየው መንገዱ መሃል ተኛች። በሦስቱም ጊዜያት በለዓም በዱላ ይደበድባት ነበር።

በመጨረሻ ይሖዋ አህያዋ እንድትናገር አደረገ። አህያዋ በለዓምን ‘እንዲህ የምትደበድበኝ ለምንድን ነው?’ አለችው። በለዓምም ‘ስለተጫወትሽብኝ ነዋ። ሰይፍ ይዤ ቢሆንማ ኖሮ እገድልሽ ነበር’ አላት። አህያዋም እንዲህ አለችው፦ ‘እስከ ዛሬ ለብዙ ዓመታት ተቀምጠህብኝ ነበር። ከዚህ በፊት እንዲህ አድርጌህ አውቃለሁ?’

ከዚያም ይሖዋ፣ በለዓም መልአኩን እንዲያየው አደረገ። በዚህ ጊዜ መልአኩ በለዓምን ‘ይሖዋ እስራኤልን እንዳትረግም አስጠንቅቆህ አልነበረም?’ አለው። በለዓምም ‘ጥፋት ሠርቻለሁ። በቃ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ’ አለ። መልአኩ ግን እንዲህ አለው፦ ‘ወደ ሞዓብ መሄድ ትችላለህ፤ ግን የምትናገረው ይሖዋ እንድትናገር ያዘዘህን ነገር ብቻ ነው።’

በለዓም ከስህተቱ ተምሯል? በጭራሽ። ከዚያ በኋላ በለዓም ሦስት ጊዜ እስራኤልን ለመርገም ሞክሮ ነበር፤ ይሖዋ ግን በሦስቱም ጊዜያት እንዲባርካቸው አደረገው። በኋላም እስራኤላውያን በሞዓብ ላይ ጥቃት ሰነዘሩ፤ በለዓምም ተገደለ። በለዓም መጀመሪያውኑ ይሖዋን ቢሰማ አይሻልም ነበር?

“አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ንብረቱ ሕይወት ሊያስገኝለት አይችልም፤ ስለዚህ ተጠንቀቁ፤ ከስግብግብነትም ሁሉ ተጠበቁ።”—ሉቃስ 12:15