በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 62

በትልቅ ዛፍ የተመሰለ መንግሥት

በትልቅ ዛፍ የተመሰለ መንግሥት

አንድ ቀን ናቡከደነጾር ተኝቶ ሳለ የሚያስፈራ ሕልም አየ። በመሆኑም የባቢሎንን ጥበበኛ ሰዎች አስጠርቶ የሕልሙን ትርጉም ጠየቃቸው። ሆኖም አንዳቸውም ትርጉሙን ሊነግሩት አልቻሉም። በመጨረሻም ዳንኤልን አስጠራውና የሕልሙን ትርጉም ጠየቀው።

ናቡከደነጾር ዳንኤልን እንዲህ አለው፦ ‘በሕልሜ አንድ ዛፍ አየሁ። ዛፉ በጣም አድጎ ሰማይ ደረሰ። ከየትም ቦታ ሆኖ ይህን ዛፍ ማየት ይቻል ነበር። የሚያማምሩ ቅጠሎችና ብዙ ፍሬዎች ነበሩት። እንስሳት በጥላው ሥር ያርፉ፣ ወፎችም በቅርንጫፎቹ ላይ ጎጇቸውን ይሠሩ ነበር። ከዚያም አንድ መልአክ ከሰማይ ወረደ። እንዲህም አለ፦ “ዛፉን ቁረጡ፤ ቅርንጫፎቹንም ጨፍጭፉ። ጉቶው ግን በብረትና በመዳብ ታስሮ ከነሥሩ መሬት ውስጥ ይቆይ። ልቡ ከሰው ልብ ይለወጥ፤ የአውሬም ልብ ይሰጠው፤ እንደዚያም ሆኖ ለሰባት ዘመናት ይቆይ። ሁሉም ሰዎች አምላክ በሁሉም ላይ ገዢ እንደሆነና መንግሥቱን ለፈለገው ሰው እንደሚሰጥ ይገነዘባሉ።”’

ይሖዋ ለዳንኤል የዚህን ሕልም ትርጉም ገለጠለት። ዳንኤል የሕልሙን ትርጉም ሲረዳ ደነገጠ። ከዚያም ንጉሡን እንዲህ አለው፦ ‘ንጉሥ ሆይ፣ ሕልሙ ስለ ጠላቶችህ ቢሆን ደስ ይለኝ ነበር፤ ሆኖም ሕልሙ አንተን የሚመለከት ነው። የተቆረጠው ትልቅ ዛፍ አንተ ነህ። መንግሥትህ ከአንተ ይወሰዳል፤ እንዲሁም እንደ ዱር እንስሳ በሜዳ ላይ ሣር ትበላለህ። ሆኖም መልአኩ ጉቶው ከነሥሩ መሬት ውስጥ እንደሚቆይ ስለተናገረ በድጋሚ ንጉሥ ትሆናለህ።’

ከአንድ ዓመት በኋላ አንድ ቀን ንጉሡ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ እየተመላለሰ ባቢሎንን በአድናቆት ይመለከት ነበር። ከዚያም እንዲህ አለ፦ ‘የገነባኋትን አስደናቂ ከተማ ተመልከቱ። እንደ እኔ ያለ ታላቅ ንጉሥ የለም!’ ልክ እየተናገረ ሳለ ከሰማይ የመጣ አንድ ድምፅ ‘ናቡከደነጾር! አሁን መንግሥትህ ከአንተ ተወስዷል’ አለው።

ወዲያውኑ ናቡከደነጾር አእምሮውን ስቶ እንደ ዱር እንስሳ ሆነ። ስለሆነም ከቤተ መንግሥቱ ወጥቶ ከዱር እንስሳት ጋር መኖር ጀመረ። የናቡከደነጾር ፀጉር እንደ ንስር ላባ ረዘመ፤ ጥፍሮቹም አድገው እንደ ወፍ ጥፍሮች ሆኑ።

ሰባት ዓመታት ካለፉ በኋላ ናቡከደነጾር እንደገና ጤናማ ሆነ፤ ይሖዋም የባቢሎን ንጉሥ አደረገው። ከዚያም ናቡከደነጾር እንዲህ አለ፦ ‘የሰማያት ንጉሥ የሆነውን ይሖዋን አወድሳለሁ። አሁን ይሖዋ በሁሉም ላይ ገዢ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። ኩራተኞችን ያዋርዳል፤ ንጉሣዊ ሥልጣንንም ለፈለገው ሰው መስጠት ይችላል።’

“ኩራት ጥፋትን፣ የትዕቢት መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል።”—ምሳሌ 16:18