በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 34

ጌድዮን ምድያማውያንን አሸነፈ

ጌድዮን ምድያማውያንን አሸነፈ

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ እስራኤላውያን እንደገና ይሖዋን በመተው የሐሰት አማልክትን ማምለክ ጀመሩ። ለሰባት ዓመታት ያህል ምድያማውያን የእስራኤላውያንን እንስሳት ይሰርቁ እንዲሁም እርሻቸውን ያበላሹ ነበር። እስራኤላውያን ከምድያማውያን ለማምለጥ ሲሉ በዋሻዎች ውስጥና በተራሮች ላይ ይደበቁ ነበር። በመጨረሻም እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ጮኹ። ስለዚህ ይሖዋ፣ ጌድዮን ወደተባለ አንድ ወጣት መልአኩን ላከ። መልአኩ ጌድዮንን ‘ይሖዋ ኃያል ተዋጊ እንድትሆን መርጦሃል’ አለው። ጌድዮንም ‘እንዴት እስራኤልን ላድን እችላለሁ? እኔ እንዲህ ለማድረግ የሚያስችል አቅም የለኝም’ አለ።

ጌድዮን፣ ይሖዋ እንደመረጠው በእርግጠኝነት ማወቅ የሚችለው እንዴት ነው? መሬት ላይ የበግ ፀጉር ካስቀመጠ በኋላ ይሖዋን እንዲህ አለው፦ ‘ጠዋት ላይ የበጉ ፀጉር በጤዛ ርሶ በዙሪያው ያለው መሬት በሙሉ ደረቅ ከሆነ፣ እኔ እስራኤልን እንዳድን እንደምትፈልግ በዚህ አውቃለሁ።’ በማግስቱ ጠዋት መሬቱ በሙሉ ደረቅ ቢሆንም የበጉ ፀጉር ረጥቦ አገኘው! ከዚያም ጌድዮን በቀጣዩ ቀን የበጉ ፀጉር ደረቅ ሆኖ ዙሪያው ያለው መሬት እርጥብ እንዲሆን ጠየቀ። ጌድዮን ይህ መፈጸሙን ሲያይ በእርግጥ ይሖዋ እንደመረጠው አመነ። ስለዚህ ከምድያማውያን ጋር ለመዋጋት ወታደሮቹን ሰበሰበ።

ይሖዋ ጌድዮንን እንዲህ አለው፦ ‘እስራኤላውያን እንዲያሸንፉ አደርጋለሁ። ግን ወታደሮቹ በጣም ብዙ ስለሆኑ ውጊያውን ያሸነፋችሁት በራሳችሁ ኃይል እንደሆነ ልታስቡ ትችላላችሁ። ስለዚህ የፈሩ ሁሉ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ንገራቸው።’ በመሆኑም 22,000 ወታደሮች ወደ ቤታቸው ተመልሰው 10,000 ወታደሮች ብቻ ቀሩ። ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለ፦ ‘አሁንም ወታደሮቹ በጣም ብዙ ናቸው። ወታደሮቹን ወደ ወንዙ ውሰዳቸውና ውኃ እንዲጠጡ ንገራቸው። ውኃ በሚጠጡበት ጊዜ ንቁ ሆነው ጠላት መምጣቱን የሚከታተሉትን ብቻ ከአንተ ጋር አስቀር።’ በንቃት እየተከታተሉ ውኃ የጠጡት 300 ሰዎች ብቻ ነበሩ። ይሖዋም እነዚህ ጥቂት ሰዎች 135,000ዎቹን የምድያም ወታደሮች እንደሚያሸንፉ ቃል ገባ።

በዚያ ቀን ምሽት ላይ ይሖዋ ጌድዮንን ‘አሁን ምድያማውያን ላይ ጥቃት ሰንዝር!’ አለው። ጌድዮን ለሰዎቹ ቀንደ መለከትና በውስጣቸው ችቦ ያለባቸው ትላልቅ ማሰሮዎች ሰጣቸው። ከዚያም ‘እኔን ተመልከቱና ልክ እንደማደርገው አድርጉ’ አላቸው። ጌድዮን ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ ማሰሮውንም ሰበረ፤ ከዚያም ችቦውን በእጁ ያዘና ‘የይሖዋና የጌድዮን ሰይፍ!’ ብሎ ጮኸ። አብረውት የነበሩት 300 ሰዎችም ተመሳሳይ ነገር አደረጉ። ምድያማውያኑ ፈርተው በሁሉም አቅጣጫ ሸሹ። በዚህ ጊዜ ትርምስ ስለተፈጠረ እርስ በርስ መዋጋት ጀመሩ። እስራኤላውያን ይሖዋ ስለረዳቸው በድጋሚ ጠላቶቻቸውን አሸነፉ።

“ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነው ኃይል ከእኛ ሳይሆን ከአምላክ የመነጨ መሆኑ [እንዲታወቅ ነው]።”—2 ቆሮንቶስ 4:7