በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 72

ኢየሱስ በአሥራ ሁለት ዓመቱ

ኢየሱስ በአሥራ ሁለት ዓመቱ

ዮሴፍና ማርያም ከኢየሱስና ከሌሎች ልጆቻቸው ጋር በናዝሬት ይኖሩ ነበር። ዮሴፍ የአናጺነት ሥራ በመሥራት ቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ያቀርብ ነበር፤ እንዲሁም ቤተሰቡን ስለ ይሖዋና ስለ ሕጉ አስተምሯል። ቤተሰቡ አዘውትረው ወደ ምኩራብ በመሄድ አምልኳቸውን ያከናውኑ ነበር፤ እንዲሁም በየዓመቱ የፋሲካ በዓልን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ይጓዛሉ።

ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ ሳለ ቤተሰቡ እንደተለመደው ረጅም ርቀት ተጉዘው ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ። ኢየሩሳሌም የፋሲካ በዓልን ለማክበር በመጡ ሰዎች ተጨናንቃ ነበር። ዮሴፍና ማርያም በዓሉን ካከበሩ በኋላ ወደ ቤታቸው ለመመለስ ጉዞ ጀመሩ፤ በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አብረዋቸው ከሚጓዙት ሰዎች ጋር ያለ መስሏቸው ነበር። ሆኖም ዘመዶቻቸው ጋ ሲፈልጉት ሊያገኙት አልቻሉም።

ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ለሦስት ቀን ያህል ሲፈልጉት ቆዩ። በመጨረሻም ወደ ቤተ መቅደሱ ሄዱ። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ባሉ አስተማሪዎች መካከል ቁጭ ብሎ በደንብ እያዳመጣቸውና ጥያቄ እየጠየቃቸው ነበር። አስተማሪዎቹ በጣም ከመገረማቸው የተነሳ እነሱም ጥያቄ ይጠይቁት ጀመር። በሚሰጣቸውም መልስ በጣም ተደነቁ። ኢየሱስ የይሖዋን ሕግ በሚገባ እንደሚያውቅ ማስተዋል ቻሉ።

ዮሴፍና ማርያም በጣም ተጨንቀው ነበር። ማርያም ኢየሱስን እንዲህ አለችው፦ ‘ልጄ፣ እኛ እኮ አንተን ፍለጋ ያልሄድንበት ቦታ የለም! የት ሄደህ ነው?’ እሱም ‘በአባቴ ቤት መሆን እንደሚገባኝ አታውቁም?’ አላቸው።

ኢየሱስ ከወላጆቹ ጋር ወደ ናዝሬት ተመለሰ። ዮሴፍ ኢየሱስን የአናጺነት ሙያ አስተማረው። ኢየሱስ በወጣትነቱ ምን ዓይነት ሰው የነበረ ይመስልሃል? ኢየሱስ እያደገ ሲመጣ ይበልጥ ጥበበኛ እየሆነ እንዲሁም በአምላክና በሰው ፊት ሞገስ እያገኘ ሄደ።

“አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው።”—መዝሙር 40:8