በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 81

የተራራው ስብከት

የተራራው ስብከት

ኢየሱስ 12 ሐዋርያቱን ከመረጠ በኋላ ከተራራው ወርዶ ብዙ ሕዝብ ወደተሰበሰበበት ቦታ ሄደ። ሰዎቹ የመጡት ከገሊላ፣ ከይሁዳ፣ ከጢሮስ፣ ከሲዶና፣ ከሶርያና ከዮርዳኖስ ማዶ ሲሆን የታመሙና በአጋንንት የተያዙ ሰዎችን ይዘው መጥተው ነበር። ኢየሱስ ሁሉንም ፈወሳቸው። ከዚያም ተራራው ላይ ተቀምጦ መናገር ጀመረ። የይሖዋ ወዳጅ መሆን ከፈለግን ምን ማድረግ እንዳለብን ተናገረ። የይሖዋ አመራር እንደሚያስፈልገን ማወቅና እሱን መውደድ አለብን። ሆኖም ሌሎች ሰዎችን የማንወድ ከሆነ ‘አምላክን እወደዋለሁ’ ማለት አንችልም። ጠላቶቻችንን ጨምሮ ለሰው ሁሉ ደግና የማናዳላ መሆን አለብን።

ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ ‘ጓደኞቻችሁን ብቻ መውደዳችሁ በቂ አይደለም። ጠላቶቻችሁንም መውደድና ሰዎችን ከልባችሁ ይቅር ማለት አለባችሁ። አንድን ሰው ቅር ካሰኛችሁ ቶሎ ወደ እሱ ሄዳችሁ ይቅርታ ጠይቁ። ሌሎች ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናንተም አድርጉላቸው።’

በተጨማሪም ኢየሱስ ለሰዎቹ ገንዘብን በተመለከተ ጥሩ ምክር ሰጥቷቸዋል። እንዲህ አላቸው፦ ‘የይሖዋ ወዳጅ መሆን ሀብታም ከመሆን ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ገንዘባችሁን ሌባ ሊሰርቀው ይችላል፤ ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት ግን ማንም ሊሰርቅባችሁ አይችልም። ምን እንበላለን፣ ምን እንጠጣለን ወይም ምን እንለብሳለን ብላችሁ አትጨነቁ። ወፎችን ተመልከቱ። አምላክ ሁልጊዜ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ይሰጣቸዋል። መጨነቃችሁ በዕድሜያችሁ ላይ አንድም ቀን ሊጨምርላችሁ አይችልም። ይሖዋ ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃል።’

የተሰበሰቡት ሰዎች ማንም ሰው እንደ ኢየሱስ ሲያስተምር ሰምተው አያውቁም ነበር። የሃይማኖት መሪዎቻቸው የሆኑት ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን እነዚህን ነገሮች አላስተማሯቸውም። ኢየሱስ እንዲህ ያለ ጥሩ አስተማሪ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? የሚያስተምረው ከይሖዋ የተማረውን ብቻ ስለነበረ ነው።

“ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ፤ ለራሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ።”—ማቴዎስ 11:29