በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 44

የይሖዋ ቤተ መቅደስ

የይሖዋ ቤተ መቅደስ

ሰለሞን የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ በኋላ ይሖዋ ‘ምን እንድሰጥህ ትፈልጋለህ?’ በማለት ጠየቀው። ሰለሞንም እንዲህ አለ፦ ‘እኔ ገና ልጅ ነኝ፤ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም። እባክህ ሕዝብህን መምራት እንድችል ጥበብ ስጠኝ።’ ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለው፦ ‘ጥበብ እንድሰጥህ ስለጠየቅክ በምድር ላይ ካሉ ሰዎች ሁሉ የበለጠ ጥበበኛ አደርግሃለሁ። ብዙ ሀብትም እሰጥሃለሁ። እኔን ከታዘዝክ ረጅም ዕድሜ ትኖራለህ።’

ሰለሞን ቤተ መቅደሱን መገንባት ጀመረ። ምርጥ የሆነውን ወርቅ፣ ብር፣ እንጨትና ድንጋይ ተጠቅሞ ቤተ መቅደሱን ገነባ። በሺዎች የሚቆጠሩ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ወንዶችና ሴቶች ቤተ መቅደሱን በመገንባቱ ሥራ ተካፍለዋል። ከሰባት ዓመት በኋላ ቤተ መቅደሱ ተሠርቶ አለቀ፤ ከዚያም ቤተ መቅደሱን ለይሖዋ ለመወሰን ዝግጅት ተደረገ። በዚያም መሠዊያ ይገኝ የነበረ ሲሆን ቤተ መቅደሱ ለይሖዋ በተወሰነበት ጊዜ መሠዊያው ላይ መሥዋዕት ቀርቦ ነበር። ሰለሞን በመሠዊያው ፊት ተንበርክኮ እንዲህ በማለት ጸለየ፦ ‘ይሖዋ ሆይ፣ የዚህ ቤተ መቅደስ መጠንም ሆነ ውበት ለአንተ በጣም ያንስሃል፤ ግን እባክህ አምልኳችንን ተቀበል፤ ጸሎታችንንም ስማ።’ ታዲያ ይሖዋ ሰለሞን የገነባውን ቤተ መቅደስም ሆነ ያቀረበውን ጸሎት ተቀብሎታል? ሰለሞን ጸሎቱን እንደጨረሰ እሳት ከሰማይ ወርዶ በመሠዊያው ላይ የቀረበውን መሥዋዕት አቃጠለ። ይሖዋ በዚህ መንገድ ቤተ መቅደሱን እንደተቀበለው አሳየ። እስራኤላውያንም ይህን ሲያዩ በጣም ተደሰቱ።

በመላው እስራኤልም ሆነ ራቅ ብለው በሚገኙ ቦታዎች የነበሩ ሰዎች በንጉሥ ሰለሞን ጥበብ ይደነቁ ነበር። ሰዎች ችግር ሲገጥማቸው መፍትሔ ለማግኘት ወደ ሰለሞን ይመጡ ነበር። የሳባ ንግሥትም ከባድ ጥያቄዎች በመጠየቅ ልትፈትነው መጥታ ነበር። ለጥያቄዎቿ የሰጠውን መልስ ስትሰማ ግን እንዲህ አለች፦ ‘ሰዎች ስለ አንተ የነገሩኝን ነገር አላመንኩም ነበር፤ አሁን ግን እነሱ ከተናገሩትም በላይ ጥበበኛ እንደሆንክ አይቻለሁ። አምላክህ ይሖዋ ባርኮሃል።’ ሰለሞን ይገዛ በነበረበት ዘመን እስራኤላውያን አስደሳች ሕይወት ይኖሩ ነበር። ሆኖም ከጊዜ በኋላ ሁኔታዎች ተለወጡ።

“ከሰለሞን የሚበልጥ እዚህ አለ።”—ማቴዎስ 12:42