በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 65

አስቴር ሕዝቧን ከጥፋት አዳነች

አስቴር ሕዝቧን ከጥፋት አዳነች

አስቴር የፋርስ ከተማ በሆነችው በሹሻን የምትኖር አይሁዳዊት ነበረች። ከብዙ ዓመታት በፊት ናቡከደነጾር የአስቴርን ቤተሰቦች ከኢየሩሳሌም ወደ ሹሻን አምጥቷቸው ነበር። አስቴርን ያሳደጋት የአጎቷ ልጅ የሆነው መርዶክዮስ ሲሆን እሱም የፋርሱ ንጉሥ የአሐሽዌሮስ አገልጋይ ነበር።

ንጉሥ አሐሽዌሮስ አዲስ ንግሥት ለመምረጥ ፈለገ። ስለዚህ አገልጋዮቹ በአገሪቱ ያሉትን ቆንጆ ሴቶች አመጡለት፤ ካመጡለት ሴቶች መካከል አስቴርም ትገኝበት ነበር። ንጉሡ ከመጡት ሴቶች በሙሉ ንግሥት እንድትሆን የመረጠው አስቴርን ነው። መርዶክዮስ አስቴርን አይሁዳዊ መሆኗን ለማንም እንዳትናገር አዟት ነበር።

ሃማ የተባለ አንድ ኩራተኛ ሰው ከሌሎቹ መኳንንት ሁሉ የበላይ ሆኖ ተሾመ። ሃማ ሰው ሁሉ እንዲሰግድለት ይፈልግ ነበር። መርዶክዮስ ለሃማ ለመስገድ ፈቃደኛ አልሆነም፤ ሃማ በዚህ በጣም ስለተበሳጨ መርዶክዮስን ሊገድለው ፈለገ። ሃማ፣ መርዶክዮስ አይሁዳዊ መሆኑን ሲሰማ በአገሪቱ የሚገኙትን አይሁዳውያን በሙሉ ለማስገደል አሰበ። ከዚያም ንጉሡን ‘አይሁዳውያን በጣም አደገኛ ሰዎች ናቸው፤ እነሱን ማጥፋት አለብህ’ አለው። አሐሽዌሮስም ሃማን ‘የፈለግከውን ማድረግ ትችላለህ’ አለው፤ ሕግ ለማውጣት የሚያስችል ሥልጣንም ሰጠው። ሃማ፣ አዳር በተባለው ወር በ13ኛው ቀን ሕዝቡ አይሁዳውያንን በሙሉ እንዲገድሉ የሚያዝዝ ሕግ አወጣ። ይሖዋ ይህ ሁሉ ሲፈጸም ይመለከት ነበር።

አስቴር ይህ ሕግ መውጣቱን አላወቀችም ነበር። ስለዚህ መርዶክዮስ የወጣውን ሕግ ቅጂ ለአስቴር ላከላትና ‘ሄደሽ ንጉሡን አነጋግሪው’ አላት። አስቴር ግን እንዲህ ብላ መለሰችለት፦ ‘ሳይጠራ ወደ ንጉሡ የሚሄድ ሰው በሙሉ ይገደላል። ንጉሡ ደግሞ እኔን ለ30 ቀን ያህል አልጠራኝም! ቢሆንም እሄዳለሁ። ንጉሡ በትረ መንግሥቱን ከዘረጋልኝ በሕይወት እተርፋለሁ። ካልዘረጋልኝ ግን እሞታለሁ።’

አስቴር ወደ ንጉሡ ግቢ ሄደች። ንጉሡ አስቴርን ሲያያት በትረ መንግሥቱን ዘረጋላት። እሷም ወደ እሱ ቀረበች፤ ንጉሡም ‘አስቴር፣ ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ?’ አላት። እሷም ‘አንተና ሃማ ዛሬ ባዘጋጀሁት ግብዣ ላይ እንድትገኙልኝ እፈልጋለሁ’ አለችው። በግብዣው ላይ፣ አስቴር በቀጣዩ ቀን በምታዘጋጀው ሌላ ግብዣ ላይ እንዲገኙ አሐሽዌሮስንና ሃማን ጋበዘቻቸው። በሁለተኛው ግብዣ ላይ ንጉሡ በድጋሚ ‘አስቴር፣ ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ?’ ብሎ ጠየቃት። አስቴርም ‘አንድ ሰው እኔንና ሕዝቤን ሊገድለን ነው። እባክህ አድነን’ አለችው። ንጉሡም ‘ለመሆኑ ይህ ሰው ማን ነው?’ በማለት ጠየቃት። እሷም ‘ይህ ክፉ ሰው ሃማ ነው’ አለችው። አሐሽዌሮስ በጣም በመናደዱ ወዲያውኑ ሃማን አስገደለው።

ይሁንና ሃማ ያወጣውን ሕግ ንጉሡ ራሱም እንኳ ሊሽረው አይችልም ነበር። ስለዚህ ንጉሡ መርዶክዮስን በመኳንንቱ ላይ ሾመውና አዲስ ሕግ እንዲያወጣ ሥልጣን ሰጠው። መርዶክዮስ አይሁዳውያን በጠላቶቻቸው ላይ ጥቃት በመሰንዘር ራሳቸውን እንዲከላከሉ የሚፈቅድ ሕግ አወጣ። በመሆኑም አዳር በተባለው ወር በ13ኛው ቀን አይሁዳውያን ጠላቶቻቸውን አሸነፉ። ከዚያ ጊዜ አንስቶ በየዓመቱ ይህን ቀን ማክበር ጀመሩ።

“በእኔ ምክንያት በገዢዎችና በነገሥታት ፊት ያቀርቧችኋል፤ በዚያ ጊዜ ለእነሱም ሆነ ለአሕዛብ መመሥከር ትችላላችሁ።”—ማቴዎስ 10:18