በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 46

ይሖዋ እውነተኛ አምላክ መሆኑን አሳየ

ይሖዋ እውነተኛ አምላክ መሆኑን አሳየ

በአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ላይ የነገሡት ብዙዎቹ ነገሥታት ክፉዎች ነበሩ፤ ንጉሥ አክዓብ ደግሞ በጣም ክፉ ከነበሩት ነገሥታት አንዱ ነው። አክዓብ የባአል አምላኪ የሆነች አንዲት ክፉ ሴት አገባ። ስሟ ኤልዛቤል ይባላል። አክዓብና ኤልዛቤል በአገሪቱ ውስጥ የባአል አምልኮ እንዲስፋፋ አድርገዋል፤ እንዲሁም የይሖዋን ነቢያት ገድለዋል። ታዲያ ይሖዋ ምን አደረገ? በነቢዩ ኤልያስ አማካኝነት ለአክዓብ መልእክት ላከ።

ኤልያስ ንጉሥ አክዓብን ‘አንተ በፈጸምከው ክፋት የተነሳ በእስራኤል ምድር ዝናብ አይዘንብም’ አለው። በምድሪቱ ላይ እህል መብቀል ካቆመ ከሦስት ዓመት በላይ አልፏል፤ ስለዚህ ሕዝቡ ተራበ። በኋላም ይሖዋ በድጋሚ ኤልያስን ወደ አክዓብ ላከው። በዚህ ጊዜ ንጉሡ ኤልያስን ‘አንተ ችግር ፈጣሪ ነህ! ይህ ሁሉ ችግር የመጣው በአንተ ምክንያት ነው’ አለው። ኤልያስም እንዲህ አለ፦ ‘ይህ ድርቅ የመጣው በእኔ ምክንያት አይደለም። ድርቁ የመጣው አንተ ባአልን በማምለክህ ነው። አሁን እውነተኛው አምላክ ማን እንደሆነ ይታያል። ሕዝቡንና የባአልን ነቢያት በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ሰብስብ።’

ሕዝቡ በተራራው ላይ ተሰበሰበ። ኤልያስም እንዲህ አለ፦ ‘አንዱን ምረጡ። እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ከሆነ እሱን ተከተሉ። እውነተኛው አምላክ ባአል ከሆነ ደግሞ እሱን ተከተሉ። አሁን 450ዎቹ የባአል ነቢያት መሥዋዕት ያዘጋጁና ወደ አምላካቸው ይጸልዩ፤ እኔም መሥዋዕት አዘጋጅቼ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። እሳት በመላክ መልስ የሚሰጠው አምላክ እሱ እውነተኛው አምላክ ነው።’ ሕዝቡም በሐሳቡ ተስማማ።

የባአል ነቢያት መሥዋዕት አዘጋጁ። ከዚያም ቀኑን ሙሉ ‘ባአል ሆይ፣ መልስልን!’ እያሉ ሲጮኹ ዋሉ። ባአል ምንም መልስ ሳይሰጥ ሲቀር ኤልያስ በባአል ማሾፍ ጀመረ። እንዲህ አለ፦ ‘ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ እንጂ። ተኝቶ ሊሆን ስለሚችል የሚቀሰቅሰው ያስፈልገው ይሆናል።’ የባአል ነቢያት እስከ ምሽት ድረስ መጣራታቸውን ቀጠሉ። ግን ምንም መልስ አልነበረም።

ኤልያስ መሥዋዕቱን በመሠዊያው ላይ አስቀመጠና ውኃ አፈሰሰበት። ከዚያም ‘ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ እውነተኛው አምላክ አንተ መሆንህን ለሕዝቡ አሳውቃቸው’ በማለት ጸለየ። ይሖዋም ወዲያውኑ ከሰማይ እሳት በመላክ መሥዋዕቱን አቃጠለው። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ‘እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ነው!’ በማለት ጮኸ። ከዚያም ኤልያስ ‘የባአል ነቢያት እንዳያመልጡ ያዟቸው!’ አለ። በዚያ ቀን 450ዎቹ የባአል ነቢያት ተገደሉ።

ከባሕሩ በላይ ትንሽ ደመና ሲታይ ኤልያስ አክዓብን ‘ከባድ ዝናብ እየመጣ ነው። ሠረገላህን አዘጋጅና ወደ ቤት ሂድ’ አለው። ሰማዩ በደመና ጠቆረ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ከባድ ዝናብም መጣል ጀመረ። በመጨረሻ የድርቁ ወቅት አበቃ። አክዓብ ሠረገላውን በፍጥነት እየነዳ ሄደ። ኤልያስ ግን እየሮጠ በይሖዋ እርዳታ ከሠረገላው ቀድሞ ሄደ! ታዲያ የኤልያስ ችግር ሙሉ በሙሉ ተወገደ ማለት ነው? እስቲ እንመልከት።

“ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ አዎ፣ አንተ ብቻ በመላው ምድር ላይ ልዑል እንደሆንክ ሰዎች ይወቁ።”—መዝሙር 83:18