በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 64

ዳንኤል አንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ተጣለ

ዳንኤል አንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ተጣለ

በባቢሎን ላይ የነገሠው ሌላው ንጉሥ ደግሞ ሜዶናዊው ዳርዮስ ነበር። ዳርዮስ፣ ዳንኤል ከሌሎቹ ባለሥልጣናት ሁሉ የተለየ እንደሆነ አስተዋለ። ስለዚህ ዳንኤልን በባለሥልጣናቱ ላይ ሾመው። እነዚህ ሰዎች በዳንኤል ስለቀኑ ሊገድሉት ፈለጉ። ዳንኤል በየቀኑ ሦስት ጊዜ ወደ ይሖዋ እንደሚጸልይ ያውቁ ነበር፤ ስለዚህ ዳርዮስን እንዲህ አሉት፦ ‘ንጉሥ ሆይ፣ ሁሉም ሰው ወደ አንተ ብቻ እንዲጸልይ የሚያዝዝ ሕግ ይውጣ። ይህን ሕግ የማያከብር ማንኛውም ሰው ወደ አንበሶች ጉድጓድ ይጣል።’ ዳርዮስ በሐሳባቸው ተስማማ፤ ስለዚህ በሕጉ ላይ ፈረመ።

ዳንኤል ስለ አዲሱ ሕግ እንደሰማ ወደ ቤቱ ሄደ። የቤቱም መስኮት ተከፍቶ ነበር፤ ዳንኤልም መስኮቱ አጠገብ ተንበርክኮ ወደ ይሖዋ ጸለየ። በዳንኤል የቀኑት ሰዎች በሩን በርግደው ሲገቡ ዳንኤልን ሲጸልይ አገኙት። ስለዚህ ወደ ዳርዮስ ሄደው እንዲህ አሉት፦ ‘ዳንኤል አንተን አይታዘዝም። በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላኩ ይጸልያል።’ ዳርዮስ ዳንኤልን ይወደው ስለነበር እንዲሞት አልፈለገም። ቀኑን ሙሉ ዳንኤልን ማዳን የሚችልበትን መንገድ ሲያስብ ዋለ። ሆኖም ንጉሡ የፈረመበትን ሕግ ራሱም እንኳ ሊቀይረው አይችልም ነበር። ስለዚህ ዳንኤልን አስፈሪ አንበሶች ወዳሉበት ጉድጓድ እንዲጥሉት ትእዛዝ አስተላለፈ።

በዚያ ሌሊት ዳርዮስ የዳንኤል ነገር በጣም ስላስጨነቀው እንቅልፍ ሊወስደው አልቻለም። በጠዋት ወደ ጉድጓዱ ሄዶ ዳንኤልን ‘አምላክህ ከአንበሶቹ አድኖሃል?’ አለው።

በዚህ ጊዜ ዳርዮስ አንድ ድምፅ ሰማ። የሰማው የዳንኤልን ድምፅ ነበር! ዳንኤል ዳርዮስን እንዲህ አለው፦ ‘የይሖዋ መልአክ የአንበሶቹን አፍ ዘጋ። ስለዚህ አንበሶቹ ምንም አልጎዱኝም።’ ዳርዮስ ይህን ሲሰማ በጣም ተደሰተ! ዳንኤልን ከጉድጓዱ እንዲያወጡት አዘዘ። ዳንኤል ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰበትም ነበር። ከዚያም ንጉሡ ‘ዳንኤልን የከሰሱትን ሰዎች አምጥታችሁ ጉድጓዱ ውስጥ ጣሏቸው’ በማለት አዘዘ። እነዚያ ሰዎች ወደ ጉድጓዱ ሲጣሉ አንበሶቹ በሏቸው።

ዳርዮስ እንዲህ በማለት ለሕዝቡ ትእዛዝ አስተላለፈ፦ ‘ሁሉም ሰው የዳንኤልን አምላክ መፍራት አለበት። ምክንያቱም ዳንኤልን ከአንበሶቹ አድኖታል።’

አንተስ እንደ ዳንኤል በየቀኑ ወደ ይሖዋ ትጸልያለህ?

“ይሖዋ፣ ለአምላክ ያደሩ ሰዎችን ከፈተና እንዴት እንደሚያድን . . . ያውቃል።”—2 ጴጥሮስ 2:9