በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 48

የአንዲት ድሃ ሴት ልጅ ከሞት ተነሳ

የአንዲት ድሃ ሴት ልጅ ከሞት ተነሳ

በድርቁ ወቅት ይሖዋ ኤልያስን እንዲህ አለው፦ ‘ወደ ሰራፕታ ሂድ። በዚያ የምትኖር አንዲት ባሏ የሞተባት ሴት ምግብ ትሰጥሃለች።’ ኤልያስ ወደ ከተማዋ መግቢያ እንደደረሰ ይሖዋ በነገረው መሠረት አንዲት ድሃ ሴት እንጨት ስትለቅም አየ። ከዚያም የሚጠጣው ውኃ እንድትሰጠው ጠየቃት። ውኃ ለማምጣት ስትሄድ ድጋሚ ጠራትና ‘እባክሽ ቁራሽ ዳቦም ይዘሽልኝ ነይ’ አላት። ሴትየዋ ግን ‘የምሰጥህ ዳቦ የለኝም። እንዳልጋግርልህ እንኳ ያለኝ ዱቄትና ዘይት ለእኔና ለልጄ ትንሽ ዳቦ ለመጋገር ብቻ የሚበቃ ነው’ አለችው። ኤልያስም ‘ለእኔ ዳቦ ከጋገርሽልኝ ዳግመኛ ዝናብ እስኪዘንብ ድረስ ዱቄቱና ዘይቱ እንደማያልቅ ይሖዋ ተናግሯል’ አላት።

ስለዚህ ሴትየዋ ወደ ቤት ገብታ ለይሖዋ ነቢይ ዳቦ ጋገረችለት። ልክ ይሖዋ ቃል እንደገባው በድርቁ ወቅት ሴትየዋና ልጇ የሚበሉት ምግብ አላጡም። ዱቄቱም ሆነ ዘይቱ አላለቀም።

ከዚያም አንድ በጣም የሚያሳዝን ነገር ተፈጠረ። የሴትየዋ ልጅ በጣም ታመመና ሞተ። እሷም ኤልያስን እንዲረዳት ለመነችው። ኤልያስም ትንሹን ልጅ ከእሷ ተቀብሎ በሰገነቱ ላይ ወዳለ ክፍል ወሰደው። ከዚያም አልጋ ላይ አስተኛውና ‘ይሖዋ፣ እባክህ ይህን ልጅ አስነሳው’ በማለት ጸለየ። ይሖዋ ልጁን ከሞት ቢያስነሳው በጣም አስደናቂ ተአምር ይሆናል። ምክንያቱም እስከምናውቀው ድረስ ከዚያ በፊት ማንም ሰው ከሞት ተነስቶ አያውቅም። በተጨማሪም ይህች ሴትና ልጇ እስራኤላውያን አልነበሩም።

ሆኖም የልጁ ሕይወት ተመለሰለትና መተንፈስ ጀመረ! ኤልያስም ሴትየዋን ‘ይኸው! ልጅሽ ተነስቷል’ አላት። እሷም በጣም ተደስታ ኤልያስን እንዲህ አለችው፦ ‘አንተ በእርግጥም የአምላክ ሰው ነህ። ምክንያቱም የምትናገረው ይሖዋ እንድትናገር ያዘዘህን ነገር ብቻ ነው፤ የተናገርከውም ነገር ሁልጊዜ ይፈጸማል።’

“ቁራዎችን ተመልከቱ፦ አይዘሩም፣ አያጭዱም እንዲሁም የእህል ማከማቻ ወይም ጎተራ የላቸውም፤ ሆኖም አምላክ ይመግባቸዋል። ታዲያ እናንተ ከወፎች እጅግ የላቀ ዋጋ የላችሁም?”—ሉቃስ 12:24