በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 40

ዳዊት እና ጎልያድ

ዳዊት እና ጎልያድ

ይሖዋ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ ‘ወደ እሴይ ቤት ሂድ። ከእሴይ ልጆች መካከል አንዱ ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ ይሆናል።’ ስለዚህ ሳሙኤል ወደ እሴይ ቤት ሄደ። ከዚያም የመጀመሪያ ልጁን ሲያይ ‘ይሖዋ የመረጠው ይህን ወጣት መሆን አለበት’ ብሎ አሰበ። ይሖዋ ግን ሳሙኤልን ‘የመረጥኩት እሱን አይደለም። እኔ የማየው የሰውን መልክ ብቻ ሳይሆን እውነተኛ ባሕርይውን ጭምር ነው’ አለው።

እሴይ ሌሎቹን ስድስት ልጆቹን ጠርቶ ሳሙኤል ፊት አቀረባቸው። ሳሙኤል ግን ‘ይሖዋ እነዚህንም አልመረጣቸውም። ሌላ ልጅ የለህም?’ አለው። እሴይም ‘የመጨረሻው ልጄ ዳዊት አለ። ውጭ በጎቹን እየጠበቀ ነው’ አለ። ዳዊት ወደ ቤት ሲገባ ይሖዋ ሳሙኤልን ‘የመረጥኩት እሱን ነው!’ አለው። ሳሙኤልም በዳዊት ራስ ላይ ዘይት በማፍሰስ ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን ቀባው።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እስራኤላውያን ከፍልስጤማውያን ጋር ለመዋጋት ተሰለፉ፤ ፍልስጤማውያን ጎልያድ የሚባል ግዙፍ ተዋጊ ነበራቸው። ጎልያድ በየቀኑ በእስራኤላውያን ላይ ያሾፍ ነበር። ‘ከእኔ ጋር የሚዋጋ ሰው ካለ ይምጣ። እሱ ካሸነፈኝ እኛ የእናንተ ባሪያዎች እንሆናለን። እኔ ካሸነፍኩት ደግሞ እናንተ የእኛ ባሪያዎች ትሆናላችሁ’ እያለ ይጮኽ ነበር።

የዳዊት ወንድሞች ወታደሮች ስለነበሩ ዳዊት ለእነሱ ምግብ ለማድረስ ወደ እስራኤል ጦር ሰፈር መጣ። ከዚያም ጎልያድ የሚናገረውን ሲሰማ ‘እኔ እዋጋዋለሁ!’ አለ። ንጉሥ ሳኦል ግን ‘አንተ እኮ ገና ልጅ ነህ’ አለው። ዳዊትም ‘ይሖዋ ይረዳኛል’ በማለት መለሰ።

ሳኦል የጦር ልብሱን ለዳዊት ሊሰጠው ፈልጎ ነበር፤ ዳዊት ግን ‘ይህን ለብሼ መዋጋት አልችልም’ አለ። ከዚያም ዳዊት ወንጭፉን ይዞ ወደ ወንዝ ሄደ። አምስት ድቡልቡል ድንጋዮች መረጠና ኮሮጆው ውስጥ ጨመራቸው። ከዚያም ወደ ጎልያድ እየሮጠ ሄደ። ጎልያድም ‘እስቲ ወደዚህ ና። ሥጋህን ለሰማይ አሞሮችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ’ በማለት ጮኸበት። ዳዊት ግን አልፈራም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ሰይፍና ጦር ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን በይሖዋ ስም እመጣብሃለሁ። የምትዋጋው ከእኛ ጋር ሳይሆን ከአምላክ ጋር ነው። እዚህ ያሉት ሰዎች ሁሉ ይሖዋ ከሰይፍ ወይም ከጦር የበለጠ ኃይል እንዳለው ያያሉ። ሁላችሁንም በእጃችን አሳልፎ ይሰጣችኋል።’

ዳዊትም አንድ ድንጋይ ወንጭፉ ላይ አድርጎ ባለ በሌለ ኃይሉ አሽከረከረው። ይሖዋ ዳዊትን ስለረዳው ድንጋዩ ሄዶ የጎልያድ ግንባር ውስጥ ተቀረቀረ። ከዚያም ግዙፉ ጎልያድ መሬት ላይ ተደፋ፤ በዚህ ሁኔታ ዳዊት ጎልያድን ገደለው። ፍልስጤማውያንም ሸሹ። አንተስ እንደ ዳዊት በይሖዋ ትተማመናለህ?

“ይህ በሰዎች ዘንድ አይቻልም፤ በአምላክ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ በአምላክ ዘንድ ሁሉ ነገር ይቻላል።”—ማርቆስ 10:27