በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 30

ረዓብ ሰላዮቹን ደበቀች

ረዓብ ሰላዮቹን ደበቀች

ኢያሱ የላካቸው ሰላዮች ወደ ኢያሪኮ ሄደው ረዓብ ወደምትባል ሴት ቤት ገቡ። የኢያሪኮ ንጉሥ፣ ሰላዮች መምጣታቸውን ስለሰማ ወደ ረዓብ ቤት ወታደሮችን ላከ። ረዓብ ሁለቱን ሰላዮች ጣሪያ ላይ ደበቀቻቸውና ወታደሮቹን በሌላ አቅጣጫ ላከቻቸው። ከዚያም ሰላዮቹን እንዲህ አለቻቸው፦ ‘ይሖዋ ከእናንተ ጋር እንደሆነና ምድሪቱን እንደሚሰጣችሁ ስለማውቅ እረዳችኋለሁ። እባካችሁ ቤተሰቤን እንደምታድኑልኝ ቃል ግቡልኝ።’

ሰላዮቹ ረዓብን እንዲህ አሏት፦ ‘በቤትሽ ያለ ማንኛውም ሰው ፈጽሞ ጉዳት እንደማይደርስበት ቃል እንገባልሻለን። መስኮትሽ ላይ ቀይ ገመድ አንጠልጥይ፤ እንዲህ ካደረግሽ ቤተሰብሽ ይድናል።’

ረዓብ ሰላዮቹን በመስኮት በኩል በገመድ አወረደቻቸው። እነሱም ወደ ተራሮች ሄደው ለሦስት ቀን ከተደበቁ በኋላ ወደ ኢያሱ ተመልሰው ሄዱ። ከዚያም እስራኤላውያን የዮርዳኖስን ወንዝ በመሻገር ከተማዋን ለመያዝ ተዘጋጁ። እስራኤላውያን ድል ካደረጓቸው ከተሞች የመጀመሪያዋ ኢያሪኮ ነበረች። ይሖዋ ለስድስት ቀናት ያህል በቀን አንዴ ከተማዋን እንዲዞሯት ነገራቸው። በሰባተኛው ቀን ግን ከተማዋን ሰባት ጊዜ ዞሯት። ከዚያም ካህናቱ ቀንደ መለከታቸውን ነፉ፤ ወታደሮቹ ደግሞ ባለ በሌለ ኃይላቸው ጮኹ። በዚህ ጊዜ የከተማዋ አጥር ፈራረሰ! ከአጥሩ ጋር ተያይዞ የተሠራው የረዓብ ቤት ግን አልፈረሰም። ረዓብ በይሖዋ ስለታመነች እሷም ሆነች ቤተሰቧ መትረፍ ችለዋል።

“ረዓብም መልእክተኞቹን በጥሩ ሁኔታ ተቀብላ ካስተናገደቻቸውና በሌላ መንገድ ከላከቻቸው በኋላ በሥራ አልጸደቀችም?”—ያዕቆብ 2:25