በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 71

ይሖዋ ኢየሱስን ጠበቀው

ይሖዋ ኢየሱስን ጠበቀው

ከእስራኤል በስተ ምሥራቅ ባለ አንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ከዋክብት መንገድ እያሳዩ ወደተለያዩ ቦታዎች ይወስዳሉ ብለው ያምኑ ነበር። በዚያ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች አንድ ቀን ምሽት ላይ ደማቅ ኮከብ የሚመስል ነገር በሰማይ ላይ ሲሄድ አዩ፤ ስለዚህ “ኮከቡን” ተከትለው ሄዱ። “ኮከቡ” ወደ ኢየሩሳሌም መራቸው። የአይሁዳውያን ንጉሥ የሚሆን ልጅ እንደሚወለድ አውቀው ነበር። በመሆኑም በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ሰዎች እንዲህ በማለት ጠየቁ፦ ‘የአይሁዳውያን ንጉሥ የሚሆነው ልጅ የት አለ? ለእሱ ልንሰግድ መጥተናል።’

የኢየሩሳሌም ንጉሥ የሆነው ሄሮድስ አዲስ ንጉሥ መወለዱን ሲሰማ በጣም ተጨነቀ። በመሆኑም የካህናት አለቆችን ሰብስቦ ‘ንጉሥ የሚሆነው ልጅ የት ነው ያለው?’ በማለት ጠየቃቸው። እነሱም ‘ነቢያት በቤተልሔም እንደሚወለድ ተናግረዋል’ አሉት። ስለዚህ ሄሮድስ ከምሥራቅ የመጡትን ሰዎች ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ ‘ወደ ቤተልሔም ሄዳችሁ ሕፃኑን ፈልጉት። ከዚያም ተመልሳችሁ የት እንዳለ ንገሩኝ። እኔም ልሰግድለት እፈልጋለሁ።’ ሆኖም ሄሮድስ እንዲህ ያለው ውሸቱን ነበር።

“ኮከቡ” እንደገና መንቀሳቀስ ጀመረ። ሰዎቹም ተከትለውት ወደ ቤተልሔም ሄዱ። ከዚያም “ኮከቡ” አንድ ቤት ጋ ሲደርስ ቆመ፤ ሰዎቹም ወደ ውስጥ ገቡ። ቤት ውስጥ ኢየሱስን ከእናቱ ከማርያም ጋር አገኙት። ከዚያም ሰገዱለት እንዲሁም ወርቅ፣ ነጭ ዕጣንና ከርቤ ስጦታ አድርገው ሰጡት። እነዚህን ሰዎች ወደ ኢየሱስ የመራቸው በእርግጥ ይሖዋ ነው? አይደለም።

ያን ቀን ምሽት ላይ ይሖዋ ለዮሴፍ በሕልም እንዲህ አለው፦ ‘ሄሮድስ ኢየሱስን ሊገድለው ይፈልጋል። ስለዚህ ሚስትህንና ልጅህን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ። እኔ እንድትመለስ እስክነግርህ ድረስ እዚያው ቆይ።’ ዮሴፍም ወዲያውኑ ቤተሰቡን ይዞ ወደ ግብፅ ሄደ።

ይሖዋ ከምሥራቅ የመጡትን ሰዎች ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ ነገራቸው። ሄሮድስ ሰዎቹ ተመልሰው እንዳልመጡ ሲያውቅ በጣም ተናደደ። ኢየሱስን ሊያገኘው ስላልቻለ ቤተልሔም ውስጥ በኢየሱስ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወንዶች ልጆች በሙሉ እንዲገደሉ አዘዘ። ኢየሱስ ግን ዮሴፍ ወደ ግብፅ ይዞት ሄዶ ስለነበር አልተገደለም።

ከጊዜ በኋላ ሄሮድስ ሞተ። ይሖዋም ዮሴፍን ‘አሁን መመለስ ትችላለህ’ አለው። ስለዚህ ዮሴፍ፣ ማርያምና ኢየሱስ ወደ እስራኤል ተመልሰው በናዝሬት ከተማ መኖር ጀመሩ።

“ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ እንዲሁ ይሆናል። . . . የተላከበትንም ዓላማ በእርግጥ ይፈጽማል።”—ኢሳይያስ 55:11