በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 51

የሠራዊቱ አለቃና ትንሿ ልጅ

የሠራዊቱ አለቃና ትንሿ ልጅ

ከትውልድ አገሯ ርቃ በሶርያ የምትኖር አንዲት እስራኤላዊት ልጅ ነበረች። ይህችን ልጅ የሶርያ ሠራዊት ከቤተሰቧ ለይቶ ወስዷት ነበር። በዚያም ንዕማን የተባለ አንድ የሠራዊት አለቃ ነበር፤ እስራኤላዊቷ ልጅ የንዕማን ሚስት አገልጋይ ሆነች። አብረዋት ያሉት ሰዎች ይሖዋን ባያመልኩም እንኳ ይህች ትንሽ ልጅ ይሖዋን ታመልክ ነበር።

ንዕማን ከባድ የቆዳ በሽታ ነበረበት፤ በዚህ የተነሳ ሁልጊዜ ይሠቃይ ነበር። ትንሿ ልጅ ንዕማንን መርዳት ፈለገች። ስለዚህ የንዕማንን ሚስት እንዲህ አለቻት፦ ‘ባልሽን ሊረዳው የሚችል ሰው አውቃለሁ። እስራኤል ውስጥ ኤልሳዕ የሚባል የይሖዋ ነቢይ አለ። እሱ ባልሽን ከሕመሙ ሊያድነው ይችላል።’

የንዕማን ሚስት ትንሿ ልጅ ያለቻትን ነገር ለባሏ ነገረችው። ንዕማንም ከሕመሙ ለመዳን ጓጉቶ ስለነበር በእስራኤል ወደሚገኘው የኤልሳዕ ቤት ሄደ። ንዕማን፣ ኤልሳዕ ትልቅ አቀባበል ያደርግልኛል ብሎ ጠብቆ ነበር። ኤልሳዕ ግን ራሱ ወጥቶ ንዕማንን ከማነጋገር ይልቅ አገልጋዩን ልኮ ንዕማንን እንዲቀበለውና እንዲህ ብሎ እንዲነግረው አዘዘው፦ ‘ሂድና ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ሰባት ጊዜ ታጠብ። ከዚያ ትድናለህ።’

በዚህ ጊዜ ንዕማን በጣም ተቆጣ። እንዲህ አለ፦ ‘እኔ እኮ ይህ ነቢይ የአምላኩን ስም እየጠራ ለየት ያለ ነገር አድርጎ የሚያድነኝ መስሎኝ ነበር። እሱ ግን እስራኤል ውስጥ በሚገኘው በዚህ ወንዝ ውስጥ ታጠብ ይለኛል። ሶርያ ውስጥ ከዚህ የተሻሉ ወንዞች አሉን። እዚያው አልታጠብም ነበር?’ ንዕማን በጣም ተናዶ አካባቢውን ለቆ ሄደ።

በኋላ ግን የንዕማን አገልጋዮች አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል ረዱት። እንዲህ አሉት፦ ‘ለመዳን ስትል ማንኛውንም ነገር ታደርግ የለ? ይህ ነቢይ እንድታደርግ የነገረህ ነገር ደግሞ በጣም ቀላል ነው። ታዲያ ለምን እሱ ያለህን አታደርግም?’ ንዕማን አገልጋዮቹ እንዳሉት አደረገ። ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሄዶ ሰባት ጊዜ ውኃው ውስጥ ብቅ ጥልቅ አለ። ንዕማን ለሰባተኛ ጊዜ ውኃው ውስጥ ገብቶ ሲወጣ ከሕመሙ ሙሉ በሙሉ ዳነ። በጣም ደስ ስላለው ኤልሳዕን ለማመስገን ተመልሶ ሄደ። ኤልሳዕንም ‘እውነተኛው አምላክ ይሖዋ እንደሆነ አሁን አወቅኩ’ አለው። ትንሿ እስራኤላዊት ልጅ ንዕማን ድኖ ወደ ቤት ሲመለስ ስታይ ምን የተሰማት ይመስልሃል?

“ከልጆችና ከሕፃናት አፍ ምስጋና አዘጋጀህ።”—ማቴዎስ 21:16