በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 33

ሩትና ናኦሚ

ሩትና ናኦሚ

በአንድ ወቅት እስራኤል ውስጥ ረሃብ ተከስቶ ስለነበር ናኦሚ የተባለች አንዲት እስራኤላዊት ከባሏና ከሁለት ወንዶች ልጆቿ ጋር ወደ ሞዓብ ምድር ሄደች። ከጊዜ በኋላ የናኦሚ ባል ሞተ። ከዚያም ወንዶች ልጆቿ፣ ሩትና ዖርፋ የተባሉ ሞዓባውያን ሴቶችን አገቡ። የሚያሳዝነው ነገር የናኦሚ ወንዶች ልጆችም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሞቱ።

ናኦሚ የረሃቡ ወቅት እንዳበቃ ስትሰማ ወደ እስራኤል ለመመለስ ወሰነች። ሩትና ዖርፋም አብረዋት ለመሄድ ተነሱ፤ ነገር ግን መንገድ ላይ ሳሉ ናኦሚ እንዲህ አለቻቸው፦ ‘ለልጆቼ ጥሩ ሚስቶች፣ ለእኔ ደግሞ ጥሩ ምራቶች ነበራችሁ። ሁለታችሁም ሌላ ባል ብታገቡ ደስ ይለኛል። ወደ ቤታችሁ ተመለሱ።’ ሴቶቹም ‘እኛ በጣም እንወድሻለን! ትተንሽ መሄድ አንፈልግም’ አሏት። ናኦሚ ግን በድጋሚ እንዲመለሱ ነገረቻቸው። በመጨረሻም ዖርፋ ተመለሰች፤ ሩት ግን ለመመለስ ፈቃደኛ አልሆነችም። በዚህ ጊዜ ናኦሚ ሩትን እንዲህ አለቻት፦ ‘ዖርፋ ወደ ሕዝቧና ወደ አማልክቷ ተመልሳለች። አንቺም አብረሻት ተመለሺ፤ ወደ እናትሽ ቤት ሂጂ።’ ሩት ግን ‘ትቼሽ አልሄድም። ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል’ አለቻት። ሩት እንዲህ ብላ ስትናገር ናኦሚ ምን የተሰማት ይመስልሃል?

ሩትና ናኦሚ እስራኤል የደረሱት ገብስ በሚታጨድበት ጊዜ ነበር። አንድ ቀን ሩት የተራረፈ እህል ለመሰብሰብ ቦዔዝ ወደተባለ ሰው እርሻ ሄደች፤ ቦዔዝ የረዓብ ልጅ ነበር። ቦዔዝ፣ ሩት በታማኝነት ናኦሚን ስትረዳ የቆየች ሞዓባዊት እንደሆነች ሰማ። ስለሆነም በእርሻ ቦታው ላይ የተወሰነ እህል ለሩት እንዲተዉላት ሠራተኞቹን ነገራቸው።

ማታ ላይ ናኦሚ ሩትን ‘ዛሬ ስትሠሪ የዋልሽው በማን እርሻ ውስጥ ነው?’ ብላ ጠየቀቻት። ሩትም ‘ቦዔዝ በተባለ ሰው እርሻ ውስጥ ነው’ አለቻት። ናኦሚም እንዲህ አለች፦ ‘ቦዔዝ እኮ የባሌ ዘመድ ነው። ከሌሎቹ ወጣት ሴቶች ጋር ሆነሽ በእሱ እርሻ ውስጥ መሥራትሽን ቀጥይ። በዚያ ምንም ችግር አይገጥምሽም።’

ሩት እህል የሚሰበሰብበት ጊዜ እስኪያበቃ ድረስ በቦዔዝ እርሻ ውስጥ መሥራቷን ቀጠለች። ቦዔዝ፣ ሩት ጎበዝ ሠራተኛና ጥሩ ሴት እንደሆነች አስተዋለ። በዚያ ዘመን አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ከሞተ ዘመዱ የሆነ ሰው የሟቹን ሚስት እንዲያገባ ይደረግ ነበር። ስለዚህ ቦዔዝ ሩትን አገባት። ከዚያም ኢዮቤድ የተባለ ልጅ ወለዱ፤ ኢዮቤድ ከጊዜ በኋላ የንጉሥ ዳዊት አያት ሆኗል። የናኦሚ ጓደኞች በጣም ተደሰቱ። በመሆኑም ናኦሚን እንዲህ አሏት፦ ‘ይሖዋ በመጀመሪያ ጥሩ ረዳት እንድትሆንሽ ሩትን ሰጠሽ፤ አሁን ደግሞ የልጅ ልጅ አገኘሽ። ይሖዋ የተመሰገነ ይሁን።’

“ከወንድም ይበልጥ የሚቀርብ ጓደኛ አለ።”—ምሳሌ 18:24