በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 61

ለወርቁ ምስል አልሰገዱም

ለወርቁ ምስል አልሰገዱም

ንጉሥ ናቡከደነጾር ግዙፉን ምስል በሕልሙ ካየ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አንድ ትልቅ የወርቅ ምስል ሠራ። ምስሉን በዱራ ሜዳ ካቆመው በኋላ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን ጨምሮ በባቢሎን የሚኖሩ ታላላቅ ሰዎች በምስሉ ፊት እንዲሰበሰቡ አደረገ። ንጉሡም እንዲህ በማለት አዘዘ፦ ‘የቀንደ መለከት፣ የበገናና የዋሽንት ድምፅ ስትሰሙ በግንባራችሁ ተደፍታችሁ ለምስሉ ስገዱ! ለምስሉ የማይሰግድ ማንኛውም ሰው ወደ እቶን እሳት ይጣላል።’ ታዲያ ሦስቱ ዕብራውያን ለምስሉ በመስገድ ጣዖት ያመልካሉ ወይስ ይሖዋን ብቻ ለማምለክ ቁርጥ ውሳኔ ያደርጋሉ?

ከዚያም ንጉሡ የሙዚቃው ድምፅ እንዲሰማ አዘዘ። በዚህ ጊዜ ከሲድራቅ፣ ከሚሳቅና ከአብደናጎ በስተቀር ሌሎቹ ሰዎች በሙሉ ተደፍተው ምስሉን አመለኩ። አንዳንዶቹ ሰዎች ይህን ሲያዩ ንጉሡን ‘እነዚያ ሦስት ዕብራውያን ላቆምከው የወርቅ ምስል ለመስገድ እንቢ ብለዋል’ አሉት። ናቡከደነጾርም ሦስቱን ዕብራውያን አስጠራቸውና እንዲህ አላቸው፦ ‘አንድ ተጨማሪ ዕድል እሰጣችኋለሁ፤ ለወርቅ ምስሉ ካልሰገዳችሁ ወደ እቶን እሳቱ ትጣላላችሁ። ከእኔ ሊያድናችሁ የሚችል አምላክ የለም።’ እነሱም እንዲህ በማለት መለሱለት፦ ‘ሌላ ዕድል አያስፈልገንም። አምላካችን ሊያድነን ይችላል። ሆኖም ንጉሥ ሆይ፣ እሱ ባያድነንም እንኳ ያቆምከውን ምስል አናመልክም።’

ናቡከደነጾር በጣም ተናደደ። አገልጋዮቹንም ‘እሳቱ ከበፊቱ ይበልጥ ሰባት እጥፍ እንዲነድ አድርጉ!’ አላቸው። ከዚያም ወታደሮቹን ‘እነዚህን ሰዎች አስራችሁ ወደ እሳቱ ጣሏቸው!’ በማለት አዘዛቸው። እሳቱ በጣም ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ወታደሮቹ ገና ወደ እሳቱ ሲጠጉ ወዲያውኑ ተቃጥለው ሞቱ። ሦስቱ ዕብራውያን የእቶን እሳቱ ውስጥ ተጣሉ። ሆኖም ናቡከደነጾር ወደ ውስጥ ሲመለከት ሦስት ሳይሆን አራት ሰዎች እሳቱ ውስጥ ሲመላለሱ አየ። የተመለከተው ነገር በጣም ስላስደነገጠው ባለሥልጣናቱን እንዲህ በማለት ጠየቃቸው፦ ‘እሳት ውስጥ የጣልናቸው ሰዎች ሦስት አልነበሩም እንዴ? አሁን ግን የሚታዩኝ አራት ሰዎች ናቸው፤ አንዱ ደግሞ መልአክ ይመስላል!’

ናቡከደነጾር ወደ እሳቱ ተጠግቶ ‘እናንተ የልዑል አምላክ አገልጋዮች፣ ወጥታችሁ ወደዚህ ኑ!’ አለ። በዚያ የነበሩት ሰዎች በሙሉ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ከእሳቱ ሲወጡ በጣም ተደነቁ። ሰውነታቸው፣ ፀጉራቸውና ልብሳቸው አልተቃጠለም ነበር፤ የጭስ ሽታም እንኳ በላያቸው አልነበረም።

ናቡከደነጾር እንዲህ አለ፦ ‘የሲድራቅ፣ የሚሳቅና የአብደናጎ አምላክ ታላቅ አምላክ ነው። መልአኩን ልኮ አድኗቸዋል። እንደ እነሱ አምላክ ያለ ሌላ አምላክ የለም።’

አንተስ እንደ ሦስቱ ዕብራውያን ምንም ቢመጣ ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን ወስነሃል?

“ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ።”—ማቴዎስ 4:10