በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 49

ክፉዋ ንግሥት ተቀጣች

ክፉዋ ንግሥት ተቀጣች

በኢይዝራኤል ከሚገኘው የንጉሥ አክዓብ ቤተ መንግሥት አጠገብ ናቡቴ የተባለ ሰው የወይን እርሻ ይገኝ ነበር። አክዓብ ይህን የወይን እርሻ የራሱ ማድረግ ስለፈለገ እርሻውን እንዲሸጥለት ናቡቴን ጠየቀው። ሆኖም የይሖዋ ሕግ በውርስ የተላለፈ መሬት እንዳይሸጥ ይከለክል ስለነበር ናቡቴ እርሻውን ለመሸጥ ፈቃደኛ አልሆነም። ናቡቴ ትክክለኛውን ነገር በማድረጉ አክዓብ ናቡቴን አመሰገነው? በፍጹም። አክዓብ በጣም ተናደደ። ከመበሳጨቱም የተነሳ አኩርፎ ተኛ፤ ምግብ ለመብላትም ፈቃደኛ አልሆነም።

የአክዓብ ሚስት የሆነችው ክፉዋ ንግሥት ኤልዛቤል አክዓብን እንዲህ አለችው፦ ‘አንተ እኮ የእስራኤል ንጉሥ ነህ። የፈለግከውን ነገር ማግኘት ትችላለህ። ያንን መሬት እኔ እሰጥሃለሁ።’ ከዚያም ለከተማዋ ሽማግሌዎች ደብዳቤ በመጻፍ ናቡቴን ‘አምላክን ሰድቧል’ ብለው እንዲከሱትና በድንጋይ ወግረው እንዲገድሉት ነገረቻቸው። ሽማግሌዎቹም ኤልዛቤል እንደነገረቻቸው አደረጉ፤ ከዚያም ኤልዛቤል አክዓብን ‘ናቡቴ ሞቷል። አሁን የወይን እርሻውን መውሰድ ትችላለህ’ አለችው።

ኤልዛቤል ያስገደለችው ናቡቴን ብቻ አልነበረም። ይሖዋን የሚወዱ ሌሎች ብዙ ሰዎችንም አስገድላለች። ጣዖት ታመልክ እንዲሁም ብዙ መጥፎ ነገሮች ታደርግ ነበር። ይሖዋ ኤልዛቤል ያደረገችውን መጥፎ ነገር በሙሉ አይቷል። ታዲያ ምን ያደርጋት ይሆን?

አክዓብ ከሞተ በኋላ ልጁ ኢዮራም ነገሠ። ይሖዋም ኤልዛቤልንና ቤተሰቧን እንዲቀጣ ኢዩ የተባለ ሰው ላከ።

ኢዩ ሠረገላውን እየነዳ ኤልዛቤል ወደምትኖርበት ወደ ኢይዝራኤል ሄደ። ኢዮራምም ሠረገላው ላይ ተቀምጦ ኢዩን ለማግኘት ወጣ፤ ከዚያም ኢዩን ‘የመጣኸው በሰላም ነው?’ ብሎ ጠየቀው። ኢዩም ‘እናትህ ኤልዛቤል ክፉ ነገር ማድረጓን እስካልተወች ድረስ ምንም ሰላም የለም’ አለው። ኢዮራም ይህን ሲሰማ ሠረገላውን አዙሮ ለማምለጥ ሞከረ። ሆኖም ኢዩ በቀስት ስለወጋው ኢዮራም ሞተ።

ከዚያም ኢዩ ወደ ኤልዛቤል ቤተ መንግሥት ሄደ። ኤልዛቤልም ኢዩ እየመጣ መሆኑን ስትሰማ ተኳኩላና ፀጉሯን አሰማምራ ፎቅ ላይ ባለው መስኮት በኩል ትመለከት ጀመር። ኢዩ ሲደርስ ኤልዛቤል በንቀት አናገረችው። ኢዩም ከእሷ ጎን ቆመው የነበሩትን አገልጋዮቿን ‘ወደ ታች ወርውሯት!’ አላቸው። እነሱም ኤልዛቤልን በመስኮት ወረወሯት፤ እሷም መሬት ላይ ወድቃ ሞተች።

ከዚያ በኋላ ኢዩ የአክዓብን 70 ወንዶች ልጆች አስገደለ፤ እንዲሁም የባአልን አምልኮ ከምድሪቱ ላይ አስወገደ። ይሖዋ ሁሉንም ነገር እንደሚያውቅና መጥፎ ነገር የሚሠሩ ሰዎችን በተገቢው ጊዜ እንደሚቀጣቸው አስተዋልክ?

“በመጀመሪያ በስግብግብነት የተገኘ ውርስ፣ የኋላ ኋላ በረከት አይሆንም።”—ምሳሌ 20:21