በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 45

የእስራኤል መንግሥት ተከፈለ

የእስራኤል መንግሥት ተከፈለ

ሰለሞን ይሖዋን ያመልክ በነበረበት ጊዜ ሁሉ በእስራኤል ውስጥ ሰላም ነበር። ሆኖም ሰለሞን ከተለያዩ አገሮች የመጡ ብዙ ሚስቶችን አገባ፤ እነዚህ ሴቶች ደግሞ ጣዖት ያመልኩ ነበር። ከጊዜ በኋላ ሰለሞንም ጣዖት ማምለክ ጀመረ። ይሖዋ በዚህ በጣም ተናደደ። ስለዚህ ሰለሞንን እንዲህ አለው፦ ‘የእስራኤል መንግሥት ለሁለት ይከፈላል። ትልቁን ክፍል ከአንተ ቤተሰብ ላይ ወስጄ ከአገልጋዮችህ ለአንዱ እሰጠዋለሁ፤ የአንተ ቤተሰብ የሚገዛው ትንሹን ብቻ ይሆናል።’

ይሖዋ ይህን ውሳኔውን በሌላ መንገድም ገለጸ። ከሰለሞን አገልጋዮች አንዱ የሆነው ኢዮርብዓም በመንገድ ላይ ሲሄድ ነቢዩ አኪያህን አገኘው። አኪያህም የራሱን ልብስ 12 ቦታ ቀደደና ኢዮርብዓምን እንዲህ አለው፦ ‘ይሖዋ የእስራኤልን መንግሥት ከሰለሞን ቤተሰብ ወስዶ ለሁለት ይከፍለዋል። አንተ በአሥር ነገዶች ላይ ንጉሥ ስለምትሆን አሥሩን ቁራጭ ውሰድ።’ ንጉሥ ሰለሞን ይህን ሲሰማ ኢዮርብዓምን ለመግደል ፈለገ! ስለዚህ ኢዮርብዓም ወደ ግብፅ ሸሸ። ከጊዜ በኋላ ሰለሞን ሞተና ልጁ ሮብዓም ነገሠ። በዚህ ጊዜ ኢዮርብዓም ወደ እስራኤል ቢመለስ ምንም ችግር እንደማያጋጥመው ተሰማው።

የእስራኤል ሽማግሌዎች ሮብዓምን ‘ለሕዝቡ መልካም ነገር የምታደርግ ከሆነ ለአንተ ታማኝ ይሆናሉ’ አሉት። ወጣት ጓደኞቹ ግን ‘ሕዝቡን በጭካኔ መግዛት አለብህ! እንዲያውም የበለጠ እንዲሠሩ አድርጋቸው!’ አሉት። ሮብዓም የወጣቶቹን ምክር ተቀበለ። ሕዝቡን በጭካኔ ይገዛ ጀመር፤ ስለዚህ አሥሩ የእስራኤል ነገዶች በሮብዓም ላይ ዓመፁ። ከዚያም ኢዮርብዓምን በአሥሩ ነገዶች ላይ ንጉሥ አደረጉት፤ ይህ የአሥሩ ነገድ መንግሥት የእስራኤል መንግሥት ተብሎ ይጠራ ጀመር። የቀሩት ሁለት ነገዶች መንግሥት ደግሞ የይሁዳ መንግሥት ተብሎ ይጠራ ጀመር፤ ሁለቱ ነገዶች ለሮብዓም ታማኝ ሆኑ። በዚህ መንገድ አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ተከፈሉ።

ኢዮርብዓም ሕዝቡ ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ አልፈለገም፤ ምክንያቱም ኢየሩሳሌም የምትገኘው በሮብዓም ግዛት ውስጥ ነበር። ኢዮርብዓም ‘ሕዝቡ ወደዚያ ከሄደ በእኔ ላይ ዓምፆ ሮብዓምን ሊደግፍ ይችላል’ ብሎ አሰበ። ስለዚህ ሁለት የወርቅ ጥጃዎች ሠርቶ እስራኤላውያንን እንዲህ አላቸው፦ ‘ኢየሩሳሌም በጣም ይርቃችኋል። እዚሁ ማምለክ ትችላላችሁ።’ በመሆኑም ሕዝቡ እንደገና ይሖዋን ትቶ የወርቅ ጥጃዎቹን ማምለክ ጀመረ።

“ከማያምኑ ጋር አቻ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ። ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ኅብረት አለው? . . . ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ድርሻ አለው?”—2 ቆሮንቶስ 6:14, 15