በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 75

ዲያብሎስ ኢየሱስን ፈተነው

ዲያብሎስ ኢየሱስን ፈተነው

ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው። ለ40 ቀን ያህል ምንም አልበላም፤ ስለዚህ በጣም ራበው። ከዚያም ዲያብሎስ ሊፈትነው መጣና እንዲህ አለው፦ ‘እስቲ የአምላክ ልጅ ከሆንክ እነዚህን ድንጋዮች ዳቦ እንዲሆኑ እዘዛቸው።’ ኢየሱስ ግን ከቅዱሳን መጻሕፍት በመጥቀስ እንዲህ አለው፦ ‘“ሰው በምግብ ብቻ አይኖርም” ተብሎ ተጽፏል። ይሖዋ የሚናገረውን ቃል መስማትም አስፈላጊ ነው።’

ቀጥሎ ደግሞ ዲያብሎስ እንዲህ በማለት ኢየሱስን ፈተነው፦ ‘እስቲ የአምላክ ልጅ ከሆንክ ከቤተ መቅደሱ አናት ዝለል። “አምላክ መላእክቱን ልኮ ጉዳት እንዳይደርስብህ ይጠብቅሃል” ተብሎ ተጽፏል።’ ኢየሱስ ግን በድጋሚ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመጥቀስ ‘“ይሖዋን አትፈታተነው” ተብሎ ተጽፏል’ አለው።

ከዚያም ሰይጣን የዓለምን መንግሥታት በሙሉ እንዲሁም ሀብታቸውንና ክብራቸውን ለኢየሱስ አሳየውና ‘አንድ ጊዜ ብቻ ብታመልከኝ እነዚህን ሁሉ መንግሥታትና ክብራቸውን በሙሉ እሰጥሃለሁ’ አለው። ኢየሱስ ግን ‘ሂድ፣ አንተ ሰይጣን! “ይሖዋን ብቻ አምልክ” ተብሎ ተጽፏል’ አለው።

ከዚያም ዲያብሎስ ሄደ፤ መላእክትም መጥተው ለኢየሱስ የሚበላው ምግብ ሰጡት። ከዚያ ጊዜ አንስቶ ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስበክ ጀመረ። ወደ ምድር የተላከው ይህን ሥራ እንዲሠራ ነው። ሕዝቡ ኢየሱስ የሚያስተምራቸውን ትምህርት ይወዱት ነበር፤ እንዲሁም በሚሄድበት ቦታ ሁሉ ይከተሉት ነበር።

“[ዲያብሎስ] ውሸታምና የውሸት አባት ስለሆነ ውሸት ሲናገር ከራሱ አመንጭቶ ይናገራል።”—ዮሐንስ 8:44